1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 21 ቀን 2014 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ የካቲት 21 2014

ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ የዓለማችን የፖለቲካ ትኩሳት ምናልባትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ጊዜ ፤ ጦርነቱ እያሳደረ ካለው ዓለማቀፋዊ የማህበረ ፖለቲካ እና ኤኮኖሚያዊ ብርቱ ፈተናዎች ባሻገር በስፖርቱ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/47jI4

የየካቲት 21 ቀን 2014 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በስፔን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቧ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከተሰሙ ዋና ዋና የአትሌቲክስ ዜናዎች ግንባር ቀደሙ ነው፤ በኢትዮጵያ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የኮሮና ወረርሽኝ ብርቱ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ ተሰምቷል ፤ መረጃ ይዘናል። ከውጭ ከ120  ደቂቃዎች ፍልሚያ በኋላ ሊቨርፑል የዓመቱን የካራባኦ ዋንጫ አንስቷል፤ ዋንጫው ለሊቨርፑል የመጀመሪያው ወይስ መጨረሻው ይሆን ? የሩስያ ዩክሬን ጦርነት በስፖርቱ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እና የተወሰዱ እርምጃዎች ፤ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ፤ ላሊጋ እና ቡንደስሊጋ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ምን ውጤቶች  ተመዘገቡ፤ እንቃኛለን።

በአትሌቲክስ ዜናዎች ስንጀምር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በስፔን ላ ፕላና በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ትናንት አሸናፊ ሆናለች ።

አትሌቷ ርቀቱን 29:14 በሆነ ሰዓት በመግባት ነው  ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸናፊ የሆነችው። አትሌቷ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በአየርላንድ አንትሪም ኮስት በተካሄደው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ሩጫ የዓለም ክበርወሰን ማሻሻሏ አይዘነጋም። በ,ወቅቱ በርቀቱ በኬኒያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን  በ19 ሰከንዶች በማሻሻል አሸናፊ እንደሆነች ተዘግቦ ነበር። የገባችበትም ሰዓት 1:03.43 ሆኖ በስሟ ተመዝግቧል። አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በተከታታይ ያስመዘገበገበችው የክብረ ወሰን ማሻሻል ውጤቶች የአትሌቷ ብቃት ከፍተኛ ደረጃ ስለመድረሱ ማሳያ ሆኗል። ከአሌቲክስ ዜና ሳንወጣ የአራት ጊዜ ኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ  የ38 ዓመቱ እንግሊዛዊው ሞፋራህ ወደ ነገሰበት የአስር ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር ሊመለስ መሆኑ ተሰምቷል። ሞፋራህ የፊታችን ግንቦት በለንደን ለሚደረገው የ10,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ታውቋል። ሞ ፋራህ ባለፈው ዓመት የሰኔ ወር በደረሰበት የእግር ሕመም ምክንያት ማጣሪያውን ማለፍ ተስኖት ከቶክዮ ኦሎምፒክ ውጭ ሆኖ ነበር።

የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ሊጠናቀቅ የጥቂት ቀናት ዕድሜ ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የኮሮና ወረርሽን ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ ክለቦች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን እያሳጣቸው እንደሚገኝ ተነግሯል። ሊጉ ከተጀመረ በኋላ በመጀመርያው ዙር መገባደጃ አካባቢ የጠፋ መስሎ የነበረው ወረርሽኙ ትናንት በተጀመሩ የሊጉ ጫወታዎች ግን በርካታ ተጫዋቾች በተህዋሲው ተይዘው መገኘታቸው ተዘግቧል። የመጨረሻው ዙር ጫወታዎች ከመደረጋቸው በፊትም በሊጉ ውስጥ በሚሳተፉ ስምንት ክለቦች ውስጥ በተሕዋሲው የተጠቁ ተጫዋቾች እና የቡድን አባላት መኖራቸው ተገልጿል።

በድራማዊ የመለያ ምት ሊቨርፑል ቼልሲን አሸንፎ የካራባኦ ዋንጫ አንስቷል። ከ120 ደቂቃዎች ፍልሚያ በኋላ ወደ መለያ ምት ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች አስራ አንዱንም ተጫዋቾቻቸውን መለያ ምቱን አስመትተዋል። ለመለያ ምት የአፍሪካውን ሻምፒዮን በረኛውን የቀየረው ቼልሲ የማታ ማታ ድሉን አሳልፎ ለሊቨርፑል ሰጥቷል። ሊቨርፑሎች ከበረኛ ጭምር  አስራ አንዱንም ኳሶች ከመረብ ሲያገናኙ ፤ ለቼልሲ ግብ ጠባቂውን ሜንዲን ተክቶ የገባው ኬፓ አሪዛባላጋ ኳሷን ወደ ሰማይ በማጎኑ ቡድኑን ለሽንፈት አሳልፎ ሰጥቷል። ቶማስ ቱሄልም ዋንቻ ለማንሳት ከጫፍ ደርሰው የተመለሱበት እና በቁችት የተሞላ ምሽት ለማሳለፍ ተገደዋል።  በፕሪሚየርሊግ አንድ ተስተካካይ ጫወታ እየቀረው ከመሪው ማንችስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ልዩነት ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል የዓመቱን የመጀመሪያ ዋንጫ ስሟል። ክሎፕ በፕሪምየር ሊጉ ከሚደርጉት የዋንጫ ትንቅንቅ በተጨማሪ በአውሮፓ መድረክ የነገሱበትን የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ከሚፋለሙት አስራ ስድስት ቡድኖች ስምንት ውስጥ ለመግባት የመጀመርያውን ጫወታ ከሜዳቸው ውች ተጉዘው ድል ቀንቷቸው ነው የተመለሱት ።

England Fussball Chelsea vs. Liverpool
ምስል Alastair Grant/AP Photo/picture alliance

የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተጠባቂ የፕሪሚየርሊግ ጫወታዎች ተስተናግደዋል። ቀደም ሲል ሀሙስ ዕለት ወልቨርሃምፕተን ወንደረርስን በሜዳው ያስተናገደው አርሴናል 2 ለ 1 አሸንፎ  አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠበትን ዉጤት ሲያስመዘግብ ፤  ዓርብ ዕለት ኖርዊች ሲቲን ያስተናገደው ሳውዝሀምፕተን ደግሞ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል። ቅዳሜ ዕለት ወደ ጎዲሰን ፓርክ ተጉዞ  ኤቨርተን የገጠመው ማንችስተር ሲቲ በፊል ፎደን የማታ ጎል 1 ለ 0 አሸንፎ ከተከታዩ ሊቨርፑል ያለውን የነጥብ ልዩነት አስጠብቆ የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል። ውጤቱን ተከትሎ ኤቨርተን ከወራጅ ቀጠና አንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ 17 ደረጃ ለመቀመጥ ተገዷል። በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሳምንት ድራማዊ በሆነ መንገድ መሪው ማንችስተር ሲቲን ያሸነፈው ቶተንሃም በቅዳሜ ምሽቱ ጫወታ ከሜዳው ውች ተጉዞ ሊድስ ዩናይትድን ገጥሞ 4 ለ 0 አሸንፎ የተመለሰበትን ዉጤት አስመዝግቧል። ውጤቱን ተከትሎም አንድ ደረጃ አሻሽሎ ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በዕለቱ አስቶን ቪላ ብራይተንን 2 ለ 0 ፣ እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ  ብሬንትፎርድን በተመሳሳይ 2 ለ 0 አሸንፈዋል። ማንችስተር ዩናይትድ ከዋትፎርድ 0 ለ 0 ክሪስታል ፓላስ ከበርልኔይ 1 አቻ ተለያይተዋል። ትናንት እሁድ በተደረገ ቀሪ አንድ ጫወታ ደግሞ ባለሜዳው ዌስትሃም ዩናይትድ ወልቨርሃምፕተን ወንደረርስን 1 ለ o ማሸነፍ ችሏል።

ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ የዓለማችን የፖለቲካ ትኩሳት ምናልባትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ጊዜ ፤ ጦርነቱ እያሳደረ ካለው ዓለማቀፋዊ የማህበረ ፖለቲካ እና ኤኮኖሚያዊ ብርቱ ፈተናዎች ባሻገር በስፖርቱ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ቼልሲ ባለቤት እና ሩስያዊ ቱጃሩ ሮማን አብራሞቪች ቼልሲን በይፋ መልቀቃቸውን ተከትሎ የቡድንኑ መጻኢ ዕጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። የቼልሲ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስተዳዳሪዎች ክለቡን ለማስተዳደር እስካሁን አለመስማማታቸው ደግሞ ለችግሩ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው። ምዕራባውያን በሩስያ መንግስት እና ባለሃብቶች የሚመሩ ዓለማቀፍ ተቋማት ላይ እየወሰዱ ያሉት የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዕቀባዎች ደግሞ ቱጃሩን ሩስያዊ ከክለቡ አስተዳዳሪነት ለጊዜውም ቢሆን አርቋቸዋል ነው የተባለው ። ከወቅታዊ ሁኔታ ሳንወጣ ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ የሩሲያ ፎርሙላ 1 ግራንድ ፕሪክስ የመኪና እሽቅድምድም መሰረዙን አዘጋጆች አስታዉቀዋል። ፎርሙላ አንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሮ ባወጣው መግለጫው "የሩሲያ ግራንድ ፕሪክስን አሁን ባለው ሁኔታ ማካሄድ እንደማይቻል" ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጿል። በተያያዘ ይህንኑ ወረራ ተከትሎ ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ  ሩስያ የምታደርጋቸውን የእግር ኳስ ውድድሮች በገለልተኛ ሜዳ ፤ የሩስያን ስም እና ሰንደቅ አላማ ሳትጠቀም በእግር ኳስ ፌዴሬሽኗ ዓርማ እና ስም እንድታደርግ መመርያ አስተላልፏል። ነገር ግን በርካታ ሃገራት ገና ከአሁኑ ከሩስያ ጋር ምንም አይነት ውድድር እንደማያደርጉ እያስታወቁ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ኢንግላንድ ፣ ዌልስ ፣ ፖላንድ ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስዊዲን ይገኙበታል።

Zurich FIFA Praesident Gianni Infantino beim digitalen FIFA-Kongress
ምስል ULMER Pressebildagentur/imago images
Rennsport Formel 1 Sotschi Daniel Ricciardo
ምስል MAXIM SHEMETOV/REUTERS
Roman Abramowitsch | russischer Oligarch
ምስል Ben Stansall/AFP/Getty Images

ከጀርመን ቡንደስሊጋ ጫወታዎች ፤ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሁለት ክለቦች የደረጃ መሻሻል ያደረጉባቸው የቡንደስሊጋ ጫወታዎች ተደርገዋል። ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ በተደረጉ የሊጉ ጨወታዎች ሶስት ጫወታዎች አቻ ውጤቶች ሲመዘገቡ ፤ የተቀሩት ግን በመሸናነፍ ነው የተጠናቀቁት ። በዚሁ መሰረት ወደ ፍራንክፈርት ተጉዞ ኢንትራፍራንክፈርትን የገጠመው መሪው ባየርን ሙንሽን አጥቂው ሳኔ 71 ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸና ጎል ሶስት ከተከታዩ የነበረውን የነጥብ ልዩነት አስጠብቆ የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል። በአንጻሩ ተከታዩ ቦሩሽያ ዶርትሙንድ ክለብ አውስበርግን ገጥሞ ነጥብ የተጋራበትን የአንድ አቻ የተለያየበትን ውጤት አስመዝግቧል። ዉጤቱን ተከትሎም ከመሪው የነበረውን ነጥብ ማስጠበቅ ተስኖት ተመልሷል። ባየር 04 ሊቨርኩሰን አርሚኒያ ቢዬሌፌልድን 3 ለ 0 እንዲሁም አር ቢ ላይፕሲች ባኹምን ከሜዳው ውጭ 1 ለ 0 ያሸነፉበትን ዉጤቶች አስመዝግበዋል። ሊጉን ባየርን ሙንሽን በ58  ነጥብ ሲመራ ፤ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና ባየር 04 ሊቨርኩሰን በ50 እና 44 ነጥቦችሁለተኛ ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ።

FC Barcelona - Atlético Madrid
ምስል Joan Monfort/AP/picture alliance

በሌሎች የእግር ኳስ ወሬዎች ደግሞ

በስፔይን ላሊጋ መድፈኞቹን ለቆ ባርሴሎናን የተቀላቀለው የጎል አዳኙ ኦባምያንግ ጎል ማደኑን ተያይዟል። ትናንት እሁድ ባርሴሎናን ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ያገናኘው ጫወታ በባርሴሎና አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ፤ የእርሱ መሄድ የክለቡን መነቃቃት ከፍ ያደረገው ኦቤምያንግ የመጀመርያዋን ጎል ከመረብ አሳርፎ ፤ በሁለት ጫወታዎች ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አራት አድርሶለታል።  በሌላ ዜና ባርሴሎናን ለቆ ወደ ፈረንሳዩ ፒ ኤስ ጂ ያቀናው ሊዮኔል ሜሲ  ሊግ አንድ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነለት እየተገለጸ ነው። አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ የአሜሪካው ኢንተር ማያሚ የእግር ኳስ ክለብ ሜሲን ጨምሮ አምስት አንጋፋ የአውሮጳ ሊጎች ተጫዋቾችን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ማያሚ ፤ የ34 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ፒኤስ ጂን የመልቀቅ ፍላጎት ካለው የማረፊያው ትክክለኛ ቦታ እኛጋ ነው ብሏል። ክለቡ ከሜሲ በተጨማሪ በአውሮጳ የተለያዩ ሊጎች ውስጥ ዝናን ያተረፉ እንደነ ሉዋንዶውስኪ፣ ሃላንድ ኬሴ እና ክሪስተንሰን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን የማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ይፋ አድርጓል። በእርግጥ ሜሲን ጨምሮ ስማቸው የተጠቀሰው ተጫዋቾች ወደ ማያሚ ያቀኑ ይሆን ? አብረን እናያለን። 

Leo Messi Paris Saint Germain v Olympique Lyonnais
ምስል Jose Breton/NurPhoto/imago images

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ