1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

የዓለም አቀፍ የህዋ ሳይንስ ውድድር አሸናፊዎች

ዓርብ፣ ነሐሴ 1 2012

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የህዋ ሳይንስ ውድድር ላይ ተካፍለው ለወርቅ እና ነሐስ ሽልማት የበቁ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው። ስለ ውድድሩ፣ ተሞክሯቸው እና ፈተናውን ለመውሰድ የገጠማቸው ትልቁን ፈተና አጫውተውናል። 

https://p.dw.com/p/3gaZk
Äthiopien | Award GewinnerIn | Collage
ምስል privat

የወርቅና የነሐስ የክብር ሽልማት ያገኙት እመቤትና በትረአሮን

በዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ(ሥነ ፈለክ) እና አስትሮፊዚክስ ውድድሮች የተሳተፈው እና የወርቅ የክብር ሽልማት ያገኘው ወጣት በትረአሮን ደረጀ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዮንቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው። በሶስት ዙር የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ውድድር ከ 40 ጥያቄዎች 32 ቱን በመመለስ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ እና ሶስት በመቶ ያክሉ ተወዳዳሪዎች አንዱ ሊሆን ችሏል። ውድድሩ «በህዋ ሳይንስ ላይ ያተኮረ እና የተለያዩ ሀሳብ እና ጥናቶችን በማቅረብ ተማሪዎች እንዴት እንደሚገነዘቡት በመጠየቅ ያወዳደረ ነው» ሲል ይገልፀዋል። በትረአሮን የወርቅ የክብር ሽልማት ማግኘቱም ሀገሩ ኢትዮጵያ በሥነ ፈለክ እና አስትሮፊዚክስ መዘርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትካተት ማድረጉን ይናገራል። 
እመቤት ሙሀባው በዚሁ ዓለም አቀፍ ውድድር የተሳቸፈች ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ተማሪ ናት። እሷ ደግሞ የነሐስ ተሸላሚ ሆናለች። የ 20 ዓመቷ ወጣት በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዮንቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የኤክትሮ ሜካኒካል ተማሪ ናት። በዚህ ውድድር ስትሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነበር።  « ሀገሬን በሶስተኛ ደረጃ በማስቀመጤ በጣም ደስ ብሎኛል። » ትላለች። ሌላም ደስ ያስባላት ነገር አለ። « ሴቶች ብዙውን ጊዜ ሳይንስ ላይ ሆኖ የህክምናው ሙያ ላይ ነው የሚያተኩሩት ነገር ግን እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል ስነ ፈለክም ይሁን አስትሮፊዚክስ ዘርፎች ላይ እንችላለን የሚለውን በትንሹም ቢሆን ማሳየቴ አኩርቶኛል። »
እመቤትም ትሁን የ 19 ዓመቱ በትረአሮን ከራሳቸው አልፈው የሀገራቸውን ስም ማስጠራት ችለዋል። ይሁንና ይህ እድል የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎት በመዝጋቱ የተነሳ አምልጧቸው ሁላ ነበር። በትረአሮን  « ፈተናው ባለፈ በሁለተኛው ቀን ኢንተርኔት ተለቀቀ። እኔም ወዲያውኑ ፈተናውን ሀገሪቷ ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ስለነበር ፈተናውን መውሰድ አልቻልኩም። ይህን ፈተና ባለፈው ዓመት ተሳትፌ ማሸነፌን በመግለፅ እንድፈተን እድሉኝ እንዲሰጡኝ ጠየኳቸው እነሱም በ 24 ሰዓታት ውስጥ እንድፈተን ፈቀዱልኝ።»
ምንም እንኳን እመቤት እና በትረአሮን በመጨረሻ ሰዓት ተወዳድረው ከፍተኛ ውጤት ለማግኘት ቢበቁም በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ለፈተናው በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ባለመቻላቸው የገንዘብ ሽልማት እንዳመለጣቸው ገልፀውልናል። ሌላም የ 26 ሺ ዶላር ሽልማት ያለው ውድድር እንዲሁ አመልጧቸዋል። « እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነበርን። በጣም ተዘጋጅተንበት ነበር። ግን በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ፈተናው አምልጦናል።» ትላለች እመቤት።
ዶክተር አለልኝ አስቻለ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዮንቨርስቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳሬክተር  ወይም ዲን ፤ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር እና በዮንቨርስቲው ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበረሰብ ቅርንጫፍ ቢሮ ዋና አስተባባሪ ናቸው። « እንቅስቃሴያቸው በጣም ደስ የሚል ነው። ጥሩ ልጆች ናቸው » ሲሉ እመቤት እና በትረአሮንን ይገልጿቸዋል። ቤተሰባቸው ፣ ዮንቨርስቲው እና መምህራን ተማሪዎቹን በመደገፍ ቢያበረታቱዋቸውም ልጆቹ ይበልጡን በራሳቸው ጥረት ያገኙት ስኬት እንደሆነ ይናገራሉ። ዶክተር አለልኝ አክለውም በኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበረሰብ ላይ ብዙ ስራ መስራት የሚፈልጉ ወጣቶች ስላሉ፣ በመምህራን፣ በዮንቨርስቲ እና መንግስት ደረጃ ብዙ የማበረታቻ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው ገልፀዋል። የእመቤት እና በትረአሮንም የወደፊት ራዕይ ይህንን የሚያጠናክር ነው።

Äthiopien | Award Gewinnerin | Emebet Muhabaw
ምስል privat
Äthiopien | Award Gewinner | Betrearon Dereje Tiruneh
ምስል privat

ልደት አበበ 
ነጋሽ መሀመድ