1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ተቃውሞ

ሰኞ፣ ግንቦት 16 2013

ማዕቀቡ የሁለቱን ሃገራት የረዥም ዘመን ጠቃሚ ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳና በጣም አሳዛኝም ነው ብሏል። አሜሪካን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ ግልጽ ማድረጉን የጠቀሰው መግለጫው፣ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን እንዴት እንደምትመራና እንደምታስተዳድር ሊነገራት አይገባም ሲልም አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/3tt03
Äthiopien Logo des Außenministeriums

ኢትዮጵያ ዩናይትድ ስቴትስ፣ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችውን የመግቢያ ፈቃድ ቪዛና የኤኮኖሚ ድጋፍ እርዳታ እገዳን በጥብቅ ነቀፈች። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቷ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሲል ተቃውሟል። ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ላላት ታሪካዊና በወዳጅነት ላይ ለተመሰረተ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ  መግለጫው ጠቅሶ ማዕቀቡ የሁለቱን ሃገራት የረዥም ዘመን ጠቃሚ ግንኙነት በእጅጉ የሚጎዳና በጣም አሳዛኝም ነው ብሏል። አሜሪካን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ ግልጽ ማድረጉን የጠቀሰው መግለጫው፣ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን እንዴት እንደምትመራና እንደምታስተዳድር ሊነገራት አይገባም ሲልም አሳስቧል። አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ ከውጭ በመጣ ግፊት ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ትክክለኛው መንገድ ነው ብሎ ስለሚያምን በዚህ ላይ እየሠራ መሆኑንም መግለጫ ዘርዝሯል። መግለጫው አክሎም «በጣም አሳዛኙ ነገር ከሁለት ሳምንት በፊት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ከህወሓት ጋር መንግሥት እኩል ተቀምጦ እንዲደራደር ለማስገደድ መሞከር መሆኑን» በማመልከትም፤ «ይኽም የአስተዳደሩን አሳሳች አቀራረብ እንደሚያስረዳም» ገልጿል። ድርጊቱንም አሸባሪ የተባለው ቡድን እንዲያንሰራራ የማድረግ «አፍራሽና ተግባራዊ መሆን የማይችል ሙከራ ነው» ሲልም አጣጥሏል። በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተጠያቂ ለማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል። በዚህ የዩናይትድ ስቴትስ አሳዛኝ ውሳኔም የኢትዮጵያ መንግሥት አይደናቀፍም ያለው መግለጫው መንግሥት ወቅታዊዎቹን ተግዳሮቶች ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረቱን እንደሚቀጥልና ሃገሪቱንም ወደ ዘላቂ ሰላምን ብልጽግና ጎዳና እንደሚያመራ አስታውቋል። ዩናይትድ ስቴትስ በትግራይ ክልል ለ6 ወራት የተካሄደውን ውጊያ በማባባስ ተጠያቂ ባለቻቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሏን ያሳወቀችው  የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ባወጡት መግለጫ ነው።ብሊንከን ፣የጉዞ እገዳው የአሁን ወይም የቀድሞ የኢትዮጵያ ወይም የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የአማራ ክልልና መደበኛ ያልሆኑ ኃይላትን እንዲሁም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ «ሕወሓት» የፀጥታ ኅይል አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችን እንደሚያካትት ገልጸዋል። ይሁንና መግለጫው ማዕቀቡ የሚመለከታቸው የሁለቱም ሃገራት ባለሥልጣናት እነማን እንደሆኑ አላሳወቀም። «ትግራይ የሚገኙ ሰዎች አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በደሎችና ጥቃቶች ይፈጸሙባቸዋል፤ በአስቸኳይ ሊደርሳቸው የሚገባ ሰብዓዊ እርዳታም በኢትዮጵያና በኤርትራ ወታደሮች እየታገደባቸው ነው» ሲሉም ብሊንከን አስታውቀዋል። ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢደረጉም በውጊያው የሚካፈሉ ወገኖች የትግራዩን ግጭት ለማስቆምም ሆነ ለፖለቲካዊ ቀውሱ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ምንም ዓይነት ትርጉም ያለው እርምጃ አልወሰዱም ሲሉም ወቅሰዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የኤኮኖሚና የፀጥታ ድጋፎች ላይ መጠነ ሰፊ ገደብ መጣሏንም አስታውቀው ሆኖም በጤና በምግብ እና በትምሕርት ዘርፍ የምትሰጣቸው ሰብዓዊ እርዳታዎች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ