1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2018 አበይት የዓለም ክንዉኖች

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2011

እስካሁን አሸናፊ ካለ የሶሪያ መንግሥት ነዉ።ግልፅ አሸናፊ ኖረም አልኖረ፤ 12 አማፂ ቡድናትን አስቀድማ፣ በርካታ ኃያል-ሐብታም መንግሥታትን አስከትላ በ2014 በቀጥታ የዘመተችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ተረጂ፤ ተከታዮችዋን እንደማገደች ፕሬዝደንቷ  ዉጊያ አበቃ አሉ።

https://p.dw.com/p/3ApLs
Singapur Gipfel Kim Jong Un Donald Trump
ምስል Reuters/A. Wallace

የዓለም ፖለቲካ በ2018

ሰዉ የዓየር ፀበያን መለካት ከጀመረ 140 ዓመት ደፈነ።ምድር፣ አዋቂዎች እንዳሉት እንደ 2018 ሞቃ፣ደርቃ፣ ነዳ አታዉቅም።ኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ እሳት እና መዓት በማዉረድ የሞቀዉን ዓየር ለማጋም ሲዛዛቱ የነበሩት የዋሽግተን እና የፒዮንግያንግ መሪዎች እንደወዳጅ መጨባበጣቸዉ  ላፍትም ቢሆን እፎይታ ነዉ።የቤጂንግ ዋሽግተን የንግድ ጦርነት፤ የብራስልስ፣ለንድን-ዋሽግተን መሪዎች፣ ሞስኮን ለመቅጣት-አንድ እየሆኑ፤ ሰባ ዓመት የዘለቀ አንድነታቸን ማፍረሳቸዉ ግን እፎይታ-ተስፋዉን አደብዝዞታል።ፍልስጤምና እስራኤሎች ለመገዳደል ዛር-ቆሌያቸዉ ደም እንደገበሩ ሰባ ዓመት ደፈኑ።ሶሪያ እንደወደመች፣ የመን የእልቂት ፍጅት አክሊል እንደደፋች፤ የሪያድ ገዢዎች በርካሽ ወንጀል ተጠርጠርጥረዉ እንደረከሱ፣2018ን ሊሰናበቱ ነዉ።ከአዉሮጳ እና አፍሪቃ ዉጪ ባለዉ ዓለም የተከናወኑ ዓበይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ቃኝን 2018ን እንሸኘዉ።

2018 ያኔ ባዲስነቱ የመጀመሪያ ወሩን አጋመሰ።ጥር።ወዳጆች እንደጠላት የሚዋጉ-የሚያዋጉበት፣ ጠላቶች እንደ ወዳጅ የሚተባበሩበት የሶሪያ ጦርነት ለግራ-አጋቢዉ የኃይል አሰላለፍ ተጨማሪ አብነት አሳየ።ቱርክ የዩናይትድ ስቴትስ ስልታዊ ወዳጅ፣ የኔቶ ነባር አባል ናት።YPG በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የሶሪያ ኩርዶች አማፂ ቡድን የደማስቆ መንግሥትንም፣ የቱርክንም ይወጋል።ለቱርክ አሻባሪ ነዉ።ዩናይትድ ስቴት ግን YPGን ታስታጥቃለች።የቱርክ መሪዎች ዋሽግተኖችን ሲያባብሉ፣ ሲለማመጡ፣ ሲያስታምሙም ነበር።የሰማቸዉ የለም።

Bildergalerie Jahresrückblick 2018
ምስል Reuters/Korea Summit Press Pool

ጥር 20።ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን ትዕግስታቸዉ አለቀ።ድንበር ላይ የሰፈረ ጦራቸዉን ቀጥል አሉ።ተጨማሪ ዉጊያ።እስከ መቼ? አይታወቅም።የሶሪያ ግን  ቦምብ ሚሳዬል እያረሳት-እስከሬን እንደተመረተባት፣ ሚያዚያ ስምንት አለ።ሌላ ጥፋት።

የአማፂያን የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ ዶማ ከተማ ላይ የተረጨ መርዛማ ኬሚካል 70 ሰዉ ገደለ።መርዙን የረጨዉ ወገን በዉል አልታወቀም።ምዕራባዉያን መንግሥታት ግን የሶሪያ መንግስትን ለመወነጀል፣መረጃ፣ ምስክር፣ መርማሪ፤ ዳኛም አላስፈለጋቸዉም።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ እና ፈረሳይ ከሳሽም፣ ዳኛም፣ ፖሊስም ሆነዉ ዶማ አካባቢ የሠፈረዉን የሶሪያ መንግሥት ጦርን በአዉሮፕላን ቦምብ  ቀጠቀጡት።ብዙ ሰዉ ገደሉ፣ አቆሰሉ፣ በርካታ ንብረት አወደሙ።ሚያዚያ ተጋመሰ።

ከ2011 ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ፤ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ እስራኤል፣ ቱርክ፤ሳዑዲ አረቢያ፤ ቀጠር፤ ዮርዳኖስ፣ አረብ ኤምሬቶች፤ የሌሎችም ኃያል ሐብታም መንግሥታት አስራ-ሁለት የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችን በግልፅ አስታጥቀዋል፤ አሰልጥነዋል፤ከለላ ሰጥተዋልም።

Nordkorea Architektur | Arch of Reunification
ምስል picture-alliance/AP Photo/KCNA

 ከ2014 ጀምሮ ደግሞ ምዕራባዉያን መንግሥታት እና ተባባሪዎቻቸዉ የደማስቆ መንግሥት፣ እና ISISን ለማጥፋት፤ ሩሲያ፣ኢራንና ሒዝቡላሕ የሶሪያ መንግሥትን ለማዳን ያቺን የስልጣኔ ቀንዲል፤ ሥልታዊ፣ ዉብ ሐገርን አዉድመዋታል።

የዓለም ዘመናይ መሳሪያ ካየር፤ ከባሕር፣ ከምድር የተዘረገፈበት፣ ረቂቅ የስለላ ጥበበብ የተቀለጣጠፈበት፤ ምርጥ ጦር የተፋለመበት፣ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር የተረጨበት ጦርነት 368 ሺሕ ሕዝብ ፈጅቷል።ከ7.6 ሚሊዮን በላይ አሰድዷል።5 ሚሊዮን አፈናቅሏል።

እስካሁን አሸናፊ ካለ የሶሪያ መንግሥት ነዉ።ግልፅ አሸናፊ ኖረም አልኖረ፤ 12 አማፂ ቡድናትን አስቀድማ፣ በርካታ ኃያል-ሐብታም መንግሥታትን አስከትላ በ2014 በቀጥታ የዘመተችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ተረጂ፤ ተከታዮችዋን እንደማገደች ፕሬዝደንቷ  ዉጊያ አበቃ አሉ።

«ISISን አሸንፈናል።መተናቸዋል በደንብ መተናቸዋል።የያዙትን ግዛት ተቆጣጥረናል።አሁን ወታደሮቻችን ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱበት ወቅት ነዉ።» ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ታሕሳስ 20።

Pyeongchang 2018 Winter Olympia Kim Jong Un's Schwester Kim
ምስል Getty Images/AFP/P. Semansky

የትራምፕ ዉሳኔ መከላከያ ሚንስትራቸዉን አስቆጥቶ «በቁኝ-በቃዎት»  ሲያሰኝ የምዕራብ አዉሮጳ መንግስታትን አስከፍቷል።አንድ ሰዉ ግን ደስታቸዉን አልሸሸጉም፣ የሶሪያ መንግሥት ደጋፊ የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን።

የዓለም ፖለቲከኞች የሞቃዲሾ ይሁኑ፣ የሮም፣ የአቡጃ ይሁኑ የለንደን፣ የቴልአቪቭ ይባሉ የብራስልስ በየአጋጣሚዉ እንደሚሉት የዘመኑ ዓለም  ትልቅ ስጋት አሸባሪ ቡድናት ናቸዉ።

አንድ ጥናት እንዳረጋገጠዉ ግን ከ1994ቱ የሩዋንዳ እልቂት በስተቀር በየዓመቱ ብዙ ሰዉ የሚያልቀዉ በሸባሪዎች ጥቃት አየደለም።በተፈጥሮ መቅሰፍትም አይደለም።በጦርነትም አይደለም።ግለሰቦች በታጠቁት  ጠመንጃ ነዉ።

በዓመት 250 ሺሕ ሰዉ ይገደላል።ብዙ ሰዉ ከሚያልቅባቸዉ ሐገራት አንደኛዋ ብራዚል ናት።በ2016 43 ሺሕ ሰዉ።ሁለተኛ ዩናይትድ ስቴትስት 37 ሺህ።ለዩናትድ ስቴትስ ዘንድሮም ሐቻምና መሆኑን ዓመቱ በባተ በሁለኛ ወሩ ተረጋገጠ።

ፓርክላንድ፣ ፍሎሪዳ የሚገኘዉ የሜሪጆሪ ስቶንማን ዳግላስ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የቀድሞ ተማሪ ኒኮላስ ክሩዝ አዉቶማቲክ ጠመንጃዉን ታጥቆ ወደ ትምህርት ቤቱ ገበ።የ19ኝ ዓመቱ ወጣት ተማሪ ካስተማሪ ሳይለስ ጥይቱን ያርከፈክፈዉ ያዘ።14 ወጣቶች፣ 3 አዋቂዎች ገድለ።15 አቆሰለ።የካቲት 11 ነበር።

ተደጋጋሚዉ ግድያ ያሰጋቸዉ በብዙ ሺሕ የሚቀጠሩ አሜሪካዉያን ተማሪዎች በጠመንጃ ሽያጭ እና ታጣቂዎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ባደባባይ ሰልፍ ጠየቁ።መጋቢት 14።የሰማቸዉ የለም።

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የ900 የዓለም ከተማ ነዋሪዎች  «ሕይወታችንን  የማዳን ጉዞ» ባሉት የአደባባይ ዘመቻም በጠመንጃ ሺያጭ ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠየቁ።ሰሚ እንጂ አድማጭ አልተገኘም።

Jemen l Huthi-Rebellen in Sanaa
ምስል picture alliance/dpa/H. Al-Ansi

ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ድረስ ከአቅም፣ጉልበት፣ጥንካሬዋ በላይ በዓለም ፖለቲካ  ደምቃ የገነነችዉ ኩባ ድምፅዋን አጥፍታ የካስትሮዎችን የስልሳ ዘመን አገዛዝ አሰናበተች።

የካቲት 24።ለዋሽግተኖች የአፍንጫ ስር አይነቀል መዥገር ሆነዉ ከሐምሳ ዘመን በላይ የኖሩትን የዝነኛ፣ታላቅ ወንድማቸዉን የፊደል ካስትሮን ሥልጣን የወረሱት ራዑል ካስትሮ ሥልጣን «በቃኝ » አሉ።87 ዓመታቸዉ።

ኩባዎች የወደፊት መሪያቸዉን ማንነት ለማወቅ ሲጠባበቁ፤ የቀድሞዋ የኩባ የቅርብ ረዳት የሶቭየት ሕብረት ወረሽ ሩሲያ ነባር መሪዋን ቭላድሚር ፑቲንን ለተጨማሪ ዘመነ-ሥልጣን መረጠች።መጋቢት 18።

ለዩክሬን የሚያዳሉት የምዕራባዉያንና የሩሲያ ዉዝግብ፤ የዩክሬን እና የሩሲያ ግጭት ቁርቁስም ቀጠለ።ለአራተኛ ዓመት።ሚያዚያ 19።ሚጉኤል ማሪዮ ዲያዝ-ካኔል ቤርሙዴስ የኩባ ፕሬዝደንት ሆኑ።

የካቲት።የበረዶ ወር።የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ ደቡብ ኮሪያ በምታስተናግደዉ የክረምት ኦሎሚክ ላይ ከሚወዳደሩ የሰሜን ኮሪያ ስፖርተኞች ጋር የሚወዷቸዉን ታናሽ እሕታቸዉን ኪም ዮ ጆንግን የላኩበት ምክንያት ለስፖርተኞቹም፣ለሩቅ ታዛቢዎችም ሚስጥር ነበር።ስፖርተኞች በረዶ ላይ ሲጫወቱ፣ ሴትዮዋ ከደቡብ ኮሪያ መሪዎች ጋር የሚሉትን ብለዉ ወደ ፒዮንግዮግ ተመለሱ።ከዚያማ የነበረዉ ሁሉ በነበር እየቀረ ዛቻ፣ፉከራ፣ የዉጊያ ዝግጅት፤ዘመቻዉ  ተረስቶ የድርድር ግብዣ ድግሱ ይቀለጣጠፍ ገባ።

Schweden | Friedensgespräche Jemen-Konflikt
ምስል Getty Images/AFP/J. Nackstrand

ሚያዚያ 27። የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄ ኢን ጋር ለመነጋገር ሁለቱን ኮሪያዎች የሚያዋስነዉን ድንበር ተሻገሩ።ኮሪያዎች ለሁለት ከተከፈሉ ከ1953 ወዲሕ የሰሜን ኮሪያ መሪ የደቡብን ግዛት ሲረግጥ ኪም የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ሰኔ-12። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሲንጋፑር ዉስጥ ተገናኝተዉ ተነጋገሩ።«ብዙ ለዉጥ አለ።በዉነቱ በጣም ፈጣን ነዉ።ማንም ሰዉ ሊጠብቀዉ ከሚችለዉ በላይ ነዉ።በእዉነቱ ጥሩ ነዉ።አሁን እንፈርማለን።»አሉ ትራምፕ።

ዛቻ፣ ስድድብ፣ የኑክሌር ዉጊያ ዝግጅቱ በንግግር ድርድር መተካቱ ለሰላም ወዳዱ ዓለም ታላቅ እፎይታ ነዉ።ቀጣይ ሒደቱ ግን ዝም፤ዝም እንዳሰኘ ዘንድሮ አምና ሊሆን ሰዓታት ቀሩት።

መጋቢት፣ ደሐይቱ ግን ጥንታዊቱ፣ታሪካዊቱ፤ ሐገር የመን በሪያድ፤ አቡዳቢ ተባባሪዎች ጦር ምናልባትም በቴሕራን ጠላታቸዉ ጦር መሳሪያ መዉደም፤ ጀግና ኩሩ ሕዝቧ መርገፍ ከጀመሩ  ሰወስተኛ ዓመታቸዉን ደፈነ።

የጦርነቱን አዛዦች ወይም የምዕራብ አስታጣቂዎቻቸዉን «ሐይ» ማለት የማይችለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ መንግሥት ሳይሆኑ «መንግሥት»፣ «መንግሥት ሆነዉ» አማፂ የሚባሉትን ታዛዥ ኃይላት «ተኩስ አቁሙ» እንዳለ፣ ደሐይቱ ሐገር በሟች፣ ረሐብተኛ፣ ብዛት ከዓለም አንደኛነቷን አረጋገጠ።

የመንን ጦርነት በ2015 እንደ መከላከያ ሚንስትር ያዘዙት የሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሠልማን መልካም ፈቃዳቸዉ ሆኖ ከ1983 ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ የሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ በፊልም ቤት አዳራሽ ፊልም ማየት ያዘ።ሚያዚያ 18።

የየመንን እልቂት ፍጅት ለዓብይ ርዕሥነት ያልመረጠዉ የምዕራብ ጋዜጠኛ በፊልም ቤት መከፈበት ሰበብ ወጣቱን አልጋወራሽ «ለዉጥ አራማጅ» እያለ ሲያንቆለጳጵስ፣ ሰዉዬዉ ለሐገራቸዉ ዕዉቅ ጋዜጠኛ የደገሱት ጥቅምት ላይ ፈጋ።

ሳዑዲ አረቢያዊዉ የዋሽግተን ፖስት አምደኛ ጀማል ካሾጂ ኢስታንቡል ቱርክ ከሚገኘዉ የሐገሩ ቆንስላ መረጃ ለመዉሰድ ገብቶ-አስከሬኑ እንኳን ለመረጃ እንዳይገኝ ሆኖ ተገደለ።

ዓለምም ጋዜጠኛ-ከሐገር መሪ፣ደራሲ፣ ከእንደራሴ-ከፖለቲከኛ፣ከመብት ተሟጋች ሳይለይ «ጀማል፣ጀማል» ይል ገባ። እስካሁን የተሰበሰቡ መረጃዎች ሁሉ ደግ መካሪ፣ አዛዥ ናዛዥም የሌላቸዉ የ33ት ዓመቱ አልጋወራሽ  መሐመድ ቢን ሠልማን ጋዜጠኛዉን ማስገደላቸዉን እንደሚጠቁሙ አብዛኛዉ ዓለም አምኗል፣ አዉግዟልም።

Kuba Havanna - ALBA Gipfel: Miguel Diaz Canel , Nicolas Maduro und Raul Castro
ምስል Getty Images/AFP/Y. Lage

ጀርመንን የመሳሰሉ ጠንካራ መንግስታትም በሳዑዲ አረቢያ ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ጥለዋል።በአልጋወራሽ ላይ ቀጥታ እና ጠንካራ ዉግዘት የተሰማዉ ግን ከአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች ወይም ሴናተሮች ነበር።ታሕሳስ አጋማሽ።«የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት፣ለጀማል ካሾጂ ግድያ የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ተጠያቂ መሆናቸዉን በአንድ ድምፅ አፅድቋል።»

ሴኔቱ ዩናይትድ ስቴትስ ሳዑዲ አረቢያን ማስታጠቋን እንድታቆም ጠይቋልም።የጀማል ካሾጂ ግድያ ለየመኖች በተለይ ለሁዴይዳ ከተማ ሳይደግስ አይጣላም ዓይነት ነዉ የሆነዉ።ሰወስት ዓመት ተመንፈቅ ዓለምን ንቀዉ የመንን ሲያወድሙ የነበሩት የሪያድ፣አቡዳቢ እና የተከታዮቻቸዉ ገዢዎች ከአብዛኛዉ ዓለም ግፊቱ ሲያይልባቸዉ የመኖች እንዲታረቁ ወሰኑ።የመኖችም ቢያንስ የወደብ ከተማይቱን ጦርነት ለማቆም እና ለወደፊቱ ለመደራደር ተስማሙ።

ሳዑዲ አረቢያዎች ከ1983 ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካኖችን ልብወለድ ፊልም ሪያድ ዉስጥ ሲኮሞክሙ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያምን እዉነተኛ ያሉትን «ፊልም» ለዓለም አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ ጥሩ ተዋኝ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያብራሩት ፊልም የእስራኤልም፤ የሳዑዲ አረቢያም፤ የዩናይትድ ስቴትስም ቀንደኛ ጠላት የምትባለዉ ኢራን፣ ከኃላን መንግስታት ጋር ያደረገችዉን የኑክሌር ስምምነት መጣስዋን ያሳያል ያሉትን ሰነድ ነዉ።ሚያዚያ አበቃ።መዘዙ ግን ቀጠለ

ኔታንያሁ ኢራንን የሚያጋልጥ አንድ መቶ ሺሕ ሰነድ መሰብሰባቸዉን ለዓለም በነገሩ በሳምንቱ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገዉን ዓለም አቀፍ የኑክሌር ስምምነት ለማፍረስ ዛቱ።ዝተዉ አልቀሩም።ነሐሴ፣ ስምምነቱን አፈረሱ።በኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ ጣሉም።

ዓመቱ ለኢራን መጥፎ ነበር።የካቲት፣ የመንገደኞች አዉሮፕላን ተከስክሶ 65 ሰዉ ተገደለባት።ነሐሴ፣ ማዕቀብ ዳግም ተጣለባት።መስከረም፣ ነዳጅ ዘይት የጫነ መርከቧ ጋየ።ነዳጁ 20 ሚሊዮን ዶላር ያወጣ ነበር።መስከረም 22።አሕቫዝ በተባለችዉ የኢራን ከተማ ወታደራዊ ትርዒት ያሳዩ በነበሩ ወታደሮች ላይ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተዉ 29 ሰዎች ተገደሉ።

«የሐሰት ወታደራዊ መለዮ የለበሱ ታጣቃዊች ጓዶቻችንን እያጠቁ መሆኑን ድንገት ተረዳን።ወዲያዉ ሴቶች እና ሕፃናት በነበሩበት አካባቢ ጥይታቸዉን ያርከፈክፉት ገቡ።» ቆስሎ የተረፈ ወታደር።

Bildkombo Saudi-Arabien | Jamal Khashoggi & Mohammed bin Salman

ዓለም፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የገጠሙትን አዲስ ዉዝግብ፤ የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂን ግድያ፤ ትራምፕ በቻይና፣ በአዉሮጳ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በካናዳ ላይ የከፈቱትን የንግድ ጦርነትን መዘዝ እየበጠሰ ሲቀጥል፣ ብራዚል ላይ የትራምፕ አምሳያ የፕሬዝደንትነቱን በትረ-ሥልጣን ጨበጡ።

ያይር ቦልሶናሮ፤ ዘና- ለቀቅ-ቀበጥ የሚባልባትን ትልቅ ደቡብ አሜሪካዊትን ሐገር እንደ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኛ ጨምድደዉ እንዲገዙ ሕዝባቸዉ በ55 ከመቶ ድምፅ መረጣቸዉ።ጥቅምት 28።

                        

«ከሁለት ሰዓት በፊት የሕብረ ብሔራት ጦር ኢራቅ እና ኩዌት የሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎችን መደብደብ ጀምረዋል።ድብደባዉ አሁን እየተናገርኩም ቀጥሏል።እግረኛ ጦር አልተካፈለም።ይህ ግጭት የጀመረዉ የኢራቁ አምባገነን ደካማይቱን ትንሽ ጎረቤቱን ሲወር ነበር።»

ጥር 16 1991። ጆርጅ ሔርበርት ዎከር ቡሽ። 41ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ።ሞቱ።ሕዳር 30።

ተፈጥሮን መጠበቅ ለተፈጥሮ አይጠቅምም የሚል መሪ የመረጡት አሜሪካዉያን የቀድሞ መሪያቸዉን ለመቅበር ሲዘጋጁ፣የተፈጥሮን ደሕንነት ለመጠበቅ የሚታገሉ ባለሙያዎች እና ባለሥልጣናት ካስትሶቪትስ ፖላንድ ዉስጥ ተሰበሰቡ።

Tunesien Proteste gegen Besuch Saudi Kronprinz Mohammed bin Salman
ምስል Reuters/Z. Souissi

ተሰብሳቢዎች ተፈጥሮን ለመጠበቅ መስማማታቸዉን ባስታወቁ በሰወስተኛዉ ሳምንት ግን ተፈጥሮ ቆጥቋጭ ለበቋን እንደገና ኢንዶኔዢያ ላይ አሳረፈች።ሱናሚ።ታሕሳስ 22።450 ሰዉ ሞተ።ብዙ ሺሕ ተፈናቀለ።2018ም አዲዮስ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ