1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩሮ-ኤሺያ ጦርነት፣የተሳካረዉ መርሕ

ሰኞ፣ መጋቢት 19 2014

ባይደን አዉሮጳ ላይ «የዘባረቁትን» ለማስተባበል ሹማምቶቸዉ ከዋሽግተን ሸብ-ረብ ማለታቸዉ አልቀረም።ጥፋቱን መጠገን ግን የቻሉ አይመስልም።የሞስኮዎች ቁጣ ከመንተክተኩ በፊት የፓሪሶች ትችት ቀደመ።ብራስልስ ላይ የተረጋገጠዉ ፅኑ አንድነት ስንጥቅ-ጭረት እንዳማያጣዉ ተረጋገጠም።

https://p.dw.com/p/498yP
Ukraine-Konflikt | US-Präsident Joe Biden zu Besuch in Polen
ምስል Aleksandra Szmigiel/REUTERS

የዩክሬን ጦርነት፣ የባይደን ቃላትና የምዕራባዉያን መርሕ

ከሰፊ፣ ኃያል ሐብታሚቱ ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስከ ትንሺቱ አዉሮጳዊት ሞንቴኔግሮ ያሉ የ30 የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል መንግስታት ገንዘብ፣ ጦር መሳሪያ፣ ምግባቸዉን ለዩክሬን ይዘረግፋሉ።ለዩክሬን ድጋፋቸዉን፣ለአዉሮጶች አለኝታነቸዉን ያረጋገጡት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግን ከርዳታ፣ድጋፍ ዛቻ-ፉከራ ወደ ስድብ ወርደዋል።የሩሲያ አቻቸዉን ቭላድሚር ፑቲንን «አራጅ» አሏቸዉ-ቅዳሜ።ሩሲያን ለማንበርከክ የተከፈተዉን ዘመቻ ደግሞ «ለዲሞክራሲ የሚደረግ ጦርነት።» ለዲሞክራሲ የሚዋጉት፣ ምዕራባዉያን መንግሥታት ከአምባገነኑ የፑቲኗ ሩሲያ ጋስና ነዳጅ መግዛታቸዉን ትተዉ የቀጠርንና የአረብ ኤሚሬቶችን ለመግዛት እየተሻሙ ነዉ።የዶሐ-አቡዳቢ ነገስታት «ዴምክራት» መሆናቸዉ ይሆን?ከአሜሪካኖች M-17 ሔሊኮብተር እስከ ሩሜንያ ዉኃ የሚጎርፍለት የዩክሬን ጦር የሩሲያ ጠላቶቹን መመከቱን ፕሬዝደንት ቮሎድምየር ዘሌንስኪ ሰዓት በሰዓት ይለፍፋሉ።ፑቲን ያጠቃሉ።ዩክሬን ትወድማለች። ወር-ከ4 ቀን።የዩክሬን ጦርነት፣ የሰሞኑ ዕዉነትና አሳካሪዉ መርሕ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

                                  

የኢራቅና የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች የመጀመሪያዉን የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ጦርነት ከመግጠማቸዉ በፊት የኢራቁ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ታሪቅ አዚዝና የዩናትድ ስቴትሱ አቻቸዉ ጀምስ ቤከር ተነጋግረዉ ነበር።አዚዝ ጥር 9  1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጄኔቭ ላይ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከባግዳድ ሲነሱ ጋዜጠኞች «ተዘጋጅተዋል» ብለዉ ጠየቋቸዉ።

Ukraine - Bilder zur aktuellen Situation
ምስል Agencja Wyborcza.pl via REUTERS

እዉቁ የኢራቅ ዲፕሎማት «አሳምሬ፣ ከማንጋር እንደምነጋገር አዉቃለሁ።የምነጋገረዉ እኮ ከአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጋር ነዉ» ብለዉ የአንድ አፍሪቃዊት ሐገርን ስም ጠቅሰዉ ከ---ጋር «አይደለም» ወር ከደፈነዉ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መሐል ጭል፣ጭል ከሚለዉ በጎ ተስፋ አንዱ የሁለቱ ሐገራት ተወካዮች ነገ ኢስታንቡል-ቱርክ ዉስጥ ያደርጉታል የተባለዉ ድርድር ነዉ።ለድርድሩ ማን ምን ያሕል እንደተዘጋጀ አናዉቅም።ፕሬዝደንት ቮልዶምየር ዘለንስኪ ግን አንድም በልምድ እጥረት፣ ሁለቱም በየዋሕነት፣ ሶስትም በዋሽግተን፣ ለንደን፣ብራስልሶች ሆይ ሆይታ ተጋርደዉ የገጠሙትን ጠላት አቅምና ማንነት በቅጡ ያወቁት አይመስልም።

ከዓለም ከፍተኛዉን የኑክሌር ቦምብ የታጠቁት ሞስኮዎች አዉሮጳ-አሜሪካንን ለማጋየት እየተጋበዙ የኪየቩ መሪ «ቢያዉቁን ኖሩ» እያሉ እራሳቸዉ አለማወቃቸዉን አጋለጡ።

«ሰላሳ ቀናት።ወር ደፈነ።ሩሲያዎች የሚጠብቃቸዉን አዉቀዉ ቢሆን ኖሮ እርግጠኛ ነኝ እዚሕ ለመምጣት ይፈሩ ነበር።በዚሕ አንድ ወር ዋናዎቹን የሩሲያ ጥቃቶች ተቋቁመናል።ዓለምም አጥፊ ማዕቀብ ጥሏል።ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል እየተደራደርን ነዉ።»

ማዕቀቡ በርግጥ እየተጠናከረ እንደቀጠለ ነዉ።ሩሲያንም ክፉኛ እየጎዳ ነዉ።ሩሲያን ለመጉዳት ያለመዉ ማዕቀብ ግን የአዉሮጳ የፉርኖ ዱቄት፣የምግብ ዘይት መሸጫ መደብር-መደርደሪያዎችን ኦና አስቀርቷል።የነዳጅ ዘይትና የጋስ ዋጋን አንሮ መንግስታት ለክፉ ቀን የተቀመጡ ሸቀጦችን እንዲያወጡ፣ ለየኩባንዮችና ሕዝባቸዉም ድጎማ እንዲከፍሉ እያስገደደ ነዉ።

የፕሬዝደት ዘለንስኪ «ዓለም» ያሉት ደጋፊያቸዉ አፍሪቃን የሚጨምሮ ከሆነ፣ መግለጫዉን የሰጡ ዕለት  የቡርኪናፋሶ ዜጎች ባደባባይ ሰልፍ ምዕራባዉያንን ሲያወግዙ፣ ሩሲያን ሲያሞግሱ መዋላቸዉን አላወቁም።ሰልፉን ከጠሩት አንዱ 72 ማሕበራትን የሚያስተናብረዉ ድርጅት ነበር።ምክትል ዋና ፀሐፊ ኦስማኔ ኦዲራኦጎ

  «(ግንኙነታችንን) ማስፋት አለብን።ብዙ ሐገራትን መርጠናል።ይሁንና ሩሲያን ከግንዛቤ ልናስገባት ይገባል።የሶሪያ አሸባሪዎችን ያስወገደችዉ፣ ቬኑዙዌላ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና ጎረቤታችን ማሊ ዉስጥም ብዙ ጥሩ ነገሮች ያደረገችዉ ሩሲያ ናት።»

ዘለንስኪ ጦርነቱ ወር መድፈኑን ባለፈዉ ቅዳሜ ከኪየቭ ሲናገሩ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዎርሶ ላይ የዘለንስኪን ዲሞክራሲያዊነት፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን መያዛቸዉን ያወድሱ፣ ሩሲያን በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ያወግዙ ነበር።

«ዛሬ ሩሲያ ዴሞክራሲን ደፍልቃለች።ሌላ ስፍራም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰደች ነዉ።በሐገሯ ብቻ ሳይሆን ለጎሳ የሚደረግ ትብብር በሚል የሐሰት ምክንያት ጎረቤትዋ ላይ አረጋግጣለች።ፑቲን ዩክሬንን ከናዚዎች ለማፅደት ብለዉ ሲናገሩ አያፍሩም።ዉሸት ነዉ።ወንጀል ነዉ።ይሕን ራሳቸዉም ያዉቁታል።»

 

ፕሬዝደንት ባይደን አዉሮጳን የጎበኙት መስተዳድራቸዉ ለዩክሬን መንግስት ጠንካራ ድጋፍ እንደሚሰጥ ለማረጋገጥ፤ምዕራባዉያን በሩሲያ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ለማጠናከር፣ ኃያል ሐብታሚቱ ሐገራቸዉ ለአዉሮጶች የምትሰጠዉ ድጋፍና ከአዉሮጶች ጋር ያላት ወዳጅነት እንደማይናወጥ ለማረጋገጥ ነዉ።

Ukraine | Präsident Wolodymyr Selenskyj
ምስል Ukrainian Presidential Press Office/AP/dpa/picture alliance

ባይደንን ጨምሮ ብራስልስና ዎርሶ ላይ በተደረጉ ተከታታይ ጉባኤዎች ላይ የተሳተፉት የኔቶ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የቡድን 7 አባል ሐገራት መሪዎችም ይሕን አረጋግጠዋል።ይሁንና ባይደን ዎርሶ ላይ ፕሬዝደንት ፑቲን ስልጣን ላይ መቆየት የለባቸዉም ማለታቸዉ ብዙ የተወራለትን የምዕራባዉያን አንድነትን አጠያያቂ አድርጎታል።«ይሕ ሰዉዬ ሰልጣን ላይ ሊቆይ አይችልም።»

የሰባ ዘጠኝ ዓመቱ አዛዉንት ስድብ ይቀናቸዋል።አምና መጋቢት ፑቲንን «ገዳይ» ብለዋቸዉ ነበር።ከባይደን በ10 ዓመት የሚያንሱት የክሬምሊኑ መሪ የያኔ አፀፋ «ለባይደን መልካም ጤና እመኝላቸዋለሁ።» አሉ ኢራቅ፣ አፍቃኒስታን፣ሊቢያ የፈሰሰና የሚፈሰዉን ደም ጠቃቅሰዉ ደግሞ «ሌላዉን የሚሳደብ-ራሱን የሰደበ ነዉ» የሚል  ምፀት አከሉበት።

ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ደንብ ጥሰዉ፣የፖለቲከኞችን ምክር፣ የሕዝባቸዉን ተቃዉሞ ረግጠዉ በ2003 ኢራቅን ኢንዲወርሩ ድምፅ ከሰጡ የአሜሪካ ሴናተሮች አንዱ ባይደን ነበሩ። በስተርጅና ዓለምን በጣምን ምዕራቡን የማስተባበሩን ኃላፊነት የያዙት አዛዉንት ፖለቲከኛ ዘንድሮም አላማረባቸዉም-አላረማቸዉምም።ፑቲኒን «አራጅ» አሏቸዉ-ቅዳሜ።

የቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንትና ዋና ተቀናቃኛቸዉ ዶናልድ ትራም «እንቅልፋሙ» ያሏቸዉ ባይደን አዉሮጳ ላይ «የዘባረቁትን» ለማስተባበል ሹማምቶቸዉ ከዋሽግተን ሸብ-ረብ ማለታቸዉ አልቀረም።ጥፋቱን መጠገን ግን የቻሉ አይመስልም።የሞስኮዎች ቁጣ ከመንተክተኩ በፊት የፓሪሶች ትችት ቀደመ።ብራስልስ ላይ የተረጋገጠዉ ፅኑ አንድነት ስንጥቅ-ጭረት እንዳማያጣዉ ተረጋገጠም።ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ-ትናንት።

                                   

«መጀመሪያ ተጨባጭ ነገር ሊኖር ይገባል።ከዚያ ቀጥሎ ሁኔታዉ ከቁጥጥር ዉጪ እንዳይወጣ መከላከል የሚቻለዉን ሁሉ ማድረግ ይገባል።እንደዚያ ዓይነት ቋንቋ አልጠቀምም ነበር። ምክንያቱም አሁንም ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር እየተነጋገርኩ ነዉ፣ በጋራ ማድረግ የምንፈልገዉስ ምድነዉ ነዉ? የምንፈልገዉ ሩሲያ ዩክሬን ዉስጥ የጀመረችዉ ጦርነት፣ ሌላ ጦርነት ሳያስከትልና ሳይባባስ ማስቆም ነዉ።ዓላማችን ይሕ ነዉ።»

Ukraine Krieg Mariupol Evakuierung
ምስል AA/picture alliance

የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስም ለስለስ ባሉ ዲፕሎማሲያዊ ቃላት የማክሮን ተቃዉሞ ደግመዉታል።ሾልስ ትናንት እንዳሉት ኔቶም ሆነ ባይደን ሩሲያ ዉስጥ የስርዓት ለዉጥ ለማድረግ አይፈልጉም።«የስርዓት ለዉጥ ዓላማችንም፣ መርሐችንም እንዳልሆነ ተስማምተናል።» ባይደን «ስሕተት ሰርተዉ ይሆን» ተብለዉ ሲጠየቁም የጀርመኑ መሪ «ያለዉን ብሏል» ብለዉ ዓለፉት።

ዩክሬን ግን ለምዕራብ-ምስራቆች ፍትጊያ ጫዳ ሆናለች።ዉብ ከተሞችዋ፣ ኢንዱስትሪዎቿ፣ ታሪካዊ ስፍራዎችዋ ከስለዋል።የሐገሪቱ የማሕበረሰብና የግዛት ልማት ሚንስቴር ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳስታወቀዉ 4 ሺሕ 500 መኖሪያ ቤቶች፣ 100 መደብሮች፣400 የትምሕርት ተቋማት፣ 150 ሐኪም ቤቶች፣ ወድመዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ እንዳስታወቀዉ እስከ ትናንት ድረስ ከ1 ሺሕ 1 መቶ በላይ ሰላማዊ የዩክሬን ዜጎች ተገድለዋል።የወታደሩ፣ የሚሊሻዉ፣የወድዶ ዘማቹ ሟች ቁጥር ከ4 ሺሕ እስከ 5 ሺሕ ይገመታል።ከ10 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አንድም ተሰድዷል ወይም ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።

ፕሬዝደንት ባይደን ዴሞክራሲን ለመታደግ ከሩሲያ ጋር የሚደረግ ያሉት ጦርነት ዛሬም የሚቆምበት ብልሐት አይደለም ተስፋዉም አይታወቅም።ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያ ላይ እስካሁን ከጣሉት ማዕቀብ በተጨማሪ ከሩሲያ  ጋስና ነዳጅ ዘይት መግዛታቸዉን ጨርሶ ለማቆም የመካከለኛዉ ምስራቅ በጣሙን የቀጠርና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጋስ፣ ነዳጅና የፀኃይ ኃይል ለመግዛት እየተሽቀዳደሙ ነዉ።

Gas Gasimport Stop Gasembargo Russland Krieg Symbolbild
ምስል epa Maxim Shipenkov/dpa/picture alliance

ምዕራባዉያን «አምገነን» የሚሏቸዉ ፑቲን የሚመሯትን ሩሲያን በማዕቀብ እየቀጡ፣ ከፈላጭ ቆራጮቹ የአረብ ገዢዎች ጋር መገበያየት-መወዳጃትን መርጠዋል።የምዕራቦች ዲሞክራሲ።ብቻ የአረብ ኤምሬቶቹ የኃይል ሚንስትር ሱሀይል አል-ማዝሮዩል ዛሬ እቅጩን ተናገሩ።

«ሩሲያ በጣም አስፈላጊ አባል ናት።ፖለቲካዉን ወደጎን ትተን ብናየዉ፣ የሆነ ወገን መጥቶ 10 ሚሊዮን በርሚል ማቅረብ ካልቻለ፣ በመሰረቱ ሩሲያን የሚተካ ማግኘት አንችልም።»

በቀን 10 ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ለዓለም የምታጠጣዉ ሩሲያ ባንፃሩ ብዙ ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ለቻይና ለመሸጥ ተስማምታለች።የፕሬዝደንት ፑቲን ስምምነቱን ዛሬ ይፋ ሲያደርጉ የሩብልም ዋጋ አንሰራራቷል።«ሳይቀደሙ መቅደም» ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ