1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓቢይ ጥሪና ምላሹ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 25 2013

ዶክተር ዓቢይ ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ትንኮሳዎችን በንቃት እንዲከታተሉና ከመከላከያ ሠራዊት ጎንም እንዲቆሙ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ ስሜቶች ተንጸባርቀዋል።እርምጃው ተገቢ ነው ከሚሉት አንስቶ የሚያዋጣው ሰላማዊ መፍትሄ ነው እስካሉት ድረስ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3ksYn
Dr. Abiy Ahmed
ምስል DW/S. Teshome

የዓቢይ ትዕዛዝና ምላሹ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የትግራይ ክልል የሚያስተዳድረው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሕወሓት ትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ሠራዊቱም ሃገር የማዳን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ እንደተሰጠው ዛሬ ማለዳ አሳውቀው ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ትንኮሳዎችን በንቃት እንዲከታተሉና ከመከላከያ ሠራዊት ጎንም እንዲቆሙ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ ስሜቶች ተንጸባርቀዋል።እርምጃው ተገቢ ነው ከሚሉት አንስቶ የሚያዋጣው ሰላማዊ መፍትሄ ነው እስካሉት ድረስ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።ዳዊት ደስ በፌስቡክ 
«ዶክተር ዐቢይ እስከዛሬ ሕግ ባለማስከበርህ ንፁሃን ሲሞቱ የእምነት ቤቶችና የሃገር ንብረት ሲወድም ዝም በማለትህ ህዝብ አዝኖብህ ነበር።አሁን የጀመርከውን በድል ጨርስ ከጎንህ ነን።እግዚአብሔር ከሠራዊታችን ጋር ይውጣ፣ የትግራይ ህዝብ ክፉ አይንካውኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር» ሱሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
«መወያየት መደራደር መከራከር እንጂ ጦርነት ለማንም አይጠቅምም በምዕራብ ከኦነግ ጋር በሰሜን ከህወሃት ጋር በመላው ኦሮምያ ከተሞችን ጨምሮ ከቄሮ ጋር የብሔር ጥያቄ አንግበው እያቆጠቆጡ የመጡ ብሄሮችን በምን አቅም ነው የሚያሸንፈው?ሐገር ለማዳን ከተፈለገ በጠረጴዛ ዙሪያ ተመለሱ» የሚለውን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበዋል።ከእነዚህ ለአብነት ካቀረብናቸው አስተያየቶች ሌላ ቁጣ፣ዘለፋና ወቀሳ የያዙ በርካታ አስተያየቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተንሸራሽረዋል።ከዓቢይ ጥሪ በኋላ የክልል መንግሥታት ባወጧቸው መግለጫዎች የትግራይ ክልል መንግሥት ሰነዘረ የተባለውን ጥቃት በማውገዝ የሃገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅና ሃገሪቱን ለማረጋጋት ለፌደራል መንግሥቱ ድጋፋቸውን ማረጋገጣቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።የኦሮምያ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ  ህወሀት በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ላይ ይፈጽማል ያሉትን ጥቃት  ለመከላከል መንግሥታቸው ከፌደራል ኃይሎችና ከህዝቡ ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል። «የመከላከያ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ላይ ትናንት ለሊት ጥቃት በመሰንዘር ህወሀትበፌደራል መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል» ያሉት አቶ ሽመልስ «ህወሃት ሸኔ የተባለውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አንጃ ሲያስታጥቅ እንደነበርና ፣ቡድኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይወስዳል ያሉትን የኃይል እርምጃም ሲደግፍ መቆየቱን ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት እና የሀገራችን ኅልውና ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ «መከላከያን መንካት ማለት በሀገር ኅልውና መምጣት ነውና ሁሉም ሕዝብ ከመከላከያ ጎን ሊቆም ይገባዋል» ሲሉም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በአማራና በትግራይ ክልል ድንበር ላይ ህወሃት ሞከረ ያሉት ጥቃት በክልሉ ልዩ ኃይል ሙሉ በሙሉ ከሽፏል ሲሉ ዛሬ መናገራቸው ተዘግቧል። አቶ ተመስገን ትህነግ የጥቃት ሙከራው የተደረገው  በአማራ ክልል በሶሮቃና ቅራቅር አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል። ህዝቡ ወታደራዊውን እርምጃ በመደገፍ ከመንግሥት ጎን በመቆም እንዲያግዝና አካባቢውን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ደግሞ ህወሃት ወስዷል ባለው ተንኳሽ እርምጃ ማዘኑን በመግለጫው አስታውቆ የሃገሪቱ ደህንነት ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነትም ገልጿል።ከዚህ ቀደም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የደረሱ ጥቃቶች የተፈጸሙት በህወሃት ኃይሎች ነው ያለው ክልሉ ፣ሁሉም ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ከመከላከያ ኃይል ጋር እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዑሞዱ ኡጁሉ «የሀገር ክህደት ወንጀል»ሲሉ የገለጹት፣ ህወሃት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ፈጽሟል ያሉት ጥቃት ሊኮነን ይገባዋል ብለዋል።የክልሉ የጸጥታ አካላት ህዝቡን የመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ህዝቡም በፈንታው ከጸጥታ አባላት ጎን በመሆን ሰላሙን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል። መንግሥት በህወሃት ላይ ጀመረ ያሉትን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠንክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው  የአሁኑ ጠብ አጫሪነትን ለሃገሪቱ አደጋ መሆኑን ጠቁመው አመራሩ የጸጥታ ኅይሎችና ህዝቡ ሃገሪቱ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት ደግሞ " የዜጎችን ደህንነትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳካት በግንባር ቀደምትነት እንሰለፋለን"ሲል ለመንግሥት ድጋፉን ገልጿል።የሀረሪ ክልል መንግስትና ህዝብ ከሰራዊታችን ጎን በመሰለፍ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።ብሏል ክልሉ ባወጣው መግለጫ።የክልሉ ህዝብም ከምንጊዜውም በላይ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በከፍተኛ ትኩረትና ንቃት እንዲጠብቅ መንግሥት የሚያወወጣቸውን መግለጫዎችም እንዲከታተል አሳስቧል።የትግራይ ክልል መንግሥትም መግለጫ አውጥቷል።የትግራይ ክልል መንግሥት ድምጸ ወያኔ በተባለው ጣቢያ ባሰራጨው መግለጫ «ሕገወጥ አሃዳዊ ቡድን» ሲል የጠራው የፌደራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሃገር መከላከያ ሠራዊት በተጠንቀቅ እንዲቆምና ወደትግራይ እንዲጓዝ በማድረግ ለመውረር እያሰማራው ነው ሲል ከሷል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የትግራይ ክልልን በሚመራው በሕወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ የትግራይ ክልል መንግሥት ባወጣው በዚህ መግለጫ፣«በድርጅት መንግሥትና ሕዝብ መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን ገልጾ የተሰጠው መልስ ግን ህዝብን የመቅጣት እርምጃ ሆኗል ብሏል።የሰሜን እዝ «አምባገነን» ያለው  መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃ ለማክሸፍ ከክሉ ጎን ሆኖ መታገል ጀምሯል ብሏል።የትግራይ ህዝብ በህልውናው ላይ ያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመመከት በከፍተኛ ዝግጅት ትግሉን እንዲቀጥልም  ጥሪ አቅርቧል። በዚሁ መግለጫ መሠረት በትግራይና ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም የሃገር መከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ ታግዷል።ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም የአየር በረራም ተከልክሏል።ክልከላውን በሚጥስ ላይም ተመጣጣኝ  እርምጃ እንደሚወሰድበትም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።በትግራይ የትራንስፖርት አገልግሎትም አይኖርም።  
ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ