1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩጋንዳ አማጺ ቡድን መሪው ብይን፤ ቱርክ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጥር 29 2013

የቀድሞው የዩጋንዳ አማፅያን መሪ ዶሜኒክ ኦንግዌን በጦርና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ችሎት ፈጽሟቸዋል የተባሉ ወንጀሎች ተዘርዝረው ጥፋተኛ ተባለ።

https://p.dw.com/p/3ozM7
Niederlande Dominic Ongwen
ምስል picture alliance picture alliance/dpa/M. Kooren dpa/P. Dejong

ትኩረት በአፍሪቃ ጥር 29 ቀን 2013

የቀድሞው የዩጋንዳ አማፅያን መሪ ዶሜኒክ ኦንግዌን በጦርና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ። በዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ICC ጉዳዩ ሲታይ የቆየው በልጅነቱ ራሱ ታግቶ የጌታ ተከላካይ ጦር ለሚባለው አማፂ ቡድን በልጅ ወታደርነት ያደገው አንግዌን ከትናንት በስተያ ሐሙስ ዕለት ነው ከቀረቡበት 70 ክሶች በ60ው ጥፋተኛነቱ የተረጋገጠው። በአማፂ ቡድኑ የተፈፀሙት የጭካኔ ድርጊቶች በችሎቱ በንባብ በቀረቡበት ወቅት ዳኛው ቤርትራም ሽሚት አንግዌን ልጆችን ጨምሮ ሲቪሎች እንዲገደሉና እንዲታገቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ዘርዝረዋል።

«ዶሚኒክ ኦንግዌን ያለጥርጥር ከተዘረዘሩት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በፓጁላ፤ ኤዴክ፣ ሉኮዲና ፖክ በሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ላይ በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።  በሲቪሎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት፣ ግድያ፣ የግድያ ሙከራ፤ ማሰቃየት፣ ለባርነት መዳረግ፣ ሰብዓዊ ክብር ማዋረድ፣ ዝርፊያ፣ ንብረት ማውደምና መክሰስ፤ በሁለተኛ ደረጃ ከክሱ ዝርዝር ውስጥ ስማቸውና የተፈጸመባቸው በተጠቀሰ ተጠልፈው በቤቱ ታግተው በነበሩ ሰባት ሴቶች ላይ በርካታ ወሲባዊና ፆታዊ ጥቃቶችን ፈጽሟል።»

ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ዶሜኒክ አንግዌን ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር በእንግሊዝኛ ምህጻሩ LRA በሚለው አማፂ ቡድን የታገተው። ቡድኑ ከጎርጎሪዮሳዊው 2000 ዓ,ም ጀምሮ በተለይ ሰሜን ዩጋንዳ ውስጥ ሴቶችን በማገትና የወሲብ ባሪያ በማድረግ፤ ሕጻናትን ለውትድርና በመመልመልና በማሰቃየት፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው የሚገኙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶችን እንዲሁም ልጆችን በጭካኔ በመግደል ተከሷል። በችሎቱ ውሎ የዳኞቹ ፕሬዝደንት ቤርትራም ሽሚት፤ በጎርጎሪዮሳዊው 2004 ዓ,ም ቡድኑ ሉዲክ በተሰኘችው መንደር ጥቃት ሲፈጽም በዶሜኒክ አንጉዌን ትዕዛዝ ሲቪሎች በጥይት፤ በእሳት ቃጠሎና በድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን ዘርዝረዋል። ይህ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላም የቡድኑ መሪ ጆሴፍ ኮኒ ለአንጉዌን የኮማንደርነት ማዕረግ እንደሰጠው ነው የተነገረው። የዩጋንዳ መንግሥት የአማፂው ቡድን ተዋጊዎች ከጥቂት መቶዎች አይበልጡም ባይ ነው። ሆኖም የቡድኑ መሪ ጆሴፍ ኮኒ እስካሁን አልተያዘም። 

ተፈላጊው የLRA መሪ ጆሴፍ ኮኒ
ምስል AP

ተከሳሹ ዶሜኒክ አንግዌን በረዥሙ የተዘረዘረው ጥፋትና ክሱን ደንዝዞ ሲከታተል፤ በአንጻሩ ጠበቃው ተከሳሹ ጥፋተኛ የሚባል ሳይሆን ራሱ የአማፂው ቡድን ሰለባ ነበር የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ ሞክረዋል። ሆኖም ዳኛው ክሱ የቀረበው ዶሜኒክ አንግዌን ራሱ ነፍስ አውቆ የአማፂው ቡድን ኮማንደር በነበረበት ወቅት የፈጸመው መሆኑን በማስገንዘብ መከራከሪያውን ውድቅ አድርገዋል። ከዓመታት በፊት በቀረቡበት ክሶች ሁሉ ጥፋተኛ አይደለሁም ያለው ዶሜኒክ አንግዌ የዕድሜ ልክ እስራት ሊበየንበት እንደሚችል ተገምቷል።

ዩጋንዳ ውስጥ መንግሥት በመቃወም እንቅስቃሴ የጀመረው LRA ሕጻናትን እያገተ ለውትድርና አሰልጥኖ በማሰለፍም ይታወቃል። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የቡድኑ መሪዎች በሲቪሎች ላይ የጥቃት ርምጃ እንዲወሰድ ሲያስተላልፉ የነበረውን ትዕዛዝ ቅጂ በድምጽ አሰምቷል። በቡድኑ ታግተው በልጅ ወታደርነት ተሰማርተው ከነበሩ ብዙዎች አሁን ከዚያ ወጥተው ወደማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ጥረት እየተደረገ ነው። በለጋ ዕድሜያቸው በአማፂው ቡድን በወታደርነት ተመልምለው የስቃይ ሕይወት ይገፉ ከነበሩት አንዱ ከሞት መትረፉን ይናገራል።

«የዛሬ 18 ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር የታገትኩት፤ እዚያ ለአምስት ዓመታት ያህል ቆይቼ ፤ ወደ እዚህ  ተመለስኩ። የወሰዱኝ ከቤተሰቦቼ ጋር እያለሁ ነው። ከወሰዱን 22 ልጆች መካከል 19ኙ ሞቱ፤ እኔ ከተረፉት አንዱ ነኝ።»

ዩጋንዳውያን በመንደራቸው ሆነው የዶሜኒክ ኦንግዌን የፍርድ ውሳኔ ሲከታተሉ
ምስል Sumy Sadurini/AFP/Getty Images

መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የመብት ተሟጋች የሆነው ኢንቪዝብል ችልድረን የተሰኘው ቡድን፣ በጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓ,ም በጌታ ተከላካይ ጦር የተፈጸሙ ጥቃቶችን በቪዲዮ ለዓለም ይፋ አደረገ። የአማፂ ቡድኑን መሪ ጆሴፍ ኮኒን የማደኑ ርምጃም ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያዘ። በዚህ ሳምንትም ድርጅቱ በአማፂው ቡድን የታገቱ 108 ስምንት ልጆች እስካሁን እንዳልተገኙ አመልክቷል።

ዶሜኒክ ኦንግዌን ዩጋንዳ ውስጥ በጦር አበጋዝነት ሲሳተፍ የፈፀማቸው የጦርና በሰብዓዊነት ላይ የተደረጉ ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ሲዘረዘር በሉኮዲ መንደር የድርጊቱ ሰለባዎች ሂደቱን በአንዲት አነስተኛ ራዲዮ አጠገብ ተሰባስበው ተከታትለዋል።

LRA የሰሜን ዩጋንዳ ነዋሪዎችንና የአጎራባች ሃገራት መንደሮችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲያሸብር ኖሯል። ቡድኑ በሰሜን ዩጋንዳ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ እንዲሁም በዴሞክራቲክ ኮንጎ በሲቪሎች ላይ ለፈፀመው አሰቃቂ ጥቃት እስካሁን ቢያንስ ከቡድኑ መሪዎች አንዱ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቧል። በዓለም አቀፍ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ ፍትህ መርሃግብር ተባባሪ ዳይሬክተር ኤሲዜ ኩፕለር ይህን እንደ አንድ ስኬት ነው የቆጠሩት። የትኛውም የመብት ጥሰት ዓመታት ቢያስቆጥርም ጥፋተኞች በፍትህ ፊት መቆማቸው እንደማይቀር ማሳያ ነውም ብለውታል።

ቱርክ በአፍሪቃ 

ባለፉት 15 ዓመታት ቱርክ ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ያላትን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ትስስር እያጠናከረች መጥታለች። በተለይም ባለፉት አስር ዓመታት የቱርክ የውጭ ፖሊሲ በአፍሪቃ ውስጥ ያላት ተሳትፎ በአራት እጅ እንዲያድግ ሠርቷል። ከሰሃራ በስተደቡብ በተለይም በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ተሳትፎዋ ጎልቶ እየታየ ነው። በቅርቡም ቱርክ ራሷን «ኢሮ እስያ» ማለቱን ትታ «አፍሮ አውሮ እስያ» በማለት መግለጽ ጀምራለች። አንካራ ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ባላት ትስስር በንግድ፣ በወታደራዊ ትብብር፤ በትምህርት፣ በዲፕሎማሲ፣ በመሠረተ ልማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብና በፖለቲካ ግንኙነቱ ላይ ሁሉ ተፅዕኖዋን እያሳደገች ነው። ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት ጋር ቱርክ የምታካሂደው ንግድ ከአንድ ቢሊየን ዶላር ተነስቶ ወደ 7,6 ቢሊየን ደርሷል። በአፍሪቃ የአንካራ ትልቁ  የጦር ሰፈር የሚገኘው ሶማሊያ ነው። የሶማሊያ ወታደሮችንም ታሰለጥናለች። የቱርክ የትብብርና ግንኙነት ተቋም እንደሚለው በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ከቱርክ የጋራ ትብብር ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል ከሚባሉት ሃገራት ሶማሊያ ሁለተኛ ናት። ሱዳን፣ ኒዠር፤ ጅቡቲ፣ ቻድና ጊኒም የዚሁ ተጠቃሚዎች ናቸው። በቶጎ እና በጊኒ ቢሳው ደግሞ አዳዲስ ኤምባሲዎችን ለመክፈት አልማለች።

የቱርክ ባለሥልጣናት በሶማሊያ የወታደሮች ማሰልጠኛን ሲጎበኙ
ምስል picture alliance/AP Photo/F. Abdi Warsame

 ፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን ወደ ሥልጣን ከመጡበት ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ቱርክ በዓለም ደረጃ ያላትን ሚናና ተፅዕኖ ለማጉላት በግልፅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አልፋ ተርፋም አንካራ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ባለፈ ወደሌሎች ዘልቃ እየታየች ነው። በላፍበራ ዩኒቨርሲቲ የቱርክ የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አሊ ቢልጊክ የቱርክን ተፅዕኖ መቀበል ግድ ነው ባይ ናቸው።

«ቱርክ አዲሷ ተዋናይ መሆኗን መቀበል ግድ ነው። አፍሪቃ ውስጥ 1o ዓመት ማለት ምንም ማለት አይደለም። ሌሎቹን ትላልቅ ሃገራት ማለትም ሩሲያ፣ ቻይናም ሆነች ምዕራብ ሃገራትን ብንመለከት አፍሪቃ ውስጥ ከገቡ ከርመዋል።»

በጂኖዋ ዩኒቨርሲቲ በቱርክ የአፍሪቃ ፖሊሲ አዋቂ ፌዴሪኮ ዶኔሊ ለዚሁ አፅንኦት ይሰጣሉ። እሳቸው እንደሚሉት በጎርጎሪዮሳዊው 2004 እና 2005 ዓ,ም የኤርዶኻን ገዢ ፓርቲ በዓለም አቀፉ አውድ የአዲሲቱን ቱርክ ሚና አጉልቶ ለማውጣት ሠርቷል። ፓርቲው እያደገች ያለች ቱርክን በመላው ዓለም ለማሳየት ነበር ፍላጎቱ። በተለይም በተመድ 15 ቋሚ አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት የተገፉ ሃገራትን ካላካተተ ጎዶሎ ነው የሚል አቋሟን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ማካተቷም እንደዋና ጉዳይ ተወስዷል። ቱርክ ለተገፉት ድምፅ ነኝ ለማለት መሞከሯ ሌላው ገፅታዋን የገነባ ነው ብለው ያምናሉ በደቡብ አፍሪቃ የቱርክ አምባሳደር ኤሊፍ ኮሞጉሉ ዑልጋን።

«በዚህ አህጉሩ የቅኝ ግዛት ድምፀት አሁንም በጣም ሕያው ነው። የቅኝ ግዛት የኋላ ታሪክ አሁንም የአፍሪቃን ሕዝቦች እየተከተለ ነው። ቱርክ ደግሞ ምንም አይነት የቅኝ ገዢነት መገለጫ የላትም። ይህም እዚህ በቀላሉ የተሻለ ስፍራ እንዲኖራት ያደርጋል።»

ምንም እንኳን የኦቶማን ቱርክ ሥርዓት ከአፍሪቃ ጋር በርካታ ግንኙነቶች ቢኖሩትም ያ ከቅን ግዛት ይዞታ ጋር አይገናኝ ባይ ናቸው ሌላኛው ምሁር ዶክተር ፌዴሪኮ ዶኔሊ። በዚህም አንካራ ራሷን በአንድ ወቅት የቅኝ ገዢዎች ከነበሩት የአውሮጳ ኃይሎች በተሻለ በአፍሪቃ ውስጥ ለወንድማዊ ትብብር አማራጭ አድርጋ ማቅረብ ተሳክቶላታል ብለው ያምናሉ።

የቱርክ ፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን
ምስል Reuters

በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም የቱርክ ፕሬዝደንት ኤርዶኻን በ20 ዓመታት ውስጥ የጎበኙ ብቸኛው አፍሪቃዊ ያልሆኑ የሀገር መሪ ናቸው። በወቅቱ አብረዋቸው የተጓዙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የአሁኑ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አህማት ዳቦቱጉሉ ወደሶማሊያ የሄዱት ለሀገሪቱ ህዝቦችና ያላቸውን ወንድማዊ ዝምድና ለማሳየት መሆኑን ሲገልፁ፤ ግንኙነቱ በአንድ ጊዜ ብቻ የሚገታ እንዳልሆነ መናገራቸው ይታወሳል። የቱርክ የዜና ወኪል እንደሚለው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሀገሪቱ ሶማሊያ ውስጥ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ገንዘብ ለርዳታ እና ለመሠረተ ልማት አፍስሳለች። መቃዲሾ ላይ የገነባችው ኤምባሲም በትልቅነቱ ግንባር ቀደም መሆኑ ይነገራል።

ምንም እንኳን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ቱርክ በአፍሪቃ ያላትን ተቀባይነት እያጠናከረች መጥታለች ቢባልም ዶክተር ፌዴሪኮ ዶኔሊ ግን ብዙም መጋገነን የለበትም ነው የሚሉት። 

«እንደሚመስለኝ ከችሎታ ጋር በተገናኘ የቱርክን እውነተኛ አቅም ከሚገባው በላይ አድርገን መውድ የለብንም። ምንም እንኳን አንዳንድ የቱርክ ፖሊሲ አውጪዎችና ትረካቸው ቱርክን በአፍሪቃ አህጉር የቻይና ወይም የፈረንሳይ ተፎካካሪ ኃይል አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም፤ እኔ አይመስለኝም።»

የእሳቸውን ሃሳብ የላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ዑልፍ ኤንግልም ይጋሩታል። እሳቸው እንደሚሉትም የቱርክ ምድብ ከነአረብ ኤሜሬት፣ ቀጠር፤ ሳውድ አረቢያ ወይም ኢራን ተርታ ነው። የእነዚህ ሃገራት አቅም በተወሰኑ አካባቢዎች የተገደበ ነውም ባይ ናቸው።

እንዲያም ሆኖ  የቱርክ የአፍሪቃ ፖሊሲ ጥልቅ መሠረት ያለው ይመስላል። የፖለቲካ ተንታኞቹ አንካራ አፍሪቃ ውስጥ አዎንታዊ ገጽታ መገንባቷን አፅንኦት ይሰጡታል። በዶክተር አሊ ቤልጂክ እምነትም ቱርክ አሁን አፍሪቃ ውስጥ የምታሳየው ባህሪ ለጊዜው የሚሠራ ይመስላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ልደት አበበ