1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካናት በኢትዮጵያ እና ሱዳን

ቅዳሜ፣ ጥር 14 2014

የዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የአፍሪቃ ቀንድ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሞሊ ፊ በዚሁ ሳምንት ጎረቤት ሱዳን እና ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ልዑካናቱ የአፍሪቃ ቀንድ ጉብኝታቸው በሁለቱም ሃገራት ለበርካታ ወራት የዘለቀውን ግጭት እና ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ ያለመ እንደኾነ ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/45vht
Sudan Khartum | Protest gegen die Machtübernahme durch das Militär
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ልዑካኑ የዩናይትድ ስቴትስ ፍላጎትን ያሳኩ ይሆን?

የዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የአፍሪቃ ቀንድ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሞሊ ፊ በዚሁ ሳምንት ጎረቤት ሱዳን እና ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ልዑካናቱ የአፍሪቃ ቀንድ ጉብኝታቸው በሁለቱም ሃገራት ለበርካታ ወራት የዘለቀውን ግጭት እና ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ ያለመ እንደኾነ ተዘግቧል።

ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ አዲስ መልእክተኛዋ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሞሊ ፊን ወደ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የላከችው በዚሁ ሳምንት ነው። አዲሱ ልዑክ በሱዳን ቆይታቸው በሀገሪቱ ተቃውሞ ወቅት የተገደሉ ሰዎች ፍትኅ እንዲያገኙ ምርመራም እንዲደረግ ረቡዕ ዕለት የሱዳንን መንግሥት አሳስበዋል። በተቃውሞ ወቅት ከተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ጋርም ልዑካናት መነጋገራቸው ተዘግቧል።

ሱዳን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ልታገኘው የነበረውን የ650 ሚሊዮን ድጋፍ  በመፈንቅለ መንግሥቱ የተነሳ ታኅሣስ ወር ላይ እንዲቋረጥባት ተደርጓል። ይኸን ርዳታ ሱዳን ልታገኝ የምትችለው በሀገሪቱ የተከሰተው ቀውስ ረግቦ በሲቪል የሚመራው መንግሥት ዳግም ሥልጣኑን የሚይዝ ከኾነ ብቻ እንደኾነ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑኩ እና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ አሳስበዋል። ሱዳን ውስጥ ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ከሲቪል ጥምር መንግሥቱ ነጥቆ ሙሉ ለሙሉ በመፈንቅለ መንግሥት ከተቆቆጣጠረበት ያለፈው ዓመት ታኅሣሥ 16 ቀን አንስቶ ቢያንስ 72 ሰዎች በፀጥታ ኃይላት መገደላቸው ተገልጧል። ከ2,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደቆሰሉ የሕክምና ምንጮች ይጠቁማሉ።

Sudan Khartum | Protest gegen die Machtübernahme durch das Militär
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ረዳት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሞሊ ፊን ሱዳንን ረቡዕ ጎብኝተው ሐሙስ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ እንዳቀኑ ተገልጧል። ይህንኑ በመለከተ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር  ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ቀጣዩን በአጭሩ ተናግረዋል።

አዲሱ የአሜሪካ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናታቸው በፊት የቀድሞው ልዑክ ጄፍሬ ፌልትማን በልዑክነታቸው ዘመን የመጨረሻ የሆነውን ጉዞ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አድርገው ነበር። በወቅቱ ታዲያ በርካቶችን እጅግ ያስደመመ፤ ምናልባትም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ይዛው ከነበረው አቋሟ ያልተጠበቀ ነገር መከሰቱን ብዙዎች ይጠረጥራሉ። ጥርጣሬውን ለማጽዳት ግን መንግሥት ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ለኅብረተሰቡ አላደረሰም። ጥርጣሬውን ካጎሉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንደኛው  የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጄፍሬ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ ማስታወቁ ነበር።

በተጨማሪም የቀድሞው ልዑክ ኢትዮጵያ ይገባሉ በተባለበት ቀን በርካቶች ባልጠበቁት መንገድ የሕወሓት የቀድሞ አመራርን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው ጥያቄ አጭሯል። ከሕወሓት ጋር ድርድር የለም፤ ምዕራባውያንም እጃችን ሊጠመዝዙ ይሻሉ እኛም አንበገርም ሲል የነበረው መንግሥት ሕዝቡ ምኑንም ሳያውቅ በድንገት እስረኞቹን መፍታቱ ቁጣም፤ ንዴትም፣ ግርታም፣ ፈጥሯል። በእርግጥ በጉዳዩ የተደሰቱም አልጠፉም። በወቅቱ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩ እሳቸውንም እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል።

ስለዚህ ጉዳይ ጥርት ያለ መረጃ በወቅቱ ለኅብረተሰቡ ባለመስጠቱም ቀድሞ ሲፎክር የነበረው መንግሥት ለዩናይትድ ስቴትስ እጁን ሰጥቷል፤ በድብቅም እጁ ተዘምዝዟል ሲሉ በርካቶች ተደምጠዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ መነሻቸው በዝርዝር ዐይታወቅም። የዓለም አቀፍ ድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዱጃሪክ ረቡዕ ዕለት ቀጣዩን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

COP26 in Glasgow
ምስል Yves Herman/Pool/REUTERS

«ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ ውስጥ እና በቀጠናው በርካቶች ላይ ተጽእኖ ካሳረፈው ከአንድ ዓመቱ የጦር መሣሪያ ግጭት በኋላ  ሰላም ለማውረድ የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመስማታቸው  መደሰታቸውን ተናግረዋል። ሁሉም አካላት ሠላም ለማስፈን ትክክለኛ ወደ ሆነው መንገድ በማምራት በፍጥነት ከባላንጣነት እንዲቆጠቡ በድጋሚ ጥሪ አስተላልፈዋል። የሰብአዊ ርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት  በግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች እንዲደግፉ እና እንዲያመቻቹም በድጋሚ ጥሪ አስተላልፈዋል።»

አንቶኒዮ ጉተሬሽ ይህን ያሉት ከአፍሪቃ ኅብረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የመጨረሻው የአዲስ አበባና የመቀሌ ጉብኝት በኋላ ከኦባሳንጆ ጋር በስልክ ካካሄዱት ንግግር ተከትሎ መሆኑን  አሶስየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።   ይሁንና ግን ኦባሳንጆ ኢትዮጵያን የጎበኙበትን ትክክለኛውን ቀን የዜና ወኪሉ አልጠቀሰም። ጉተሬሽ አክለው እንደተናገሩት ከኾነ፦ «ለኢትዮጵያው ግጭት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ አሁን ተጨባጭ እድል እንዳለ» ኦባሳንጆ አዎንታዊ አስተያየት ሰጥተዋቸዋል። ሆኖም ጉተሬሽ በመግለጫቸው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ አደረጉ የተባለውን ጥረት አልገለጹም።

Libanon - US David Satterfield mit Libanesischem Außenminister Bassil
ምስል picture alliance/AP Photo/B. Hussein

የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ለማስቆም እና ሰላማዊ መፍትኄ ለመሻት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጀመረው ጥረት መጨረሻው ምን እንደሚሆን የሚታወቅ ነገር የለም። አዲሱ ልዑክ የቀድሞው ልዑክ ፌልትማን ያላሳኩንትን የዩናይትድ ስቴትስ ፍላጎት ያሳኩ ይሆን? ሁሉንም በቅርቡ አብረን የምናየው ይሆናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ