1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የምግብ ርዳታ ድርጅት ለጎርፍ ጎዳተኞች ተጨማሪ 250 ሺ ይሮ ሰጠ

ማክሰኞ፣ መስከረም 12 2013

በኢትዮጵያ በጎርፍ የተጎዱ ሰዎች የሚበላ ምግብ የሚሰጣቸዉ አልያም ካሉበት ከዉኃ ዉስጥ የሚያወጣቸዉ ሲጠብቁ ከሳምንት በላይ እንደሆናቸዉ የዓለም የምግብ ርዳታ ድርጅት ገለፀ። በምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለዉ የጎርፍ አደጋ ለደረሰዉ ችግር የዓለም የምግብ ርዳታ ድርጅት ተጨማሪ 250 ሺህ ይሮ አስቸኳይ ርዳታ ማቅረቡን ገለፆአል።

https://p.dw.com/p/3irBW
Logo der Welthungerhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/Oliver Berg

 

በምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለዉ የጎርፍ አደጋ ለደረሰዉ ችግር የዓለም የምግብ ርዳታ ድርጅት ተጨማሪ 250 ሺህ ይሮ አስቸኳይ ርዳታ ማቅረቡን ገለፀ። የዓለሙ የምግብ ርዳታ ድርጅት ዛሬ በሰጠዉ መግለጫ፤ በምስራቅ አፍሪቃ ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለዉ የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ፤ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ሃገራት ብቻ 2,5 ሚሊዮን ሕዝብ መጠለያ አጥቶአል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በእነዚሁ ሦስት የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት በሚቀጥሉት ቀናት ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጥል የአየርት ትንበያ ባለሞያዎች ከወዲሁ እያስጠነቀቁ ነዉ። እንደ ርዳታ ድርጅቱ ገለፃ በሃገራቱ የአንበጣ መንጋን እና የኮሮና ስርጭትን ለመግታት በሚደረግ ጥንቃቄ ምክንያት ዜጎች ለአደጋ ጊዜ ያስቀመጡት እህል ተሟጥዋል ብሎአል። በኢትዮጵያ የተከሰተዉ እጅግ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እስከዛሬ ያልታየ መሆኑን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ማትያስ ሽፔት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በጎርፍ የተመቱ አካባቢዎች የእርሻ እና የግጦሽ ቦታዎች ወድመዋል፣ ብዙ እንስሳትም በጎርፍ ተወስደዋል አልያም ሰጥመዋል፤ በአንዳንድ መንደሮችም ነዋሪዎች ምግብ እና ከቦታዉ የሚያወጣቸዉ ሲጠባበቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆንዋቸዋል ብለዋል።

 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ