1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የሴቶች ቀን

ዓርብ፣ የካቲት 27 2012

ኢትዮጵያው ውስጥ በሚመጣው እሁድ ማለትም የካቲት 29 ቀን  የዓለም የሴቶች ቀን  ይከበራል። የኢትዮጵያ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የዘንድሮው መሪ ቃል ደግሞ «የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሠረት ነው » የሚል ነው።

https://p.dw.com/p/3Yvcf
Frauentag
ምስል picture-alliance/ZB/J. Wolf

በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው መጋቢት 8 ቀን የዓለም የሴቶች ቀን ይከበራል። ከዚህ የሴቶች ቀን ጋር በተያያዘ የመብት እና የእኩልነት ጥያቄዎች አብረው ይነሳሉ። አንድ የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያመላክተው በዓለም ላይ 143 ሃገራት የሴቶች እና ወንዶች እኩልነትን በሕገ መንግሥታቸው ላይ ያሰፈሩ ቢሆንም ስምንት ሃገራት ማለትም ቤልጄም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ሲውዲን፣ አይስላንድ፣ ሉክስንበርግ፤ ፈረንሳይ እና ሊትዌኒያ ብቻ ናቸው የሴቶች እና የወንዶች እኩልነት መብትን የሚያረጋግጡት። ጥናቱ ትኩረቱን ያደረገውም ሥራን፣ የቤተሰብ፣ የንብረት ባለቤትነት፣ የጡረታን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ላይ ተመርኩዞ ነው።  የሚያሳዝነው ነገር ግን እስካሁን በየትኛውም ሀገር የወንድ እና የሴቶች እኩልነት ሙሉ በሙሉ አለመረጋገጡን ነው የግሎባል ጀንደር ጋፕ መዘርዝር የሚጠቁመው። 
 የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የሴቶች ቀን መሪ ቃል "I am Generation Equality" ወይም «የእኩልነት ትውልድ ነኝ» የሚል ነው። በርግጥ አዲሱ ወይም የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ እኩልነቱ ተረጋግጧል ብሎ ያምናል? DW ያነጋገራቸው ወጣቶች እንደሚሉት በፊት ከነበረው ሁኔታ አሁን ላይ የተሻለ ነገር ነው ያለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከግንዛቤ ሁኔታ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው የሚለው አንድ ወጣት ወደ ተግባር ሲመጣ ብዙ ተግዳሮቾች አሉ ይላል። « በተለይ ባለሁበት ባህር ዳር አካባቢ ገጠር የሚገኙ ሴቶች ላይ የወንዶች ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው።» ይላል።  ወንዶ ገነት የምትኖረው ወጣትም ይህን ትጋራለች « አንዳንድ አካባቢ ሴት ወጣቶች ሰርተው እንዲለወጡ አያደርጓቸውም የቤት እመቤት ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ነው የሚፈልጉት» 

Äthiopien Frau mit Teff-Getreide
ምስል picture-alliance/blickwinkel/G. Fischer

ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በኢትዮጵያ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ናቸው። የሚሰሩበት መሥሪያ ቤት የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ቀንን ያከበረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚከበርበት ዕለት አራት ቀን ቀደም ብሎ ነበር።  « በዓሉን በሁለት መልክ ነው ያከበርነው አንዱ ጥቃት ደርሶባቸው በተለያዩ ማዕከል ውስጥ ላሉ ሁለት ተቋማት ድጋፍ እንዲሰጡ በማድረግ ሲሆን ሌላው ደግሞ  የመድረክ ውይይት በማካሄድ ነበር። » ይላሉ  የአለም የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ 109ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ እየተከበረ እንደሆነ የሚናገሩት ሚኒስትር ዴታ። የተለያዩ የሃገሪቱ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ይኸው ውይይት ላይ አሁንም ለሴቶች ፈተና ናቸው ተብለው የተነሱት ጉዳዮች ወይዘሮ ስመኝ  እንደሚሉት ሴቶች ላይ የሚፈፀመውት የተለያዩ ጥቃቶች ናቸው።
የዘንድሮው የሴቶች ቀን መሪ ቃል  «የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሠረት ነው» የሚል ነው። ሚኒስቴሩ ይህንን ርዕስ የመረጠበትንም ምክንያት በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ነው ። « በሀገራችን በተለያዩ ምክንያት ግጭቶች አሉ። በዚህ ደግሞ ዋንኛ ተጠቂ እየሆኑ ያሉት ሴቶች እና ህፃናት ናቸው» ይላሉ ወይዘሮ ስመኝ።  መሥሪያ ቤታቸው  ጥቃት ከሚለው አንዱም የታገቱት ሴት ተማሪዎችን ጉዳይ ነው። « በሴቶች ላይ እንደዚህ አይነት ጥቃቶች የሚደርሱ ከሆነ የሚጎዳው አጠቃላይ ማህበረሰቡ ነው። »

USA Demonstration Internationaler Frauentag in Miami
ምስል Getty Images/J. Raedler

ሌላው የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ቀንን በሚመለከት የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ትኩረት እንዲሰጥበት ያለው ጉዳይ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን በሚመለከት ነው። 
«  የሴቶች የፖለቲካ ለውጥን በሚመለከት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያለው» የሚሉት ወይዘሮ ስመኝ «በመጪው ምርጫ ምን ያህሉ ፓርቲ ሴቶችን ወደ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማምጣት ጥረት ያደርጋል» የሚለው እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

ልደት አበበ 

ሸዋዬ ለገሠ