1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙሉጌታ አየነ

ዓርብ፣ የካቲት 20 2012

ዎርልድ ፕረስ ፎቶ በጎርጎሮሲያኑ 2020 ለአመቱ ምርጥ ፎቶግራፍ አንሺነት ከአጫቸው የፎቶ ጋዜጠኞች መካከል ሙሉጌታ አየነ አንዱ ነው። ኢትዮጵያዊው ፎቶ አንሽ በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ በሶስት ዘርፎች ታጭቷል።

https://p.dw.com/p/3YXV5
Mulugeta Ayana World Press Photo Kandidat
ምስል privat

ሙሉጌታ አየነ

ሙሉጌታ አየነ ካለፉት አምስት አመታት አንስቶ አሶሽዬትድ ፕሬስ ለተባለዉ ዜና አገልግሎች የፎቶግራፍ ወኪል ሆኖ ያገለግላል። ወጣቱ በፎቶ ስራዎቹ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሽልማቶች ያገኘ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የዎርልድ ፕረስ ፎቶ የዓመቱ ምርጥ የፕረስ ፎቶ አንሺዎች እጩ ሆኗል።ሙሉጌታ የታጨባቸው ፎቶዎች ባለፈዉ ዓመት መጋቢት ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ሰለባ ቤተሰቦች አደጋው የደረሰበት ቦታ ሆነው ሀዘናቸውን ሲገልፁ የሚያሳይ ነው። «በሆነው ነገር የተነሳ የሰራሁት ፕሮጀክት የሚያስደስት ባይሆንም በመታጨቴ በጣም ነው ደስ ያለኝ።» ይላል ሙሉጌታ። ወጣቱ የታጨባቸው ፎቶዎች የሰው ልጅን ድንጋጤ ፣ እምባ እና መራራ ሀዘን በቦታው ላልነበረ ሰው፣ ያለ ብዙ ማብራሪያ ይገልፃሉ። ሙሉጌታ ደግሞ በስፍራው የነበረውን ስሜት ሲገልፅ « ለእኛም እጅግ ስሜት የሚነካ ነበር። ስፍራው ትልቅ የሆነ አይሮፕላን የወደቀበት ነው። ግን ምንም ነገር የማይታይበት እና የተሰባበሩ ትናንሽ ነገሮች ብቻ የሚታይበት ነበር። እና ልብ የሚሰብር እና እኛንም ያስለቀሰ ነበር።»
ይሄው መጋቢት አንድ ቀን 2011 ዓ ም  ወደ ናይሮቢ ለመብረር ከአዲስ አበባ እንደተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አይሮፕላን ውስጥ  የ35 ሃገራት ዜጎች ተሳፍረው ነበር። በአደጋው የአውሮፕላኑን 8 ሠራተኞችን ጨምሮ የ 157 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። ሙሉጌታ ብዙ ሰዎች የታደሙበት በርካታ ሀገሪቷ ላይ የተከናወኑ እንደ ሰልፍ እና ክብረ በዓላትን የመሳሰሉ ዝግጅቶችን  በፎቶ አስደግፎ የዘገበ ቢሆንም ይሄኛው የፎቶ ዘገባዎቹ እስካሁን ከሰራቸው ሁሉ  ራሱን አግልሎ ስራው ላይ ብቻ ማተኮር ያልቻለበት እንደነበር ይናገራል። « እኔ ራሴ ዲፕረሽን ውስጥ ገብቼ ነበር። በጣም ስሜት የሚነካ ነበር። የደረሰው አደጋ ቀላል የሚባል አልነበረም። እና እየተፈታተነኝም ቢሆን ሰዎች ሀዘናቸውን ሲገልፁ ስሜታቸውን በማይነካ መልኩ ፊታቸው ቀርቤ ሳይሆን ቴሌ ሌንስ ተጠቅሜ ነው የነበረውን ነገር ለማንሳት የቻልኩት።»

Untersuchungsbericht zum Boeing-Absturz in Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene
World Press Photo nominees Äthiopien Flug ET302
ሙሉጌታ ለዎርልድ ፕረስ ፎቶ ካቀረባቸው ፎቶዎች መካከል ይሄኛው ይገኝበታል።ምስል Reuters/M.Ayene

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ሙሉጌታ በዘንድሮው የዎርልድ ፕረስ ፎቶ ሶስት ዘርፎች ነው የታጨው። ከተፎካካሪዎቹ ስራዎች መካከል የአውስትራሊያ የደን ቃጠሎ፣ የባሀማስ አውሎ ንፋስ አደጋ እና ናይሮቢ በሚገኝ ሆቴል ላይ አሸባብ የሽብር ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የፀጥታ ኃይላት ሰዎችን ሲያሸሹ የነበረውን ሁኔታ የሚሳዩ ይገኙበታል። የዎርልድ ፕረስ ፎቶ ውድድር አሸናፊዎች በጎርጎሮሲያኑ ሚያዚያ 16 ይፋ ይሆናሉ። ዎርልድ ፕረስ ፎቶ በብዛት እጩ የሚያደርጋቸው ወይም የሚያሸንፉት ፎቶ አንሺዎች ምዕራባዊያን ናቸው በመባል ይተቻል። ሙሉጌታ ለሱም ይሆን ለሌሎች ከአህጉሩ ለመጡ የፎቶ ዘገባ ባለሙያዎች የእሱ መታጨት ምናልባትም ደግሞ አሸናፊ መሆን  « አዲስ ለሚመጡም ይሁን አሁን ላሉ ፎቶግራፈሮች ሞራል የሚሰጥ ይመስለኛል» ይላል የ 35 ዓመቱ የፎቶ ጋዜጠኛ እና የዓመቱ ምርጥ የፕረስ ፎቶዎች እጩ ሙሉጌታ አየነ።  ሌላው ሙሉጌታ በአሁኑ ሰዓት እየሰራ የሚገኘው ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያሉ ለውጦችን የሚያሳይበት የፎቶ ዘገባ ነው። 

ልደት አበበ 

ነጋሽ መሐመድ