1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ለአማራ ክልል አርሶ አደሮች

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015

በአማራ ክልል በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ሚሊዮን 200 ሄክታር መካከል እስካሁን 237 ሺህ ብቻ መልማቱን የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ከ10ሺህ 400 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሮች አከፋፍሏል። አርሶ አደሮች መስኖን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4HXOe
Amhara regional gov. Wasserpumpen
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ማሳን በመስኖ ለማልማት መታቀዱ

 በአማራ ክልል በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ሚሊዮን 200 ሄክታር መካከል እስካሁን 237 ሺህ ብቻ መልማቱን የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ፣ ቢሮው ከ10ሺህ 400 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሮች አከፋፍሏል፣ የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል ለሚካሄደው የመስኖ ስራ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ የግብርና ሚኒስትር አመልክቷል፣ እገዛ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች መስኖን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል፡፡ 
በአማራ ክልል ሰፊ በመስኖ የሚለማ መሬት ቢኖርም በተለያዩ ሰበቦች መልማት የቻለው ካለው አቅም ውስጥ 237ሺህ ሄክታር (10 ከመቶ) እንደማይበልጥ ክልሉ አስታውቋል፣ ችግሮችን አስወግዶ ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ የአማራ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አመልክቷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዳኝነት ፋንታ በአማራ ክልል ከ2 ሚሊዮን 200 ሺህ ሄክታር በላይ በመስኖ የሚለማ መሬት ይገኛል፣ ጥቅም ላይ የዋለው ግን በጣም አነስተኛ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡
ሀብቱን ለመጠቀም ከሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የዉኃ መሳቢያ ሞተርን ማቅረብ አንዱ መሆኑን ጠቁመው አርሶ አደሩን በዚህ ረገድ ለማገዝ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
“ ቢራችን  በዛሬው እለት የምግብ ዋስናን ለማረጋገጥ ከሚሰሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎች መካከል አንዱ ሆነው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመስኖ ልማትን ማስፋፋት እንድንችል፣ ለአርሶ አደሮቻችን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 10ሺህ 467 የመስኖ ዉኃ ፓምፖችን ገዝቶ ሲያበረክት ከፍተኛ ደስታና ኩራት ይሰማዋል እነዚህ ፓምፖች አጠቃላይ ማልማት የሚችሉት እስከ 50ሺህ ሄክታር የሚደርስ ቢሆንም በተለያዩ የአፈፃፀም 50 ከመቶ ቢቀንሱ እንኳን በትንሹ 25ሺህ ሄክታር ማልማት ይችላሉ፡፡ ”
የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን የዉኃ መሳቢያ ሞተሮች ስርጪት በባሕር ዳር ሲካሄድ እንዳመለከቱት የአማራ ክልል የመስኖ ልማትን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት መንግስት እገዛ ያደርግለታል፡፡

Amhara regional gov. Wasserpumpen
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

“በግብርና ሚኒስቴር 3400 ፓምፖች፣ እናቀርባለን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር 4000 ይደርሳል ከዚያ ውስጥ በቀመሩ መሰረት አማራ ክልል ድርሻውን ስዳል”ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ልቃል ከፋለ በበኩላቸው በዚህ ዓመት 250 ሺህ ሄክታር ማሳ በመስኖ ለማልማት መታቀዱን አብራርተዋል፡፡ አርሶ አደሩ ህን ቴክኖሎጂ በመጠቀምም ምርታማነቱን እንዲሳድግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Amhara regional gov. Wasserpumpen
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የውኃ ሞተር ከተሰጣቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ይበልጣል ሰንደቅና ዋለ ደመወዝ ለዶቼ ቬሌ እንደነገሩት ቴክኖሎጂው በዓመት ሶስት ጊዜ ለማምረት ያስችላቸዋል፡፡ ራሳቸውን ጠቅመው ለአገር እድገትም የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ነው አርሶ አደሮቹ የገለፁት፡፡

የዉኃ መሳቢያ ሞተር ስርጭቱ የህዝብ ብዛትን፣ ፍላጎትን፣ በግንባታ ላይ ያሉትንና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ተመልክቷል፣ ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች በተቀመጠላቸው መስፈርቶች መሰረት መሳሪያዎቹን ከክብር እንግዶች እጅ ተረክበዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ታምራት ዲንሳ