1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2015

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ምሽቱን አዲስ አበባ ገብተዋል። ብሊንከን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ተሰምቷል።

https://p.dw.com/p/4Oiqo
Äthiopien | Permierminister Abiy Ahmed und Anthony Blinken
ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C

«ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል»

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ምሽቱን አዲስ አበባ መግባታቸውን ተሰምቷል። ከሁለት ዓመታት በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የአሜሪካው ከፍተኛ ባለሥልጣን ያደረጉት የአሁኑ ጉብኝት በአዲስ አበባ እና ዋሽንግተን መካከል ሻክሮ የከረመውን ግንኙነት ለማለዘብ ሊረዳ እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካን መንግሥትም ሆነ ከሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት ያገኝ የነበረውን የኤኮኖሚም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን ዳግም ለመመለስ ጥረት የሚያደርግበት አጋጣሚ ይመስላል። ሆኖም ግን ይኽ እውን እንዳይሆን በጦርነቱ ወቅት በሁለቱም ኃይሎች የተፈጸመውን መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተመ የታቀደውን ምርመራ አለመቀበሉ ስጋት እንደሆነ ተጠቅሷል። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሃገራት ተባብረው በሚሰሩባቸው በሁለትዮሽ ጉዳዮች እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳይ አንስተው መነጋገራቸው ተገልጿል። ቀደም ብለው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመቀጠልም  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም ናይሮቢ ኬንያ ላይ የሰላም ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ እየተደረጉ ስላሉ ክንውኖችና ሂደቱ ያለበትን የተመለከተ ገለጻና እና ውይይት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መግለጻቸው ተሰምቷል። በመልሶ ማቋቋም እና በመሰል ተያያዥ ሥራዎች በሚከደረጉ ክንውኖች ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ድጋፍ እንደምትፈልግም ተመላክቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሰብአዊ እርዳታ የሚሆን በግጭት፣ በድርቅ እና በምግብ አቅርቦት ስጋት ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች አዲስ የ331 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

Äthiopien | Permierminister Abiy Ahmed und Anthony Blinken
አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያይተዋልምስል Fana Broadcasting Corporate S.C

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ