1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ4.3 በመቶ እንደሚያድግ ተነበየ

ረቡዕ፣ ጥር 18 2014

የዓለም ባንክ ትንበያ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እስከ መጪው ጥር ባለው አንድ አመት በ4.3 በመቶ ያድጋል። በጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም. ዕድገቱ ወደ 6.5 በመቶ ከፍ ይላል። ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በተያዘው አመት እንደሚያገግም ቢተነብይም የጸጥታ መጓደልና ግጭት ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው በዚህ ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርት ጠቅሷል

https://p.dw.com/p/467Ov
Video Still TV Magazin The 77 Percent
ምስል DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ4.3 በመቶ እንደሚያድግ ተነበየ

በዓለም ባንክ ትንበያ መሠረት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት እስከ መጪው ጥር ባለው አንድ አመት በ4.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ባንኩ ለጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም ለኢትዮጵያ  ያስቀመጠው የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያ 6.5 በመቶ ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት በዚህ አመት የሚኖራቸውን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ባለፈው ጥቅምት ሲተነብይ የኢትዮጵያን ሳያካትት መቅረቱን የሚያስታውሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት መተንበዩ አንድ ነገር ነው። በጥቅምት መጨረሻ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የአገሪቱ ሁኔታ አሳስቦኛል´ ብሎ የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ትንበያ አላካተተም ነበር። ይኸ አንድ ጥሩ ጎኑ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ያለፉት አመታት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአገሪቱ ምጣኔ ሐብት የሚበጁል አልነበሩም። ይኸ በኢትዮጵያ የለት ተለት ውጣ ውረድም ሆነ በዓለም ባንክ የጥር ወር ሪፖርት ቁልጭ ብሎ ይታያል። የዓለም ባንክ እንደሚለው "ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አገራት ትልቋ ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2020/21 የበጀት አመት 2.4 በመቶ የሚገመት የዕድገት መቀነስ ገጥሟታል።" በሪፖርቱ መሠረት ይኸ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመቀስቀሱ በፊት ከነበረው በሁለት ሶስተኛ ገደማ ዝቅ ያለ ነው።

በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም 9 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት በአመቱ ወደ 6.1 በመቶ ዝቅ ብሏል። በዓለም ባንክ ትንበያ መሠረት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. ያደገው 2.4 በመቶ ብቻ ነው። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው እርግጠኝነት ማጣት እና በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለኢትዮጵያ ዕድገት ማሽቆልቆል ኹነኛ ሚና ነበራቸው።

Äthiopien Symbolbild Tigray-Konflikt
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው እርግጠኝነት ማጣት እና በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለኢትዮጵያ ዕድገት ማሽቆልቆል ኹነኛ ሚና ነበራቸው።ምስል Eduardo Soteras/AFP

ዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረው ተጽዕኖ በተጨማሪ "በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰ ጦርነት ምክንያት የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ እንደሚኖር ምንም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ስለሆነ የ2021 የኤኮኖሚ ዕድገቱ በጣም ዝቅተኛ ቢሆን አይገርምም" የሚሉት አቶ አብዱልመናን በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም. ምጣኔ ሐብቱ እንደሚያገግም የዓለም ባንክን ትንበያ እያጣቀሱ ይናገራሉ።

"በ2022 ኤኮሚው ያገግማል። ዕድገቱ እጥፍ ገደማ ይሆናል። ከዚያ በኋላ 2023 ላይ ደግሞ ወደ 6.5 በመቶ ይሆናል ማለት ነው። ይኸ ማለት 2020 አካባቢ ያለውን የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ይመጣል ማለት ነው። ይኸ ማለት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ አሁን ከገባበት ችግር የማገገም ተስፋ አለው ማለት ነው። የ2019ን የኤኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ግን ሥራ ይጠይቃል" ሲሉ አቶ አብዱልመናን አስረድተዋል።

የግብርና ምርቶች ለዓለም ገበያ አቅራቢ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ያሉ አገሮች እንደ ቡና እና ጥጥ ያሉ ምርቶች ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገታቸው በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ይበረታታል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ድርቅ፣ የዝናብ እጥረት እና ውጊያ በኢትዮጵያ ለዚሁ ለግብርና ዘርፍ መልሰው ማነቆ ሊሆኑ እንደሚችሉ የዓለም ባንክ ሥጋት አለው።

ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በተያዘው አመት እንደሚያገግም ቢተነብይም ሥጋቶች እንዳሉበት ግን ቸል አላለም። ባለፈው አመት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሳህል ቀጠና በሚገኙት ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ ኒጀር እና ሰሜናዊ ናይጄሪያ የማኅበራዊ ቀውስ መበርታት፣ የጸጥታ መጓደል እና ግጭት መዋዕለ-ንዋይ ማደናቀፋቸውን እና የሸማቾችን ግብይት መግታታቸውን የዓለም ባንክ በዘገባው ይፋ አድርጓል። ውጊያ እና የጸጥታ መጓደል በዚህ አመትም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ይደርስበታል ተብሎ ከተተነበየው የምጣኔ ሐብት ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኢትዮጵያ የፖሊሲ አመለመረጋጋት፣ ማኅበራዊ ቀውስ እና የጸጥታ መጓደል በማዕድናት ማምረቻ እና የግብርናው ዘርፍ ተጽዕኖ ያሳድሩባቸዋል ከተባሉ አገሮች መካከል አንዷ ናት።

Äthiopien | Militärfahrzeug in Kombolcha
ውጊያ እና የጸጥታ መጓደል በዚህ አመትም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ይደርስበታል ተብሎ ከተተነበየው የምጣኔ ሐብት ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ባለፈው ዓመት የማገገም አዝማሚያ ያሳየው የዓለም ምጣኔ ሐብት የኮቪድ-19 አዳዲስ ዝርያዎች ባሳደሩት ሥጋት፣ በዋጋ ንረት እና በዕዳ ጫና እና በደሐ እና ሐብታም አገሮች መካከል በሚታየው የገቢ አለመመጣጠን ሳቢያ መልሶ መቀዛቀዙን የዓለም ባንክ አስታውቋል። ባንኩ ከሁለት ሣምንታት በፊት ገደማ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም 5.5 በመቶ የነበረው የዓለም የምጣኔ ሐብት ዕድገት በዚህ ዓመት ወደ 4.1 በመቶ ዝቅ እንደሚል ጠቁሟል። የዓለም ባንክ ትንበያ እንደሚያሳየው የዓለም ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት በጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም በአንጻሩ ወደ 3.2 በመቶ ዝቅ ይላል።

ይኸ ሪፖርት የዓለም አገራት ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ትንበያ በስድስት ቀጠናዎች ተከፋፍሎ በዝርዝር የቀረበበት ነው። ዓለም ባንክ በሪፖርቱ ባወረበው ትንበያ መሠረት የምሥራቅ እስያ እና ፓሲፊክ አገራት ምጣኔ-ሀብት በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም 5.1 በመቶ ያድጋል። አውሮፓ እና መካከለኛው እስያ በ3 በመቶ፣ ላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን አገሮች 2.6 በመቶ፤ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ 4.4 በመቶ እንደሚያድጉ የዓለም ባንክ ትንበያ ያሳያል። ከፍተኛው ዕድገት የሚጠበቀው በዓለም ባንክ 7.6 በመቶ እንደሚያድግ በተተነበየለት በደቡብ እስያ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት የጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም. ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት 3.6 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል። ይኸ ትንሽ መሻሻል አሳይቶ በሚቀጥለው አመት ወደ 3.8 በመቶ ይደርሳል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ