1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዕፅዋትን በሽታ በፎቶ የሚለየው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 15 2013

ጀርሚያ ባይሳ እና ቡዔዝ ብርሃኑ በተባሉ ሁለት ወጣቶች የተሰራው ይህ መተግበሪያ ዕጽዋትን ፎቶ በማንሳት ብቻ በሽታን የሚለይ ሲሆን መወሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎች ጭምር ለተገልጋዮቹ የሚጠቁም ነው።መተግበሪያው ያለኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራ ሲሆን ለጊዜው በአራት ቋንቋዎች እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።

https://p.dw.com/p/3r2xm
Äthiopien | Software von Jermia Bayisa und Boaz Berhanu zu Pflanzen
ምስል Privat

​​​ሳይንስና ሀብረተሰብ ፣ የዕፅዋትን በሽታ በፎቶ የሚለየው መተግበሪ


መቀመጫውን ጅማ ከተማ ያደረገው «ደቦ ኢንጅነሪንግ» የተባለ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ለግብርናው ዘርፍ አጋዥ የሆነ መተግበሪያ ጥቅም ላይ አውሏል።መተግበሪያው ዕጽዋትን ፎቶ በማንሳት ብቻ በሽታን የሚለይ ሲሆን መወሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎች ጭምር ለተገልጋዮቹ የሚጠቁም ነው።
በምስል የዕፅዋትን በሽታ የሚለየው መተግበሪያ ጀርሚያ ባይሳ እና ቡዔዝ ብርሃኑ በተባሉ ሁለት ወጣቶች የተሰራ ነው።ወጣቶቹ በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኙ  ሲሆኑ ፤ቡዔዝ ከከሚሴ ጀርሚያ ከአምቦ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ  ጅማ ዩንቨርሲቲ ባቀኑበት ወቅት ነበር  የተዋወቁት።ሁለቱም ከተለያዬ የትምህርት መስክ የመጡ ቢሆንም በቴክኖሎጅው ዘርፍ ህብረተሰቡን ማገልገል የጋራ ፍላጎታቸው ነበርና ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ  ከሁለት አመት በፊት ደቦ ኢንጅነሪንግ  የተባለ  መለስተኛ የቴክኖሎጅ ኩባንያ መሰረቱ።ኩባንያው ሙያቸውን አቀናጅተው በጋራ ለመስራት የወጠኑት በመሆኑ ፤ደቦ የሚለው የኩባንያው ስያሜም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ወጣት ቡዔዝ ይገልፃል።

Äthiopien | Jermia Bayisa und Boaz Berhanu - Softwareentwickler
ምስል Privat

« ቢ ኤስ ሲ ጨርሰን ማስተርስ እየተማርን እኔ በኮምፒውተር ሳይንስ  ጀርሚያ ደግሞ በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የተለያየ የትምህርት ዘርፍ ነው ያለን። ስለዚህ የሆነ ችግር ለመፍታት ስንተባበርና አንድ ላይ ስንሰራ ነው ውጤታማ የምንሆነው። ምክንያቱም እኔ ጋ የሌለ እሱ ጋ ይኖራል እሱ ጋ የሌለ እኔ ጋ ይኖራል።ስለዚህ ይህንን አንድ አድርገን ለመስራት ስንነሳ ይህንን  የሚደገፍ ደቦ ብለን ተነሳን ማለት ነው።እንደሚታወቀው የተለያዩ ገበሬዎች ተሰባስበው የአንዱን ገበሬ ችግር ለመፍታት የሚሄዱበት የሀገራችን ባህላዊ ተባብሮ የመስራት ዘዴ ነውና በቴክኖሎጅ ዘርፍም ይህንን ማስተዋቅ አለብን በማለት አንድ የማህበረሰባችን ችግር ለመፍታት ስለተነሳን ይህንን የሚገልጽ ዓላማ  ስለሚገልፅልን  ደቦ ብለን ተነሳና ማለት ነው ።»በማለት ገልጿል።
ወጣቶቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በሁሉም ዘርፎች የማዋል ሀሳብ ቢኖራቸውም የመጀመሪያ ትኩረት ያደረጉት በኢትዮጵያ  አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደርበትን የግብርና ስራ የሚያዘምንና ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ይመለከቱት የነበረውን በግብርናው በዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን የሚፈታ ቴክኖሎጅ ማበልፀግን ነበር።ወጣት ጀርሚያ እንደሚለው በዘርፉ የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶችን ማገላበጥ ሲጀምሩ ደግሞ በዕፅዋት በሽታ ላይ ብቻ ማተኮርን መረጡ። 

Pokemon Go in Afrika
ምስል Getty Images/S.Heunis

«መጀመርያ ግን  85 በመቶ የሚሆነው የኛ ህዝብ ገበሬ ስለሆነ፤ወይም ደግሞ የሚተዳደረው በግብርና ስለሆነ መጀመሪያ የግብርናን እናስቀድም በሚል ነው። የግብርናው ዘርፍ ውስጥ ስንገባ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ችግሮችን አገኘን።ችግሮችን ስንጠይቅ፣ ጥናት ስናደርግ ፣የጥናት ወረቀቶችን ስናነብ በሽታው በጣም የሚያስቸግር አይነትና ነበር። የዕፅዋት በሽታ በአጠቃላይ ማለት ነው። ከዛ እሱን አስቀደምን ማለት ነው።» በማለት ነበር ወጣት ጀርሚያ የገለፀው።
በዚህ ሁኔታ በ2012 ዓ/ም ዕፅዋትን ፎቶ በማንሳት በበሽታ መያዝና አለመያዛቸውን የሚለይ እንዲሁም መፍትሄ የሚጠቁም መተግበሪያ ያበለፀጉ  ሲሆን፤ በቡና ምርቷ በምትታወቀው ጅማ የተመለከቷቸው የቡና ተከልን የሚፈታተኑ በሽታዎች ደግሞ እንደ ወጣት ቡኤዝ ገለፃ የሰሩትን መተግበሪያ ይህንኑ ችግር በመፍታት ላይ እንዲያውሉት አድርጓቸዋል።
«እንደሚታወቀው ቡና የሀገራችን ትልቁ የእክስፖርት ምርት ነው።ትልቅ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ የግብርና ውጤት ነው።እኛ ደግሞ ጅማ ስለሆንን እንደሚታወቀው ጅማ አካባቢ በስፋት ቡና ይመረታል። በዚህ የቡና ምርት ሂደት ውስጥ የቡና በሽታ ትልቅ ተጽዕኖ እንዳለው ከተለያዩ የቡና በሽታ ተመራማሪዎች ካገኘነው መረጃ በመነሳት እዚህ የቡና በሽታ መረጃ ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም የቡና ቅጠሎቹን ናሙና  በመሰብሰብ ምን ያህል እንደ ተጠቃ ከቅጠሉ በመነሳት የመከላከያ መንገዶች ምን መሆን እንዳለባቸው  የሚጠቁም መተግበሪያ ለመስራት ነው የተነሳነው። በዚህም ከተለያዩ በጅማ ዙሪያ ከሚገኙ የቡና እርሻዎች «ዳታ» በመሰብሰብ የተጠቁ ቅጠሎቹን ምስል በመሰብሰብ ከዚያ «አርትፊሻል ኢንተለጀንስ»ን በመጠቀም  የሰራነውን በሞባይልና በዴስክቶፕ መተግበርያ ላይ በመጫን ሠዎች እንዲጠቀሙ ለማስቻል ማለት ነው።» በማለት ወጣት ቡኤዝ ገልጿል።
ይህ አገልግሎት  በትልልቅ የቡና ማሳዎች ላይ የድሮን ቴክኖጅ በመጠቀም ጭምር የሚከናወን ነው።መተግበሪያው ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም መረጃና ምስልን በማቀናበርና  በመተንተን  የዕፅዋቱን በሽታ ከለየ በኋላ መወሰድ ያለባቸውን መፍትሄዎች ጭምር ለተገልጋዮቹ የሚጠቁም ሲሆን፤ከዕፅዋት ምርምር ባለሙያዎች ጋር  በቅንጅት የሚሰራ ነው።

Indonesien Kaffee aus Exkrementen von Fleckenmusangs Alamid-Bohnen
ምስል Getty Images/N. Loh

«በመጀመሪያ ቡና ነው በቆሎ ነው ስንዴ ነው የሚለውን ይለያያል። ማለት በመጀመሪያ የትኛው ነው የሚለውን ይለያል ማለት ነው።ከዚያ በኋላ ስንዴ ከሆነ ስንዴ ላይ ያሉትን በሽታዎች ይታወቃሉ በጣም አስቸጋሪ የሆኑና  »ሲስተማች»ን ላይ የተጫኑ  በቆሎ ከሆነ ደግሞ  በብዛት የሚታዩ የበቆሎም እንደዛው የታወቁ በሽታዎች አሉ። የቡና የሚታወቁ በሽታዎች አሉ። ይለያል ያለው ነገር ይነገራል። ከዚያ በኋላ መፍትሄ እንዲናገር ይደረጋል። ይህንን ስንሰራ ግን ብቻችንን አይደለም የሠራነው። በዕፅዋት በሽታ «ኤክስፐርት» ከሆኑ ሰዎች ጋር ሆነን ነው ማለት ነው።»በማለት ወጣት ጀርሚያ ገልጿል። 
ጀርሚያና ቡኤዝ እንደሚሉት በጅማና አካባቢዋ የሚገኙ  የቡና አምራች ገበሬዎች በዚህ መተግበሪያ ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ አገልግሎቱ  በበይነ መረብ ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አማካኝነት በአንድ ጊዜ ወይም በየወሩ በሚደረግ ክፍያ የሚጫን ነው።መተግበሪያው ያለኢንተርኔት ግንኙነት የሚሰራ ሲሆን ለጊዜው በአራት ቋንቋዎች እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።አጠቃቀሙን የበለጠ ቀላል ለማድረግም የመጠቀሚያ ቋንቋዎቹን ቁጥር ከፍ የማድረግና መፃፍና ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ በድምፅ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ ይዘዋል።
«ቋንቋ ችግር ስላለ አሁን በአራት ቋንቋዎች ጀምረናል። የጀመርነው በአማርኛ በትግርኛ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዘኛም አለ።ደቡብ ላይም ለመስራት ሰው እያፈላለግን ነው።ቋንቋውንመተርጎም ብቻ ነው። በዚህ መንገድ በሌሎች ቋንቋዎችም «እስኬል አፕ»እያደረግን ለመሄድ ነው።ማንበብና መረዳት ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ  በድምፅ የሚያዙትን ነገር የሚሰራ ነው።በ«ቮይስ አሲስታንስ» የሚያዙት ነገር ተረድቶ እንዲሠራ ማድረግ ነው።ለምሳሌ  አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ሄዶ  የሞባይል መተግበሪያውን ከፍቶ ፎቶ አንሳ ሲለው እንዲያነሳለት። ቅጠሉ ጤናማ ነው አይደለም ብሎ ሲጠይቅ መልስ የሚሰጥ ጭምር ነው።»በማለት ጀርሚያ አብራርቷል።

Kaffee Bauer in Äthiopien
ምስል AP Photo

ለዚህ ስራቸውም ወጣቶቹ በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የግሪን ኢኖቬሽን ሽልማትን፣በ2020 ደግሞ በአፍሪቃ ደረጃ በየዓመቱ በሚዘጋጅ ሜስት አፍሪካ በተባለ ውድድር የኢትዮጵያ አሸናፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ወጣቶቹ ገለፃ ከግብርናው ዘርፍ  በተጨማሪ በትራንስፖርት ዘርፍ ለትራፊክ ቁጥጥር አጋዥ የሆነ ቴክኖሎጅ፣ በጤናው ዘርፍ ደግሞ በኮቪድ-19 በሽታ የተያዘን ሰው መለየት የሚያስችልና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን የሚቆጣጠር እንዲሁም የወባ በሽታ አምጭ ትንኞችን ከሌሎቹ ትንኞች የሚለይ ቴክኖሎጅ ሰርተዋል። 
በቀጣይም በጅማና በአካባቢዋ  ብቻ የታጠረውን  የቴክኖሎጅ እገዛ  በማስፋፋት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የማዳረስ ህልም አላቸው።ያም ሆኖ ስራው በእነሱ አቅም ብቻ የማይቻል በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያሻቸው አስረድተዋል።

ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ