1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደመራ በዓል በአትላንታ

ማክሰኞ፣ መስከረም 17 2015

በአትላንታና አካባቢው የሚኖሩኢትዮጵያውያን የተገኙበት መርሐ ግብር በጸሎት ተጀምሮ የወረብና የተለያዩ በዓሉን የተመለከቱ ያሬዳዊ መዝሙሮች ቀርበውበታል።የጆርጂያና አካባቢው ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት ቃለምዕዳንና ቡራኬ፣በዓሉ ሲከበር ስለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በማሰብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

https://p.dw.com/p/4HQ3z
USA | Meskel Damera Feierlichkeiten in Atlanta
ምስል Tariku Hailu/DW

የደመራ በዓል በአትላንታ

 አትላንታና አካባቢዉ-ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉን የደመራን በዓል ትናንት አክብሩ።በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የጆርጅያና አካባቢዉ ሐገረ ስብከት ሊቀጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ለበዓሉ ለታደሙት ባስተላለፉት መልዕክት ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ ስለሰላምና አንድነት ማሰብና መጸለይ አለባቸዉ።የአትላንታዉ ወኪላችን ታሪኩ ኃይሉ እንደዘገበዉ በበዓሉ ላይ በከተማይቱ የሚገኙ ሰባት አድባራት ተካፍለዋል።

በአትላንታና አካባቢው የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተገኙበት ይኸው መርሐ ግብር በጸሎት ተጀምሮ የወረብና የተለያዩ በዓሉን የተመለከቱ ያሬዳዊ መዝሙሮች ቀርበውበታል።የጆርጂያና አካባቢው ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት ቃለምዕዳንና ቡራኬ፣በዓሉ ሲከበር ስለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በማሰብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

"ሁላችሁም ይህን በዓል ስናከብር ከልባችን እንደመሆኑ መጠን ብትሄዱም በየቤታችሁ እግዚአብሔርን ለምኑ ስለሃገራችን ሰላም ስለአንድነታችን ሰላም ስለወገኖቻችን ሰላም ስለዓለማችን ሰላም ወደየቤተክርስትያኑ በምትሄዱበትም ሆነ በቤታችሁ ስትተኙ ስትነሱ ይህ የሰላም ነገር በውነት ርቆናልናልና ሰላምን ለሃገራችን እግዚአብሔር ለሃገራችን ይላክ።እንዲሁም ደግሞ፣የሚቀጥለውን ዓመት በሰላም ደርሰን በሃገራችንም ዛሬ ያለው ንፋስ ተወግዶ መልካም ንፋስ ወርዶ  የሰላም ንፋስ የሰላም ምርት የሰላም ምርት፣ህፃናት ተወልደው በሰላም ሃገራችን አምና እንዲህ ነበር ዘንድሮ ግን ደስ አለን ብለን እናቶች በልጆቻቸው የሚደሰቱበት ያድርግልን።"

በስነስርዓቱ ላይ ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣የሃገረ ስብከቱ ዋና ስርአስኪያጅና በአትላንታ የዳግማዊ ቁሉቢ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል በአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ መጋቤ አዲስ ይልማ ቸርነት፣በመስቀሉ ፍቅር በመሸነፍ ይቅርታና ሰላም ማስፈን ይገባል ብለዋል።

USA | Meskel Damera Feierlichkeiten in Atlanta
ምስል Tariku Hailu/DW

"ዛሬ አንገታችንን በሚያሰብር አንገታችንን በሚያስደፋ አሳዛኝ በዚህ በሰለጠነ ዘመን እርስ በርሳችን ወደመባላት ሄደናል።አሳፋሪ አስደንጋጭ አሰቃቂ ዕለት ዕለት ሞት እንሰማለን።እናቶች ልጆች አረጋዊያን ሁሉ በጣም አፍረናል በውነቱ እና አሁን ግን በተለይ መሪዎችየፖለቲካ አመራር ያሉ በየቡድኑ የሚመሩ ሁሉ ይህ የማይረባና የማይጠቅም መሆኑን አውቀው ክርስትያኖች ሙስሊሞችም ሁሉ አሁን በሰሜን በኩል ክርስትናውን ይዘናል እነዚህ ሁሉ በውነት መስቀል ይዞ ነውር መስራት ተገቢ ስላልሆነ በመስቀሉ ፍቅር ተሸንፈንና ተገዝተን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ማንም ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉን ይሸከም ነው የሚለውና ክርስትያን ማለት የክርስቶስን መስቀል የተሸከመ በክርስቶስ ፍቅርና ትምህርት በይቅርታ የሚኖር በመስቀሉ ላይ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ይቅርታ ያወጀ ጌታ ስለሆነ ለዚህ ፍቅርና ይቅርታ የአምላካዊ ምህረት ተሸንፈን ይቅርታ ወርዶ ሰላም ታውጆ ክፋት ከምድራችን ተነቅሎ እንደ አደይ አበባው ጌጥ ውበት ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅርና ዝማሬ ተውባ በፍቅርና በአንድነት እንድንኖር የመስቀሉ ሚስጥር ያስተምረናል።"

የመስቀሉ ዓላማ ህብረት ነው ያሉት የሃገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ፣ቤተክርስትያን በዓሉን ስታከብር የምታስተምረው ሁሉም የሰላም ሐዋሪያ እንዲሆን ነው ሲሉ አስረድተዋል።

"እኛም ሆንን ቅድስት ቤተክርስትያን የምታስተላልፈው መልዕክት ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ መስቀሉን በሚገባ ተረዱትና ጦርነትን ጠብን ክፋትን ተንኮልን ክፉ ንግግርን ይህን የምንሰማው አሳዛኝ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጣላ ንግግር ቆሞ ሁሉም የሰም ሐዋሪያ የሰላም ሰባኪ የሰላም መምህር ሆኖ መሪዎችም ደግሞ ራሳቸውንና እልኻቸውን አሸንፈው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደቀድሞ ሁሉ አንድ እንዲያደርጉት የተሳሳተ ነገር ካለ ያንን ማረም አረሙን መንቀል ስንዴውን ግን መንከባከብ ያስፈልጋል እላለሁ እና የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ይህን በጎ ዐሳብ በአባቶቻችን ሁሉ የሚነገረውን እንዲፈጸምልን ሊቃውንት ለጠቢባን ሁሉ ብልሃት ጥበብ እንዲሰጥልን ክፉውን ጨለማውን ጭጋጋማ ነገር ከፊታቸው እንዲገፍ እንለምናለን ቤተክርስትያን ትጸልያለች። የመስቀል ደመራ በዓል በሌሎች የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች እንዲሁም በካናዳ ቶሮንቶ በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል።

ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ