1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የወባ መድሃኒት ና ኮቪድ19

ረቡዕ፣ ግንቦት 19 2012

ይህንን መድሃኒት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ባለፈው መጋቢት መጨረሻ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የብራዚሉ አቻቸው ጄር ቦልሶናሮ ለኮቪድ-19 ፍቱን ነው በሚል በተደጋጋሚ ቢያወድሱትም፤ የአሜሪካው የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር በሚያዚያ ወር መጨረሻ የመድሃኒቱን አደገኛነት በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል

https://p.dw.com/p/3crHu
Frankreich Marseille | Medizinisches Personal mit Tabletten
ምስል Getty Images/AFP/G. Julien

ሳይንስ እና ሕብረተሰብ፦ የሎሮኪዩንና ሃያድሮክሲክሎሮኪዩን መድሐኒትነት

                       
የኮቪድ -19 በሽታን የሚፈዉስ መድሃኒት ወይም መከላከያ ክትባት ለማግኘት የሚደረገዉ ምርምር እንቀጠለ ነዉ።እስካሁን ከተደረጉ ሙከራዎች የወባ በሽታ የሚያድነዉ መድሃኒት ሃይድሮክሲክሎሮክዊን አንዱ ነዉ።የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ሰሙኑን እንዳስታወቀው ግን በዚህ መድሃኒት ላይ ይደረግ የነበረው  ሙከራ ለጊዜው እንዲቋረጥ ተወስኗል።የዛሬዉ ሳይንሳና ሕብረተሰብ ዝግጅታችን ስለሐይድሮሲክሎሮኪን የነበረዉን ግምትና ሙከራዉ የተቋረጠበትን ምክንያት ይቃኛል። «ክሎሮኪዩንና ሃይድሮክሲክሎሮኪዩን በተመለከተ ብዙ ጥሩ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ። በጣም ልትገረሙ ትችላላችሁ ።ምን ያህል ሰዎች እንደሚወስዱት። በተለይ ግንባር ቀደሞቹ የጤና ባለሙያዎች ከመያዛቸው በፊት ይዉሰዱት።ብዙ ሰዎች እየወሰዱት ነው ።እኔም እየወሰድኩት ነው።» በማለት ነበር የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃያድሮክሲክሎሮኪዩን የተባለውን መድሃኒት ያሞካሹት። 
የወባ በሽታን ለማከም የሚውለውና በህክምና ስሙ ሃያድሮክሲክሎሮኪዩን የሚባለው ይህ መድሃኒት የኮቪድ -19ን  ለማከም ያገለግላል በሚል ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል። 
ይህንን መድሃኒት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ባለፈው መጋቢት መጨረሻ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የብራዚሉ አቻቸው ጄር ቦልሶናሮ ለኮቪድ-19 ፍቱን ነው በሚል በተደጋጋሚ ቢያወድሱትም፤ የአሜሪካው የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር በሚያዚያ ወር መጨረሻ የመድሃኒቱን አደገኛነት በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ተመራማሪዎችም የኮቪድ-19 በሽታን ለመዋጋት መድሃኒቱ ውጤታማ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ አለመገኘቱን በተደጋጋሚ ገልፀዋል። 
በኮቪድ-19 በሽታ ሳቢያ በከፍተኛ መጠን ዜጎቿ የሚሞቱባት ብራዚልም፤ በጥቂት ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህመምተኞች የሕክምና ክትትል ሳይደረግላቸው በቤት ውስጥ መድሃኒቱን ራሳቸው በመጠቀም ለሞት ተዳርገዋል በሚል የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። 
የዓለም ጤና ድርጅት ያለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 በሽታን ለማከም ይረዳ ይሆናል በሚል ሃይድሮክሲክሎሮክዊን ላይ ይደረግ የነበረው ክሊኒካዊ ሙከራ ለጊዜው እንዲቋረጥ ወስኗል። 
የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው ላንሴት የተባለው የሕክምና መጽሔት በሰሞኑ ዕትሙ ይዞት የወጣውን ጥናት መሰረት በማድረግ ነው። በዚህ ጥናት መሰረት መድሃኒቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለሞት ይዳርጋል።የዓለም ጤና ድርጅት  
 ሀላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በሰጡት መግለጫ በዚህ መድሃኒት ላይ የሚደረገው ሙከራ ለጊዜው እንዲቋረጥ የተወሰነው በታካሚዎች ጤና ላይ አደጋ ሊያደርስ ይችላል በሚል  ስጋት ነው። 
"የከፍተኛ የስራ አስፈፃሚው ቡድን አባላት የሃይድሮክሲክሎሮክዊን ሙከራ ዳግም በመረጃ ቁጥጥር ቦርዱ እስኪመረመር ድረስ ለጊዜው እንዲቋረጥ ወስኗል። ሌሎች ሙከራዎች ይቀጥላሉ።ይህ ማሳሰቢያ ሃይድሮክሲክሎሮክዊንና ክሎሮክዊንን ለኮቪድ -19 ከመጠቀም ጋር የሚያያዝ ነው።» 
ከሁለት ወራት በፊት ፣ በዓለም ዓቀፉ ጤና ድርጅት ተነሳሽነት ኢቦላን ለማከም ይረዳ የነበረውን ሬሚዲሲቪር የተባለውን መድሃኒት ጨምሮ COVID-19ን ለማከም ይረዳሉ በተባሉ አራት መድሃኒቶች ላይ ክሊኒካዊ ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል።በዚህ ሙከራ መድሃኒቶቹ ውጤታማ ስለመሆናቸውና ስለጎንዮሽ ጉዳታቸው ሲመዝን ከቆየ በኃላ ነበር ሃይድሮክሲክሎሮኪን ሙከራ ከሚደረግባቸው ዝርዝር መድሃኒቶች ውስጥ መውጣቱ የተሰማው። 
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በኦሃዮ ስቴት ዩንቨርሲቲ ግሎባል ሄልዝ ኢንሸቲቭ የምስራቅ አፍሪቃ ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት ይመር ፤ይህ መሰሉ ነገር መድሃኒት በማበልፀግ ሂደት የተለመደ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው በሂደቱ የተለያዩ ያገባኛል የሚሉ አካላት መኖራቸዉን በማብራራት ይጀምራሉ። 
በተለይ የወባ መድሃኒትን ለመሞከር በ35 አገራት ውስጥ ከ400 በሚበልጡ ሆስፒታሎች  በሽተኞች ተለይተው የነበረ ሲሆን፤መድሃኒቱን ለመሞከርም እስካሁን በ17 አገሮች ወደ 3 ሺህ 500 የሚጠጉ ታካሚዎች ተመዝግበው እንደነበር የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል፡፡ 
በላንካሴት የህክምና መፅሄት በታተመው ጥናት 96 ሺህ በተዋህሲው የተያዙ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ከነዚህ መካከል፤15 ሺህ የሚሆኑት በክሎሮኩዊንና በሃይድሮክሳይድክሎሮኪዩን ህክምና ተደርጎላቸው፤ ለከፍተኛ ልብ ድካም ሊዳርግ የሚችል ያልተለመደ የልብ ምት እንዳጋጠማቸው ተደርሶበታል።የወባ በሽታ መድሃኒት ለአመታት ሲሰጥ የቆየ መድሃኒት ሆኖ እያለ ኮቪድ-19ን ለማከም በተደረገው ሙከራ ይህ መሰሉ ጉዳት ለምን አጋጠመ? ዶክተር ጌትነት ይመር የጉዳቱ መንስኤ መድሃኒቱ ከሚሰጥበት መጠን ጋር እንደሚያያዝ ያብራራሉ። 
ከዚህ በተጨማሪ የፀረ-ወባ መድሃኒት ለብቻውም ሆነ «ማክሮይድ»ከተባለው ንጥረ ነገር ጋር በሚወስዱ የኮቪድ-19 ህሙማን ላይ ከማይወስዱት የበለጠ ከፍተኛ የሞት መጠን መመዝገቡን ጥናቱ ይፋ አድጓል። በአጠቃላይ ጥናቱ በስድስት አህጉሮች፤ በ671 ሆስፒታሎች በሚገኙ በኮሮና ተዋህሲ የተያዙ ሰዎችን የሕክምና ታሪኮች የቃኘ ሲሆን፤ በዚህም መድሃኒቱ ከውጤት ይልቅ በታካሚዎቹ ጤና ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ተመልክቷል።ያም ሆኖ የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሁንም ድረስ መድሃኒቱን ለመከላከያነት እየተጠቀምኩት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።የህክምና ባለሙያው ዶክተር ጌትነት ይመር ግን ህብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ ያለሀኪም ትዕዛዝ መድሃኒቱን ከመውሰድ እንዲቆጠብ ይመክራሉ። 
ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የዋሉ መድሃኒቶችን ለአዳዲስ በሽታዎች መጠቀም የክሊኒካል ሙከራ ጊዜን ለማሳጠርና ተመርተው ገበያ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ገዝቶ ለመጠቀምም ቀላል ቢሆንም፤ በመድሃኒቶቹ ላይ ተከታታይና ጥንቃቄ የተሞላበት ሳይንሳዊ ምዘና መደረግ እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። 
በዚህ መሰረት ከአስር ሀገራት የተወከሉት የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ስራ የአስፈፃሚ ቡድን አባላት፤ ያለፈው ቅዳሜ ባደረጉት ዉይይት በዓለም ዙሪያ በተገኙ መረጃዎች ላይ አጠቃላይ ትንተናና ወሳኝ ግምገማ ለማድረግ ተስማምተዋል ፡፡ 
እንደ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፤ ይህ መሰሉ ግምገማ እስካሁን በተደረገው ሙከራ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ፣ የዚህን መድሃኒት ጥቅሞች እና ጉዳቶች በበቂ ሁኔታ ለመመዘን ያስችላል ። 
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅቱ የድንገተኛ የጤና ችግሮች መርሃ ግብር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ማይክ ሪያን በበኩላቸው ደኅንነትን ጠብቆ ለመቀጠል የቅርብ ጊዜ ጥናቶችንና ሌሎች ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ድርጅቱ ሙከራውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚሰራ አመልክተዋል ፡፡ 
እስከዚያው ግን ለዓለም ሀገራት ስጋት ሆኖ የቀጠለውን የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት ለመከላከል ክትባት ለማግኘት ከሚደረገው ምርምር ጎንለጎን፤ በሽታው በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚያስችሉ ሌሎች መድሃኒቶችን ላይ የሚካሄዱ ሳይንሳዊ ምርምሮች ይቀጥላሉ።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ
 

USA Pressekonferenz Donald Trump
ምስል Reuters/L. Millis
Tedros Adhanom Ghebreyesus
ምስል Getty Images/Afp/F. Coffrini
Coronavirus im Elektronenmikroskop
ምስል picture-alliance/dpa/AP/NIAID-RML