1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት እና የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት መበተን

ቅዳሜ፣ ግንቦት 7 2013

በዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ቃለ መሐላ ፈፅመው ከጎርጎሮሳዊው 1986 ጀምሮ የያዙትን ሥልጣን ጠበቅ አድርገዋል። የ76 ዓመቱ ሙሴቬኒ አንዴ ከሁለት ጊዜ በላይ መወዳደር የሚከለክለውን ሌላ ጊዜ ከ75 አመት በላይ የሆነው ሰው ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችልም የሚለውን የሕገ መንግሥቱ ክፍሎች የአገራቸው ምክር ቤት እንዲያሻሽል አድርገዋል

https://p.dw.com/p/3tRhZ
Uganda Kampala | Erneute Amtseinführung | Yoweri Museveni
ምስል Lubega Emmanuel/DW

ትኩረት በአፍሪካ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት የቀድሞ ተቀናቃኞቻቸውን ለማካተት የአገሪቱን ምክር ቤት የበተኑት ልክ የዛሬ ሳምንት ነበር። የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ይፋ የሆነው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን አዲሱ ምክር ቤት የሚቋቋምበት ጊዜ ግን አልተገለጸም። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ አቴኒ ዌክ አቴኒ ለሬውተርስ "የጊዜ ጉዳይ ነው። [አዲሱ ምክር ቤት] በቅርቡ ይቋቋማል" ሲሉ ተናግረዋል።

የተበተነው የደቡብ ሱዳን ምክር ቤት በተፈረመው የሰላም ሥምምነት መሠረት የአባላቱ ቁጥር ከ400 ወደ 550 ከፍ ማለት አለበት። አባላቱም የሰላም ሥምምነቱን ከፈረሙ ሁሉም ፓርቲዎች የተውጣጡ መሆን ይገባቸዋል። ከምክር ቤቱ አባላት 332ቱ ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (SPLM) የሚወከሉ ናቸው። የአዲሱ ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ፓርቲዎች የሚጠቆሙ እንጂ የሚመረጡ አይሆንም።

ውሳኔው የዘገየም ቢሆን የለውጥ አራማጆች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ቡድኖች በቀና ተቀብለውታል። ትናንት በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ማድረግ የጀመሩት የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ዶናልድ ቡዝ የአገሪቱን የርስ በርስ ጦርነት ለማቆም የተፈረመው ሥምምነት ተግባራዊነት ዘገምተኛ መሆን አገራቸውን እንደሚያሳስባት ገልጸው ነበር።

በዩጋንዳ ደግሞ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በዚሁ ሳምንት ቃለ መሐላ ፈፅመው ከጎርጎሮሳዊው 1986 ጀምሮ የያዙትን ሥልጣን ጠበቅ አድርገዋል። ከሶስት አስርት አመታት በኋላም ሰውየው መንበረ ሥልጣኑን ለማስረከብ ፈቃደኛ አልሆኑም። ለዚህም የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እስከ ማሻሻል ደርሰዋል። የዛሬው የትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ