1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 25/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ የካቲት 25 2013

ኢትዮጵያ ዉስጥ በትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አደረሱት የተባለዉ በደል   «በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል » ሊሆኑ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የበላይ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/3qE3R

ኢትዮጵያ ዉስጥ በትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አደረሱት የተባለዉ በደል   «በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል » ሊሆኑ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የበላይ አስታወቁ። የዓለም አቀፉ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼሌ ባቸሌት ትግራይ ክልል ወራት ባስቆጠረዉ ግጭት ደርሷል የተባለዉ ጥፋት በገለልተኛ ወገን መመርመር እንዳለበት አሳስበዋል። ባለፈው የህዳር ወር በመቀሌ፣ ሁመራ እና አዲግራት የቦምብ ጥቃት መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውን የድርጅቱ ተጠሪ ሚሼሌ ባቸሌት ተናግረዋል። እንደ ባቸሌት «በክልሉ ለደረሱ የሰብአዊ ጥፋቶች ተሳትፎ የነበራቸው እና ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊትን፣ ሕወሓት፣ የኤርትራ ወታደሮች ፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና  የአካባቢው የሚሊሻ አባላት ናቸው። » እነዚሁ ኃይሎች በአካባቢው ለደረሰው ጥፋት አንዳቸው በሌላኛው ላይ ጣት እየቀሰሩ በመሆኑ ድርጅቱ ተጨባጭ እና ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው የመብት ተሟጋቹ ኮሚሽን አስታውቋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት  እንደዘገበው የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ገለልተኛ መርማሪ አካላት ወደ ትግራይ ክልል ገብተው እውነት የማፈላለግ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ለሚደረግ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት በሩን እንዲከፍትም ተጠይቋል።

ከምስራቅ አፍሪቃ ወደ የመን ሊሻገሩ የነበሩ 20 ስደተኞች ወደ ባህር ተወርውረው ህይወታቸው ማለፉን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይ ኦ  ኤም አስታወቀ። ድርጅቱ እንዳለው ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በጂቡቲ የባህር ዳርቻ በሰዎች ከተጨናነቀች ጀልባ 80 ሰዎችን ወደ ባህር ገፍትረው ጥለዋል። ከሟቾች መሐል የ5 ሰዎች አስክሬን መገኘቱም ተገልጿል። ጀልባዋ የኢትዮጵያ እና የሶማልያ ዜጎች ሳይሆኑ አልቀሩም የተባሉ ከ18 ዓመት በታች ታዲጊዎች እና ሴቶችን  ጨምሮ ከ200 በላይ ስደተኞችን አሳፍራ እንደነበር የአሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። ከአደጋው የተረፉ ስደተኞች በጂቡቲ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።ከምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት ስራ እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በየመን አድርገው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚደረገው ስደት አሁንም እንደቀጠለ ስለመሆኑ የትናንቱ አደጋ ማሳያ ነው ሲል አይኦ ኤም ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። እጎአ በ2019 138,000 ስደተኞች በተመሳሳይ መንገድ ወደ የመን መጓዛቸውን ያመለከተው ዘገባው  የመን ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት በ2020 ቀንሶ 37,500 ደ,ርሶ ነበር ። ባለፈው የጥቅምት ወር ስምንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተመሳሳይ መንገድ ከጀልባ ተገፍትረው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። 
 

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ኦፌኮ በምርጫ እንዳንሳተፍ ተገፍተናል ማለታቸው ተቀባይነት የለውም አለ። በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ቃል አቃባይ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳሉት ገዢው ፓርቲ በምርጫው ከመወዳደር ባለፈ ምርጫውን የተሻለ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ) በመጪዉ ግንቦት ማብቂያ ሊደረግ በታቀደዉ ብሔራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ ትናንት አስታውቆ ነበር ፡፡ አንጋፋዉ የፖለቲካ ፓርቲ «ታስረዋል» ያላቸዉ ባለስልጣናቱ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ እንዲፈቱ፣ የተዘጉ በርካታ ጽሕፈት ቤቶቹም እንዲከፈቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ በበኩሉ ገዢው ፓርቲ ከምርጫው እየገፋኝ ነው ሲል ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ነገር ግን ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው አቤቱታዎች ተቀባይነት የሌላቸው  እና አሳዛኝ ናቸው ሲሉ አቶ ታዬ ይናገራሉ።«አሁን ያለውን ሁኔታ ከዚያ የባሰ አስቸጋሪ ነው አንሳተፍም ማለታቸው አሳዛን ሁኔታ እንደሆነ ነው እኔን የሚገባኝ እኛ እንደ ገዢ ፖርቲ እንደ  መንግስትም ይኼምርጫ በተጨባጭ የተለያየ ሀሳቦች ቀርበውበት ህብረተሰቡ ነጻ ሆኖ የራሱን መንግስት በራሱ ፍላጎት እንዲመሰርት ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሃላፊነት አለብን ያንን ደግሞ ከግብ ለማድረስ እየሰራን እንገኛለን።  »የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ለመገፋታቸው የአባላቶቻቸውን መታሰር በምክንያትነት ማቅረባቸው ተገቢ አይደለም ፤ ከህግ አግባብ ውጭ የታሰረ ሰው እንደሌለ ነው አቶ ታዬ የገለጹት። «መንግስት ሲታገስ መንግስት ደካማ ነው እያሉ ፤ መንግስት ህግ ሲያስከብር ደግሞ መንግስት አምባገነን ሆነ እያሉ በመሰዋእትነት የመጣውን ትግል ጠምዝዘው ለግል ጥቅም ለመጠቀም የሞከሩ ነበሩ። እና ነጻነት መጥቷል ይኬን ነጻነት መንከባከብ ያስፈልጋል።ያንን ደግሞ ማድረግ የምንችለው የህግ የበላይነትን በማስከበር ስለሆነ ወንጀል የሰሩ አካላትንን ለህግ ማቅረብ የመንግስት ትልቁ ኃላፊነት ነው።  »የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ምንም እንኳ ከምርጫው መውጣቱን ባያስታውቅም እስካሁን ዕጩ አባላቱን ስለማስመዝገቡ የተባለ ነገር የለም።

ምዕራባዊ ሱዳን የዳርፉር ግዛት በጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ አስር ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ አንድ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን አስታወቁ። በግጭቱ ከሞቱት  ውጭ ሌሎች 32 ሰዎች መጎዳታቸው ተነግሯል። በሰሜናዊ የዳርፉር ግዛት በምትገኘው በሳራፍ ኦምራ ከተማ በሚኖሩ የአረብ ፉር ጎሳዎች እና የታማ ጎሳዎች በቁራሽ መሬት ይገባኛል የቀሰቀሱት ግጭት ለጥፋቱ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ጄኔራል ያህያ መሀመድ አል ኑር ተናግረዋል። በግችቱ ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ የተባሉ በርካታ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል። በዳርፉር እና በሌሎች የሱዳን አካባቢዎች ጎልተው እየታዩ የመጡ የጎሳ ግችቶች ለሱዳን የሽግግር መንግስት ዋነኛ ተግዳሮች ሆነዋል። በአካባቢው ለግጭቶቹ መባባስ በዋነኛነት የተጠቀሰው ደግሞ ከ10 ዓመታት በላይ በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል ከአካባቢው ለቆ መውጣቱ ነው ተብሏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው የጥር ወር ብቻ  በምዕራብ እና ደቡባዊ የዳርፉር አካባቢዎች በጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 470 ሰዎች ሲገደሉ ከ120,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።
 

ርዋንዳ የጀርመን እና የአሜሪካ ኩባንያዎች ሰራሽ የሆነውን ፋይዘር ባዮንቴክ የተሰኘውን የጸረ ኮሮና ክትባት በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች።  ርዋንዳ ደሃ ሀገሮችን ለመደገፍ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በጥምረት ከሚሰራው ኮቫክስ 103,000 ብልቃጥ ክትባት ተሰጥቷት ዛሬ በመዲና ኪጋሊ ተረክባለች። ድጋፉ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመግታት ለምታደርገው ጥረት ወሳኝ ምዕራፍ ስለመሆኑ ነው የፈረንሳይ ዜና ምንጭ የዘገበው። ርዋንዳ ቀደም ሲልም በተመሳሳይ ከኮቫክስ የተለገሳትን 240, 000 ብልቃጥ  የአስትራ ዜኔካ ክትባት ተረክባለች። ርዋንዳ አሁን በድምሩ 340,000 ክትባቶችን ተረክባ ለየሆስፒታሉ ለማከፋፈል ዝግጅት እያደረገች መሆኗን የሀገሪቱ የጤና ሚንስትር አስታውቋል። ክትባቱ 171,500 ለሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች እና ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ተጋላጭ ዜጎች ከነገ ዓርብ ጀምሮ እንደሚሰጥ ተነግሯል። 12 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ርዋንዳ በተያዘው የጎርጎርሳውያን ዓመት 30 ከመቶእንዲሁም እስከ 2022 መጨረሻ ደግሞ 60 ከመቶውን የሕዝብ ቁጥር የመከተብ እቅድ አላት።   

እጎአ በ2019 በመላው ዓለም ለሰው ልጅ ለምግብነት ይውል ከነበረው አስራ ሰባት በመቶ ምግብ መወገዱን አንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አመለከተ። በዓመቱ ከመኖሪያ ቤቶች ከምግብ ቤቶች እና ከሌሎች ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች 931 ሚሊዮን ቶን ምግብ መጣሉን የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ  ዩ ኤን ኢ ፒ ዛሬ ባወጣው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። የተወገደው ምግብ ከ23 ሚሊዮን የጭነት ተሽከርካሪዎች በላይ የጭነት ልክ አለው ነው የተባለው። የሪፖርቱ ግኝት የዘርፉ ባለሞያዎች  በ54 የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ካካሄዷቸው ጥናቶች መሰብሰቡን የጀርመን ዜና ምንጭ ዲፒኤ ዘግቧል ። የተትረፈረፈ ምግብ በማስወገድ የመኖርያ ቤቶች የ11 ከመቶውን ድርሻ ሲወስዱ ፣ ምግብ ቤቶች 5 ከመቶ እንዲሁም ሌሎች ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች ደግሞ የሁለት ከመቶ ድርሻ አላቸው። አስገራሚው ነገር ደግሞ በተጠቀሰው የጎርጎርሳውያኑ 2019 በዓለም 700 ሚሊዮን ሰዎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እጃቸውን ለእርዳታ መዘርጋታቸው ነው ይላል ሪፖርቱ። ይህንኑ ተከትሎ በዓለም ላይ የሚፈጠረው  የምግብ ብክነት የሚተርፈውን ለሌላው ለማካፈል እንዲሁም   ብክነቱ የሚስከትለውን የአካባቢ ብክለት ለመከላከል ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድርጅቱ ጠይቋል።