1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዉጭ ሃገራት ወቀሳ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 28 2014

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳን ጨምሮ ስድስት ሃገራት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን መሠረት ያደረገ እስር «አሳስቦናል» አሉ። ስድስቱ ሃገራት በመግለጫው «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅን ተከትሎ የአንድ ብሔር ተወላጆች ተለይተው መታሰራቸው» ስጋት እንዳሳደረባቸው አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/43wQk
Ethnic Tigrians rally against TPLF in Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Seyoum Getu/DW

መንግሥት«ከህግ አግባብ ውጭ ያሰርኩት አንድም ዜጋ የለም»


ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳን ጨምሮ ስድስት ሃገራት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን መሠረት ያደረገ እስር «አሳስቦናል» አሉ። 
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ድረ ገጽ ላይ የወጣው የስድስቱ ሃገራት መግለጫ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅን ተከትሎ የአንድ ብሔር ተወላጆች ተለይተው መታሰራቸው» ስጋት እንዳደረባቸው ያስረዳል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ብሔርን መሰረት በማድረግ ከሕግ አግባብ ውጭ ያሰርኩት አንድም ዜጋ የለም ሲል ክሱን ተከላክሎታል፡፡ 
በጉዳዩ ላይ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት በኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ አዋጁ ብሔር ላይ የማተኮር ፍላጎት ያለው ሳይሆን መሰረቱ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን «ብሔራቸውን መሠረት በማድረግ ያለ ክስ እያሰረ ነው» ያሉት አገራት አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው። ዶይቼ ቬለ ከአዲስ አበባ ያነጋገራቸው እና እናታቸው መታሰራቸውን የሚገልጹት አንድ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት ነዋሪ እንደሚሉት በተለይም ከአንድ ወር ወዲህ መሰል ክስተቶችን ማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥትን የሚፋለመው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን በመቃወም ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሰልፍ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የትግራይ ተወላጅ የመዲናዋ ነዋሪ ሀሳቡን ውድቅ አድርገዋል፡፡ 
በዚሁ በአገራቱ ክስ እና የነዋሪዎች ቅሬታ ላይ ዶይቼ ቬለም የመንግሥትን አቋም የጠየቃቸው በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ለአገር ስጋት የሆኑ ቡድኖችን በመደገፍ የተጠረጠሩት ላይ ብቻ የሚያተኩር መሆኑን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫው ብሔር ተኮር እስራት እንደሚፈጸም እና ይህም እንዳሳሰበው ገልጿል። የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ ግን የመንግሥት እርምጃ የሕግና ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሳተ አለመሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ ዓመትን የተሻገረው የሰሜን ኢትዮጵው ጦርነት መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሞት እና የንብረት ውድመቶችን ማስከተሉም በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

Ethnic Tigrians rally against TPLF in Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Seyoum Getu/DW
Ethnic Tigrians rally against TPLF in Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Seyoum Getu/DW


ስዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ