1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዋና ዋና ዜናዎች

ሐሙስ፣ የካቲት 18 2013

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ-ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ችሎት በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥራ የነበረውን ላምሮት ከማልን በነጻ አሰናበተ። የተቀሩትን ሦስቱን ደግሞ ራሳችሁን ተከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/3pvvx
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

የየካቲት 18/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ-ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ችሎት በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥራ የነበረውን ላምሮት ከማልን በነጻ አሰናበተ። የተቀሩትን ሦስቱን ደግሞ ራሳችሁን ተከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ራሳችሁን ተከላከሉ ያላቸው ተከሳሾች ጥላዬ ያሚ፣ ከበደ ገመቹ እና አብዲ ዓለማየሁ የተባሉት ናቸው። ከዚህ ቀደም ኅዳር 23 እና 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለተከታታይ ሁለት ቀናት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የሰማው ፍርድ ቤቱ የምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ ባስቻለው መሠረት ውሳኔውን ማሳለፉ ተገልጿል። አንደኛ ተከሳሽ ጥላዬ ያሚ በአቃቤ ሕግ የተከሰሰበት ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ ሦስትን በመተላለፍ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የቀረቡበት ማስረጃዎች በቂ ሆኖ ማግኘቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ከ1ኛ ተከሳሽ ጥላዬ ያሚ «እንዝረፍ» በሚል የቀረበለት የዝርፊያ ወንጀል ለመፈጸም ተስማምቶ በወንጀሉ የተሳተፈ በመሆኑ ክሱ በ1996 በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሠረት እንዲታይ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። ሦስተኛው ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ወንጀሉ መፈጸሙን ለፍትህ አካላት ባለማሳወቁ በአንቀጽ 443/1 እንዲጠየቅ በማለት የተከሰሰበት የወንጀል አንቀጽ እንዲሻሻል ታዟል፡፡ የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበው በአራተኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል ላይ የቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ በቂ ሆኖ አላገኘሁትም ሲል ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቷታል። ፖሊስም እንዲለቃት ትዕዛዝ ሰጥቷል።  

በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ በቀለ ገርባ የህክምና ጥያቄ ጋር ተያይዞ የፍርድ ቤት ውሳኔን አላከበሩም ያላቸውን የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችን ጠርቶ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ በዛሬ ውሎው የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ በቀለ ገርባ ከፍርድ ቤቱ የተሰጣቸው በግል ሆስፒታል የመታከም ፈቃድ ሳይፈጸም በመቅረቱ  የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ኮሚሽነር ግርማ አደሬን በችሎቱ ጠርቶ ጠይቋል። ከተከሳሾች ጠበቆች አንዱ የሆኑት ጠበቃ ከድር ቡሎ ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት ባለፈው ማክሰኞ በችሎቱ ባለመቅረባቸው በፖሊስ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የወጣባቸው ረዳት ኮሚሽነሩ ምክኒያታቸውን እንዲያስረዱ በችሎቱ ተጠይቀው የጸጥታ ስጋትን በምላሽነት ሰጥተዋል፡፡«ረዳት ኮሚሽነር ግርማ አደሬ የፌዴራል ማረሚያ ቤት የከፍተና ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ዳዬሬክተር ችሎቱ ባዘዘው መሰረት ቀርበዋል። ምክንያቱ ደግሞ በእነ አቶ ጀዋር መሐመድ ህክምና ላይ በአቃቤ ሕግ የቀረበውን ውሳኔ አያይዘው ነው ያቀረቡት በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ ተከሳሾችን ከፍርድ ቤት አጅቦ በሚመላለስበት ጊዜ ስጋቱ በተደጋጋሚ የሚታይ እና እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳያጋጥም ለመከላከል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።»የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበው የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ በቀለ ገርባን ከሃኪማቸው ጋር ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል እያቀኑ በመሃል ያለፈቃዳቸው ወደ መንግሥት ሆስፒታል ሲወሰዱ ቡድኑን የመሩት ሁለት የማረሚያ ቤቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ከከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ዳይረክተሩ ጋር ለተጨማሪ ማብራሪያ ለየካቲት 22 ቀን በተያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተወስኗል።

ኤርትራ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠየቀች። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ መልዕክተኛቸውን ወደ ካርቱም ልከዋል። የሱዳኑ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መወሰናቸውን  የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነህ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል። መሪዎቹ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር እና ለቀጠናዊ ትብብር ለመሥራት ከውሳኔ መድረሳቸውንም ሚንስትሩ ገልጸዋል።  በኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኦስማን ሳሌህ የተመራው የልዑካን ቡድኑ ትናንት ረቡዕ ነበር በካርቱም ከሽግግር መንግሥቱ መሪዎች ጋር የተወያየው።

ሴራሊዮን ቻይና ሰራሹን የኮሮና ተህዋሲ መከላከያ ክትባት 200,000 ብልቃጦች ዛሬ እንደምትረከብ የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ክትባቱን ከቻይና መንግሥት በተደረገላት ድጋፍ ነው ያገኘችው። ቤጂንግ 201 ,600 መርፌ እና ስሪንጆችንም ጨምራ መስጠቷን ነው ሚንስቴሩ የገለጸው። ሴራሊዮን ከተቀሩት የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ወረርሽኙ እንዳልበረታባት ሲነገር፤ ተህዋሲው በሀገሪቱ ከተከሰተ ካለፈው ዓመት የመጋቢት ወር ጀምሮ  3,880 ሰዎች ሲያዙ 79 ሰዎች ደግሞ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሲኖፋርም የኮሮና ክትባትን ያበለጸጉት ይፋ እንዳደረጉት ክትባቱ 79 በመቶ ውጤታማ ነው። ክትባቱ ከሴራሊዮን ውጭ ሲሸልስ፣ ዚምቧብዌ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሴኔጋልን ጨምሮ በሌሎች ሃገራትም ሥራ ላይ መዋሉን የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል።

የአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት በኮሮና ሳቢያ ለተራዘመ ጊዜ በህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች እንክብካቤ እንዲያደርጉ የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮጳ ቢሮ አሳሰበ። በተሕዋሲው ከሚያዙ ከአስር ሰዎች አንዱ በኮሮና ምክንያት ለ12 እና ከዚያ በላይ ሳምንታት ለተራዘመ ጊዜ ለጠና ሕመም እንደሚጋለጡ መቀመጫውን ኮፐንሀገን ያደረገው ተቋም አመልክቷል። በዚህም ሃገራት መረጃዎችን ወጥነት ባለው መንገድ አጠናክረው በተራዘመ የኮቪድ ህመም ወቅት አልያም በድህረ ኮቪድ ለታካሚዎች የተራዘመ የስቅየት ጊዜ መፍትሄ ሊሆኑ የሚገባቸውን እርምጃዎችን እንዲወስዱ ነው የተጠየቀው። በተጨማሪም ታማሚዎች እና ቤተሰቦቻቸው በበሽታው ምክንያት ለሌላ የስነልቦና ቀውስ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊጋለጡ ስለሚችሉ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል። በአውሮጳ 38 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በተሕዋሲው መያዛቸው ሲረጋገጥ ፣ 850 ሰዎች ደግሞ በኮሮና ሳብያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮብኛል ያሉት የአርሜኒያው ጠቅላይ ሚንስትር ደጋፊዎቻቸው በመዲናዋ አደባባይ እንዲሰባሰቡ ጠየቁ። በአርሜኒያ በአካባቢያዊ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ የተነገረለት የካውካስ ሪፐብሊክ  ጠቅላይ ሚንስትር ኒኮል ፓሽንያን ከመንበረ ሥልጣናቸው እንዲለቁ መጠየቁ ተሰምቷል። ቀደም ሲል የሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ፓሽንያን እና ካቢኔያቸው ሥልጣናቸውን ይልቀቁ ብለዋል። የጀርመን ዜና ምንጭ እንደዘገበው ወታደሮቹ ጠቅላይ ሚንስትሩን ከዚህ በኋላ የሚሰጡት ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ብለዋቸዋል። ነገር ግን በድህረ የአዛርባጃን ጦርነት በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ የተነገረላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ አርሜንያውያን ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ አይፈቅዱም ብለዋል። የወታደሮችን እንቅስቃሴ ተከትሎም ዋና አዛዡን ከሥልጣን ማንሳታቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል። በቅርቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠይቁ ነበር ። ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባይቀበሉትም። ከባለፈው መስከረም ጀምሮ ለአንድ ወር ከሁለት ሳምንት ገደማ  በናጎሮ ካራባህ ይገባኛል ከአዛርባጃን ጋር በተደረገው ጦርነት በአጠቃላይ ከ4,700 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።