1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 1 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 1 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫ የማግኘት ዕድሉን አስፍቷል። ሊቨርፑልን በሜዳው 4 ለ1 በማንኮታኮትም ለዋንጫ ሽሚያ የነበረውን ዕድል አጥብቦበታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በፍራይቡርግ ተሸንፏል። የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ መሸነፍ ግን ዶርትሙንድ ስድስተኛ ደረጃውን እንደያዘ እንዲቆይ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/3p4kg
Fußball | Premier League | Manchester City - Crystal Palace
ምስል Clive Brunskill/PA Images/imago images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቻን አፍሪቃ የእግር ኳስ ፍጻሜ ሞሮኮ ዘንድሮም ዋንጫውን ወስዳለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫ የማግኘት ዕድሉን አስፍቷል። ሊቨርፑልን በሜዳው 4 ለ1 በማንኮታኮትም ለዋንጫ ሽሚያ የነበረውን ዕድል አጥብቦበታል። ማንቸስተር ዩናይትድም ነጥብ በመጣሉ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ አልተሳካለትም። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በፍራይቡርግ ተሸንፏል። የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ መሸነፍ ግን ዶርትሙንድ ስድስተኛ ደረጃውን እንደያዘ እንዲቆይ አድርጎታል። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድም ባርሴሎናም ድል ቀንቷቸዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ ግን በመሪነት እየገሰገሰ ነው። በጣሊያን ሴኢኣ መሪው ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን አንገት ላንገት ተያይዘዋል። የላይፕትሲሽ እና ሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ወደ ቡዳፔስት ተዛውሯል።

ቻን የአፍሪቃ የእግር ኳስ

በቻን አፍሪቃ የእግር ኳስ ፉክክር የፍጻሜ ጨዋታ ዘንድሮም የሞሮኮ ቡድን ዋንጫውን በመውሰድ ቀዳሚ መሆን ችሏል። ሞሮኮ ትናንት ተፎካካሪው የማሊ ቡድንን 2 ለ0 በማሸነፍ ነበር የዋንጫ ባለድል መሆን የቻለው። የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ጉልበት እና ፍትጊያ ተስተውሎበታል። ውድድሩ የተከናወነበት ካሜሩን ያውንዴ ከተማ ውስጥ የሚገኘው አኅማዱ አሂጆ ስታዲየም በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት መያዝ ከሚችለው በታች 10,000 ታዳሚያን እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።

በቻን አፍሪቃ ፍጻሜ ማሊን ያሸነፈው የሞሮኮ ቡድንከቶጎ ጋር ሲጋጠም (ፎቶ፦ ከማኅደራችን)
በቻን አፍሪቃ ፍጻሜ ማሊን ያሸነፈው የሞሮኮ ቡድንከቶጎ ጋር ሲጋጠም (ፎቶ፦ ከማኅደራችን)ምስል Alain Guy Suffo/Sports Inc/empics/picture alliance

በትናንቱ ግጥሚያ የማሊው ኢሳካ ሳማኬ መደበኛው ጨዋታ ተጠናቆ በተጨመረው 3ኛ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመሰናበቱ ማሊ የባከኑ ሰአት ጭማሪዎችን በ10 ተጨዋቾች ለመጨረስ ተገዳለች።

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት የተከናወነውን ያለፈውን ዋንጫም በሀገሩ አሰናድቶ ድል መቀዳጀቱ የሚታወስ ነው። አፍሪቃ ውስጥ ለብሔራዊ ቡድናቸው በሀገራቸው ብቻ የሚጫወቱ ተጨዋቾች የሚሳተፉበት ቻን አፍሪቃ ዋንጫ ከተጀመረ አንስቶ ለሁለት ጊዜ ዋንጫ የወሰደው የሞሮኮ ቡድን ብቻ ነው። ከዚህ ቀደም የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመጀመሪያውን ዋንጫ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ሲወስድ፤ ሁለተኛውን በሁለተኛ ዓመቱ ሱዳን በእጇ አስገብታለች። ከዚያም ደቡብ አፍሪቃ እና ሩዋንዳ ነበሩ አሸናፊዎቹ። ቀጣዩ ውድድር በ2022 አልጄሪያ ታሰናዳለች።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲኒን ከግስጋሴው የሚያስቆመው አልተገኘው። ያለፈው የጨዋታ ዘመን የዋንጫ ባለድሉ ሊቨርፑል እንኳን በሜዳው አንፊልድ በማንቸስተር ሲቲ የ4 ለ1 ከባድ ሽንፈት ነው የገጠመው። በእርግጥ ለትናንቱ የሊቨርፑል ሽንፈት በዋናነት ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ተጠያቂ ቢሆንም ማለት ነው። ሊቨርፑል በሞ ሳላህ ግብ አንድ እኩል ቢሆንም፤ ግብ ጠባቂው በፈጸማቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች እና በማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች ብቃት እና ቅልጥፍና ለሽንፈት ተዳርጓል። የፊታችን ማክሰኞ ለሻምፒዮንስ ሊግ ከላይፕትሲሽ ጋር ያለው ግጥሚያ በኮሮና ምክንያት ጀርመን ውስጥ አይከናወንም። ይልቊንስ ውድድሩን ሐንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ ውስጥ እንዲደረግ ተወስኗል።

ሊቨርፑልን 4 ለ1 በሜዳው አንፊልድ ጉድ ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ
ሊቨርፑልን 4 ለ1 በሜዳው አንፊልድ ጉድ ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላምስል Clive Brunskill/PA Images/imago images

ለማንቸስተር ሲቲ ቀዳሚዋን ግብ በ49ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ቀደም ሲል ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ኳሷን ከግብ ጠባቂው በስተቀኝ ከማእዘን በላይ የሰደዳት ኢልካይ ጉንዶዋን ነው። የቱርክ ዝርያ ያለው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ኢልካይ ጉንዶዋን በ73ኛ ደቂቃ ላይም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ራሂም ስተርሊንግ 76ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፋትን ኳስም አመቻችቷል። ሦስቱም ግቦች ታዲያ በሊቨርፑል ግብ ጠባቂ ስህተት የተገኙ ናቸው። አሊሰን ቤከር ተከላካዮች ጫና ሲበረታባቸው ወደ ኋላ መልሰው የሚልኩለትን ኳስ በስህተት አለያም በቸልተኝነት አሳጥሮ በመምታት ለባላጋራ ተጨዋቾች ሲሳይ አድርጎታል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ከግቡ በስተግራ በኩል ፈጣኑ ፊል ፎደን በድንቅ ኹኔታ የመታት ኳስ በእርግጥም አደገኛ ነበረች። አሊሰን ይህችንም ሳይዝ ጨዋታው በማንቸስተር ሲቲው ኢልካይ ጉንዶዋን እና በሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከር ዋና ተዋናይነት 4 ለ1 ተጠናቋል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በ10 ነጥብ ርቆ ደረጃውን በ50 ነጥብ ይመራል።  ማንቸስተር ዩናይትድ በ45 ነጥብ ይከተላል። ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ከኤቨርተን ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 እኩል ተለያይቷል። በዚህም ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነቱ ለማጥበብ የነበረውን ዕድል አምክኗል።

ላይስተር ሲቲ በበኩሉ በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ላይ ከሚገኘው ዎልቭስ ጋር ትናንት ተጋጥሞ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። 27 ነጥብ ባለው ዎልቭስ ላይ ግብ ማግባት የተሳነው ላይስተር ሲቲ 43 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት በሜዳው የማንቸስተር ሲቲ ውርጅብኝ የወረደበት ሊቨርፑል በ40 ነጥቡ ተወስኖ አራተኛ ደረጃውን አልለቀቀም።  ሼፊልድ ዩናይትድን ትናንት 2 ለ1 የረታው ቸልሲ አንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል።  ዘንድሮ ድል የራቀው አርሰናል ከትናንት በስትያ በአስቶን ቪላ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። በ31 ነጥቡም 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

እ.ጎ.አ. በ2019 ዓ.ም በፊፋ ምርጥ የዓለማችን ግብ ጠባቂ የተሰኘው የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ፤ አሊሰን ቤከርን ምን ነካው?
እ.ጎ.አ. በ2019 ዓ.ም በፊፋ ምርጥ የዓለማችን ግብ ጠባቂ የተሰኘው የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ፤ አሊሰን ቤከርን ምን ነካው?ምስል Getty Images/AFP/M. Bertorello

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ባየርን ሙይንሽን 48 ነጥብ፤ ላይፕትሲሽ 41፤ ቮልፍስቡርግ 38፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት 36 ነጥብ ይዘው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ተደርድረዋል።  ባየር ሙይንሽን ዐርብ ዕለት ሔርታ ቤርሊንን ያሸነፈው በጠበበ ልዩነት 1 ለ0 ነው። ዛሬ ማታ ለዓለም ቡድኖች ግማሽ ፍጻሜ ከግብጹ አል አህሊ ጋር ይጋጠማል። ባየር ሌቨርኩሰን በ35 ነጥብ 5ኛ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ32 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በቡንደስሊጋው እስከ 6ኛ ደረጃ ከተደረደሩ ቡድኖች መካከል ከቦሩስያ ዶርትሙንድ በስተቀር ሁሉም ቀደም እንዳለው ሳምንት ማሸነፍ ችለዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ብቻ ቅዳሜ ዕለት በፍራይቡግ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል።

ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች፦ ባየር ሌቨርኩሰን ሽቱትጋርትን ያሸነፈበት ግጥሚያ በርካታ ግቦች የቀቆጠሩበት ነው። በዚህ ጨዋታ ሌቨርኩሰን ሽቱትጋርትን 5 ለ2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ነው ያሸነፈው። ላይፕትሲሽም ተጋጣሚው ሻልከን 3 ለ0 ሸኝቶታል። ሻልከ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መሰናበቱ የማይቀር ነው። እስካሁን በተደረጉ 20 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፎ 5 ጊዜ አቻ ወጥቶ በያዘው 8 ነጥብ ብቻ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 18ኛ ላይ ተዘርግቷል። ከእሱ በላይ ያለው ማይንትስ እንኳን ቅዳሜ ዕለት ዑኒዮን ቤርሊንን ያሸነፈበት ነጥቡ ተደምሮለት 13 ነጥብ አለው። ከዚያም አርሜኒያ ቢሌፌልድ እንዲሁም ሔርታ ቤርሊን እኩል 17 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ብቻ ተለያይተው 16ኛ እና 15ኛ ደረጃን ተቆናጠዋል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 ማሸነፍ የቻለው ኮሎኝ ቡድን በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቮልፍስቡርግ አውግስቡርግን 2 ለ0 ድል አድርጓል።

ትናንት ሁለት ግጥሚያዎች ሊከናወኑ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበረ ቢሆንም የብሬመን እና አርሜኒያ ቢሌፌልድ ጨዋታ በብርቱ የበረዶ ብናኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ግን ሆፈንሃይምን 3 ለ1 አሸንፏል። ሆፈንሃይም ከበላዩ ቬርደር ብሬመንን ከበታች አውግስቡርግን አሰልፎ በተመሳሳይ 22 ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት 12ኛ ደረጃን ይዟል።

የስፔን ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ መሪው አትሌቲኮ ማድሪድ ከሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹ አንደኛውን ዛሬ ማታ ከሴልታ ቪጎ ጋር ያከናውናል። እስካሁን 50 ነጥብ ሰብስቧል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባርሴሎና 43 ነጥብ ይዞ ይከተለዋል።  ትናንት ከቤቲስ ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ለ2 አሸንፏል። ሪያል ማድሪድ በበኩሉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በተመሳሳይ 43 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ከሁሴካ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ1 ነበር ያሸነፈው። የፊታችን ረቡዕ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የሚጋጠመው ሴቪያ በ42 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ቪላሪያል 36 ነጥብ ይዞ ይከተለዋል።  ከትናንት በስትያ ከኤልሼ ጋር ተጋጥሞ 2 እኩል ተለያይቷል።

የባርሴሎና አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ (ፎቶ ከማኅደራችን)
የባርሴሎና አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ (ፎቶ ከማኅደራችን)ምስል Cesar Manso/AP/picture alliance

በአጠቃላይ በፕሬሚየር ሊጉ፤ በቡንደስሊጋው፣ ላሊጋው እና ሴሪኣው ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎችን ደግሞ እናቅርብላችሁ። በፕሬሚር ሊጉ፦ የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ በ16 ግቦች ይመራል። የኤቨርተኑ ካልቬርት ሌዊን፤ የማንቸስተር ዩናይትዱ  ፈርናንዴስ እንዲሁም የቶትንሃም ሆትስፐሮቹ ኬን እና ሶን ሄዉንግ ሚን በ13 ይከተላሉ። የሊድሱ ባምፎርድ እና የላይስተር ሲቲው ቫርዲ በ11 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ሦስተኛ ናቸው።

በቡንደስሊጋው፦ ሮቤርት ሌቫንዶብስኪ በ24 ግቦች ይመራል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አንድሬ ሲልቫ 17 ግቦች ይዞ ይከተለዋል። የዶርትሙንዱ ሃላንድ እና የቮልስፍቡርጉ ቬግሆርስት 14 ግብ አላቸው ሦስተኛ ናቸው። የሆፈንሃይሙ ክራሚች በ13 ግቦች አራተኛ ደረጃን ይዟል። የባየር ሙይንሽኑ ቶማስ ሙይለር ከሽቱትጋርቱ ዋማንጊቱካ በአንድ ግብ ተበልጦ በ10 ከመረብ ያረፉ ኳሶች 6ኛ ነው።

በስፔን ላሊጋ 14 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሉዊስ ሱዋሬዝ በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል። 13 ግቦች ያላቸው የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ እና የሴቪያው ኤን ኔሴሪ ይከተሉታል። የቪላሪያሉ ጄራርድ ሞሬኖ በ12 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። የሪያል ማድሪዱ ካሪም ቤንዜማ፣ የሌቫንቴው ሞራሌስ እንዲሁም የሪያል ሶሴዳዱ ኦዪያርዛባል በ10 ግቦች የአራተኛ ደረጃን በጋራ ይዘዋል።

ቡንደስሊጋ፦ ሆፈንሃይም እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት ግጥሚያ በከፊል (ፎቶ ከማኅደራችን)
ቡንደስሊጋ፦ ሆፈንሃይም እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት ግጥሚያ በከፊል (ፎቶ ከማኅደራችን)ምስል Jan Huebner/imago images

በጣሊያን ሴሪኣ በደረጃ ሰንጠረዡ 42 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ላይ የሚገኘው ጁቬንቱስ አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ16 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በኮከብ ግብ አግቢነት ይመራል። በ49 ነጥብ መሪ የሆነው የኤስ ሚላኑ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ በ47 ነጥብ 2ኛ ደረጃን የያዘው ኢንተር ሚላኑ ሉካኩ እንዲሁም የላትሲዮ ኢሞቢሌ 14 ግቦችን አስቆጥረው ሁለተኛ ናቸው። የቶሪኖው ቤሎቲ እና የካግሊያሪው ሆዋ ፔድሮ 11 ከመረብ ያረፉ ኳሶች አሏቸው። በኮከብ ግብ አግቢነቱ ተርታ ሦስተኛውን ይዘዋል።

ዝላታን ኢብራሂሞቪች በሴሪኣው 500ኛ ግቡን ባስቆጠረበት ግጥሚያ ኤሲ ሚላን ክሮቶኔን 4 ለ0 ሸኝቷል። ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና አንቴ ሬቢች ከ64ኛው እስከ 70ኛው ደቂቃ በስድስት ደቂቃዎችም ብቻ ሦስት ግቦችን በተከታታይ አስቆጥረው በርካቶችን አስደምመዋል። ቀዳሚዋን ግብ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረውም ዝላታን ነው። ኢንተር ሚላን ነገ ከጁቬንቱስ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ይጠበቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ