1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋና ኦዲተር ሪፖርት እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምላሽ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 25 2016

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓም ጀምሮ የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ በግብርና፣ በሆቴል አገልግሎት፣ በእንጨት ፣ በብረታ ብረት እና በእደ-ጥበብ ዘርፎች የራስ አገዝ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል ፡፡ ኢንተርፕራይዙታዲያ ለበርካታ ብልሹ አሠራሮች የተጋለጠ ሥለመሆኑ በዉይይት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ውይይት ላይ ተጠቅሷል ፡፡

https://p.dw.com/p/4fU2f
ሀዋሳ ዩንቨርስቲ
ሀዋሳ ዩንቨርስቲ ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

የዋና ኦዲተር ሪፖርት እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምላሽ

የዋና ኦዲተር ሪፖርት እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምላሽ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓም ጀምሮ የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ በግብርና፣ በሆቴል አገልግሎት፣ በእንጨት ፣ በብረታ ብረት እና በእደ-ጥበብ ዘርፎች የራስ አገዝ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል ፡፡ይህ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ታዲያ ለበርካታ ብልሹ አሠራሮች የተጋለጠ ሥለመሆኑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ባደረጉት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ውይይት ላይ ተጠቅሷል ፡፡

አጋጠሙ የተባሉት ብልሹ አሠራሮች ምንድ ናቸው ?

የተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አጋጥሟል ያለውን ብልሹ አሠራር ዘርዝሯል ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በራስ አገዝ የሥራ ዘርፎች  የሚገኙ ንብረቶች ወደ ኢንተርፕራይዙ ካፒታል አልተካተቱም ያለው ኮሚቴው ከ2012 ዓም ጀምሮም የኢንተርፕራይዙ ሂሳቡ በኦዲት አልተረጋገጠም ብሏል፡፡

የሺመቤት ደምሴ ዶ/ር
የሺመቤት ደምሴ ዶ/ርምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 456/2012 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ እንዲመራ ያዛል ያሉት የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ “ ነገር ግን ኢንተርፕራይዙ የሥራ ዕቅዱን፣ በጀቱንና የግዥ ዕቅዱን አዘጋጅቶ ለቦርድ አቅርቦ የማያፀድቅና ተግባራዊ የማያደርግ መሆኑ በኦዲት ግኝት ለማረጋገጥ ተችሏል ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢንተርፕራይዙ የታለመለትን ግብ እየሳተና ለኪሳራ እየተጋለጠ ይገኛል ፡፡ የኢንተርፕራይዙ ጠቅላላ ሀብትም በገለልተኛ አካል ተጠንቶ መለየት ሲገባው ይህ አልሆነም  “ ብለዋል ፡፡

የ2016 ዓ.ም በጀትና አነጋጋሪዎቹ ፕሮጀክቶች

 

የዩኒቨርሲቲው ምላሽ

በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት የተሰጡ አስተያየቶች ተገቢነት ያላቸውና የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሚገኙ የተናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር አያኖ በራሶ “ በ2014 ዓም የኢንተርፕራይዙን ተጠሪነት ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ወደ ቦርድ እንዲዛወር አድርገናል ፡፡ የሰው ሀብት ፣ የፋይናንስ እና የግዢ መመሪያና ደንቦች ተጠንተው ቀርበዋል ፡፡ ደንቦቹን ካቀረብን በኋላ ግብረ መልስ እየወሰድን እያለ በመኸል የመጀመሪያው ቦርድ ተቀየረ ፡፡ እንደገና ከአዲሱ ቦርድ ጋር አስተያየቶችን ለመሰብሰብ እየሠራን ነው ፡፡ እስከአሁን ከአዲሱ ቦርድ ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተናል ፡፡ ይሁን አንጂ ይህ ሂደት ጊዜ ሊወስድና ሊራዘም ችሏል “ ብለዋል ፡፡

ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ
ወ/ሮ መሰረት ዳምጤምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

አከራካሪው ጉርሻ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያቤት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ውይይት ላይ አከራካሪ ሆኖ የቀረበው የጉርሻ / ቦነስ / ጉዳይ ነው ፡፡ ኢንተርፕራይዙ ኪሳራ ውስጥ ቢገኝም በጉርሻና ወይንም በቦነስ መልክ ለሠራተኞች የ968 ሺህ ብር ክፍያ መፈጸሙ በሪፖርቱ ተጠቅሷል ፡፡

አሳሳቢ ደረጃ የደረሰው የመንግሥትና ህዝብ ሀብት ምዝበራ

 “ እስከዛሬ ድረስም ቦነስ የሚባል ነገር ከፍለን አናውቅም “ያሉት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር አያኖ በራሶ “ ጉርሻ የሚሰጠው ሠራተኛ ካለ በቦርድ አካላት ነው የሚወሰነው “  ብለዋል ፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ግን ዩኒቨርሲቲው ጉርሻ በሚል ክፍያ ሥለመፈጸሙ ሰነዶች አሉን ፡፡ ይህን እንዲያብራሩ  በኢሜል ተጠይቀዋል ፡፡ ኢሜይሉን ከላዩት እንዲያዩት አስታውሶታለሁ “ ብለዋል ፡፡

ዶ/ር አያና በራሶ
ዶ/ር አያና በራሶምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

ለኮሚሽኑ የቀረበው ጥያቄ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ላይ ታይቷል ያለውን የፋይናንስ ህግ ጥሰት እንዲመረምር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አሳስበዋል  ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ጋር ተያይዞ በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በተሰጠው አስተያየት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ አልቻለም ያሉት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር የሺመቤት ደምሴ ጉዳዩን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል እንዲጣራ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ