1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዉኃ ሙላት ከ100 በላይ ሰዉ ገደለ

ዓርብ፣ ሐምሌ 9 2013

ራይንላንድ ፋልስና ኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ በተባሉት የምዕራብ ጀርመን ተጎራባች ክፍለ ግዛቶች ዉስጥ እስካለፈዉ ሮብ ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ሐዲዶችን፣ የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮችን፣ የዉሐና የፈሳሽ ቆሻሻ መተላለፊያ ቦዮችን ከጥቅም ዉጪ አድርጓቸዋል

https://p.dw.com/p/3wazh
Deutschland Unwetterkatastrophe | Bad Neuenahr-Ahrweiler in Rheinland-Pfalz
ምስል Ferdinand Merzbach/AFP/Getty Images

ዜና፣ ኃምሌ 9፣2013

የጀርምን ምዕራባዊ ግዛቶችን፣ ከጀርመን ጋር የሚጎራበቱ የቤልጂግ፣ የኔዘርላንድስንና የከፊል ላክሰምበርግን ግዛቶች ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ ከ110 በላይ ሰዎችን ገደለ።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አፈናቀለ።በሺሕ የሚቆጠሩ ቤቶችን አፈረሰ።ከፍተኛ ጉዳት የደረሰዉ ዶቼ ቬለ ከሚገኝባት የቦን ከተማ በ20ና 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ አካባቢዎች ናቸዉ።ራይንላንድ ፋልስና ኖርድ ራይን ቬስትፋሊያ በተባሉት የምዕራብ ጀርመን ተጎራባች ክፍለ ግዛቶች ዉስጥ እስካለፈዉ ሮብ ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ሐዲዶችን፣ የኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮችን፣ የዉሐና የፈሳሽ ቆሻሻ መተላለፊያ ቦዮችን ከጥቅም ዉጪ አድርጓቸዋል።የጀርመን የአደጋ ሠራተኞች፣ሐኪሞች፣ ፖሊስ፣ የጦር ኃይል ባልደረቦችና ፈቃደኞች በአደጋዉ የተጎዶቱን ሰዎች ለመርዳት ዛሬ ለሁለተኛ ቀን ሌት ከቀን እየባተሉ ነዉ።መራሒቴ መንግስት አንጌላ ሜርክል ለጉብኝት ከተጓዙበት ከዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት መንግስታቸዉ ለጉዳተኞ አስፈላጊዉን ርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።ፕሬዝደንት ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬ እንዳሉት ደግሞ ጀርመኖች በመከራ ጊዜ በጋራ ይቆማሉ።
«በነዚሕ ዕለታትና ሠዓታት ከእኒያ ጎርፍ፣ ሁሉንም ነገር ከቀማቸዉ ሰዎች ጎን መቆም በጣም አስፈላጊ ነዉ።የፌደራሉና የክፍለ-ግዛት መንግስታት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸዉን ለመርዳት በጋራ መቆማቸዉ በጣም ጠቃሚ ነዉ።ጉዳት የደረሰባቸዉ ማሕበረሰቦች ኪሳራቸዉን ለመጠገን ዕርዳታ ያገኛሉ።በመከራ ሠዓታት ሐገራችን በጋራ ትቆማለች።»
የአዉሮጳ ሕብረትም በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ አባላቱ ርዳታ ለመስጠት መወሰኑን የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን አስታወቀዋል።ወይዘሮ ፎን ዴር ላይን እንዳሉት ኮሚሽናቸዉ ጀርመን፣ቤልጂግ፣ ኔዘርላንድስና ላክሰምበርግን ለመርዳታ የሚያስችለዉን ሥርዓት አነቃንቋል።«ኮሚሽኑ፣ በዚሕ በጣም፣በጣም አስቸጋሪ አደጋ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸዉን አባል ሐገራት ለማገዝና ለመርዳት የሚያስፈልገዉን ሥርዓት አንቀሳቅሷል።»
በሶስቱ ሐገራት በተለይም ጀርመን ዉስጥ አንድ ጊዜ በደረሰ አደጋ በርካታ ሰዉ ሲሞት ከ2ኛዉ ያዓለም ጦርነት ወዲሕ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።ባለሙያዎች እንደሚሉት በአንዳድ አካባቢዎች የጣለዉ የዝናብ መጠን ደግሞ በምዕተ-ዓመት ዉስጥ እጅ ከፍተኛዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ