1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅናት መንስኤ እና መፍትሄው

ዓርብ፣ መስከረም 30 2012

ለመሆኑ ፍቅር እና ቅናት አብሮ ይሄዳል ትላላችሁ? አንዳንድ ሰዎች ከቅናታቸው የተነሳ ያፈቀሩት ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ይታያል። ከድብደባ አንስቶ ፊት በአሲድ እስከማበላሸት እና ግድያ የደረሱም አሉ። የቅናት መንስኤን እና መፍትሄው ምንድን ነው?

https://p.dw.com/p/3R7yz
Zwei Frauen ohrfeigen sich
ምስል picture-alliance/E.Topcu

ፍቅር እና ቅናት አብሮ ይሄዳል?

በጀርመን ጎረቤት ሀገር ኦስትሪያ ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ነገር ብዙዎችን አስደንግጧል።  አንድ ወጣት ኪትዝቡል በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ አምስት ሰዎችን ገድሎ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል። ለዚህ ሁሉ ምክንያት የተባለው ቅናት ነው። ከብሔራዊ የወንጀል የፖሊስ ጽ/ቤት ቫልተር ፑፕ የሆነውን እንዲህ ያብራራሉ። «አንድ የሀገሬው ሰው የሆነ የ25 ዓመት ወጣት ኪትዝቡል ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ወደ ውስጥ በመግባት አንድ ሽጉጥ እና አንድ ቢላዋ የእንግዳ መቀበያው ጠረጴዛ ላይ ካስቀመጠ በኋላ አምስት ሰዎችን ገድዬ መምጣቴ ነው ሲል ተናገረ።» ወጣቱ የገደለው ከሁለት ወር በፊት የተለየችው የቀድሞ ፍቅረኛውን፣ የወጣቷን አዲስ ፍቅረኛ፣ እናት እና አባቷን እንዲሁም ወንድሟን ነው። በሰዓቱም ሁሉም በወጣቷ ወላጆች መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበሩ። ፖሊስ ከቅናት በስተቀር ለወንጀሉ ሌላ ምክንያት የለም ይላል። 

Österreich | Kitzbühl | Mann ermordet Ex-Freundin und Familie
ምስል picture-alliance/AP Photo/K. Joensson

ለጊዜው ዳንኤል ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ወጣት የቀድሞ ጓደኛውን የደበደባት በሌላ ወንድ ጠርጥሯት እንደሆነ አጫውቶናል። « ይሄ በፍቅር ነው። ቅናት ቢሆንማ ከቤት አስረሽ ታስቀምጪያታለሽ።» ሁኔታው ዳንኤልን በመጨረሻ ፀፅቶታል። አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ናቸው በወንድ አፍቃሪዎቻቸው ሲደበደቡ ወይም በደል ሲፈፀምባቸው የሚሰማው ነገር ግን እንደ ቢንያም ያሉ ወንድ ተጠቂዎች አሉ።  በእውነተኛ ስሙ የማንጠራው ወጣት ጉዳት ፈፅማብኛለች የሚላት ሴት እሱ እንደሚለው ፍቅረኛው እንኳን አልነበረች። የሆነው ነገር ዛሬም ለባለ ጉዳዩ እንቆቅልሽ ነው። « እሷ ጋር እንዴት እንደማድር እንኳን አላውቅም። ለስራ እሷ ጋር እሄድ ነበር  ሂሳብ ስንሰራ እናመሻለን፣ ማታ ላይ የሆነ የሚጠጣ ነገር እንጠጣ እንደነበር አስታውሳለሁ። » በኋላ ላይ ግን ሴትየዋ መጠጥ ታጠጣው እንደነበር፣ ታስፈራራው እና በመኪና ልታስገድለው ሙከራ ማድረጓንም ዳንኤል ነግሮናል።  ለዚህም ምክንያቷ ፍቅር ነበር። ቢንያም ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሴቶች ላይ እምነት እንዳጣ እና ሁሉም ሰዎች የሚጎዱት እንደሚመስለው አጫውቶናል። 

Symbolbild Eifersucht und Liebe
ምስል Colourbox

ስሙ እንዲገለጥ ያልፈለገ አንድ ወጣት፦  ከቤንሻንጉል «አዎ ቀንቼ አዉቃለሁ ስለጠላኋት አይደለም በጣም ስለማፈቅራት እንጅ እናም ምስጥሯን አባከንኩ ሰዉ ሁሉ እንዲታዘባት አደረኩ» ብሏል። ሌላኛው በበኩሉ፦ «ስራዬን ሳልጨርስ ወይም ጉዳዬን ሳልፈፅም ውስጤን እቤት ወንድ ገባ የሚል ስሜት ይሰማኛል። ከዛ ሁሉንም ነገር አቋርጬ ወደ ቤት ስሄድ ምንም የለም። አይ አሁን ወጥቶ ነው እልና አይንዋን  የሆነ ነገር ለመረዳት አተኩሬ አያለሁ።  ለምን ስራ ትቼ እንደመጣሁም እንዳታቅብኝ ምክኒያት እደረድራለሁ እና በተወሰነ መልኩ ትዳሬን እየረበሸ ነው» ይላል።

ቅናት ከምን ይመነጫል?

የባለሞያ አስተያየት እንስማ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሀኪም ናቸው። « ቅናት ከመጠን በላይ መውደድ ፣ ከመጠን በላይ ማፍቀር ብቻ ሳይሆን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መውደድ እና ማፍቀር ነው። ጫና የሚፈጥር ፍቅር ማለት ነው።» ይላሉ። ይህም ጫና በተፈቃሪው ላይ ከጥርጣሬ አንስቶ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እስከሚያደርስ አይነት ህመም የተቀየረ ቅናት እንደሚሸጋገር ፕሮፌሰር መስፍን ያስረዳሉ። « አስፈላጊው ዕርምት ካልተደረገበት ችግር የደረሰበት ሰው በሌላኛውም ላይ ችግር ማድረሱ አይቀሬ ነው።»
አንድ በጀርመን ነዋሪ የኾነ የዝግጅታችን ተካፋይ «ቅናት የተፈጥሮ ባህሪ ይመስለኛል» ይላል። «ህጻናት በተወለዱ በመጀመርያ ዓመታት የምያሳዩት ፍቅር ይለያያል ኣንዳንዱ ምንም ሳይመስለው ለታናሹ  ፍቅር ስያሳይ ኣንዳንዱ ወላጆች ካልጠበቁት በታናሹ ጥቃት የምያደርስም ኣለ ። እነዚህ ህጻናት ስለ ቅናት ከየት ኣወቁ? ብሏል። ለዚህም ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን ምላሽ ሰጥተዋል። « ህፃናት በላይ በላይ ሲወለድ እናቶች ትኩረት የሚሰጡት ለህፃኑ ነው። ህፃኗ ከእናቷ ፍቅር ሳትላቀቅ ሌላ ህፃን ሲመጣባት ልጅቷ ለታናሽዋ ወዳጅ እንዳትሆን ያደርጋታል። እና ቅናትን እድሜ አይወስነውም» ይላሉ በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር እና ሀኪም ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ።

Partnerschaft - Internetsucht
ምስል picture-alliance/dpa/M. Wuestenhagen

ልደት አበበ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ