1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወር አበባ ጸጋ ወይስ እርግማን?

ዓርብ፣ ሰኔ 24 2014

የወር አበባ መቀበያ ከቅንጦት ዕቃነት ወጥቶ ከቀረጥ ነጻ የሚገባበትና አገርውስጥ ለሚያመርቱትም ተገቢ ማትጊያ እንዲደረግላቸው አይ ኬር ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/4DPuJ
Äthiopien I care Kampagne Binden Menstruation
ምስል privat

የወር አበባ ጸጋ ወይስ እርግማን?

እስከ 75 በመቶ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች የወር አበባ መቀበያ እንደማያገኙ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የቆየው የወር አበባን እንደ እርግማን የማየት ባሕል የሴቶች ሕይወት ካከበዱ በጉልህ የሚጠቀስ ግን ደግሞ ትኩረት ያልተሰጠው የባሕላችን አንዱ አካል ነው። የዛሬ የባሕል ዝግጅት በዚህ ላይ ያተኩራል።

<<ስሜ ትግስት ይባላል። ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ነኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ያየሁት በ14 አመቴ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ደም ሲፈሰኝ የተሰማኝ ስሜት ዝብርቅርቅ ያለ ነበር። በአንድ በኩል ምንም እንኳ ስለ ወር አበባ እና ንፅህና አጠባበቅ የተማርኩት ነገር ባይኖርም ሙሉ ሴት የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። በሌላ በኩል ግን በማህበረሰቡ ሊደርስብኝ የሚችለውን መገለልና በዚህ ምክንያት ከትምህርት ቤት ልስተጓጎል መሆኑን ሳውቅ ከፋኝ። ይኸውላቹ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ አንዲት የወር አበባ የምታይ ሴት ከማህበረሰብ ጋር እንድትቀላቀል አይፈቀድላትም። የወር አበባዋ በመጣ ጊዜ ከማህበረሰቡ ወጣ ወዳሉት ለዚህ አላማ ብቻ ወደተዘጋጁት ቤቶች እንድታመራ ይደረጋል። እኔም የወር አበባዬ ከመጣበት ቀን አንስቶ ለሳምንት እዛ ኦና ቤት ውስጥ ተቀመጥኩ። ግራ መጋባት፣ጥፋተኝነት፣ አናሳነት እና ከምንም በላይ የቆሸሽኩ ያህል ተሰማኝ። እኔ ልቆጣጠረው በማልችለው በተፈጥሮ ለመጣ ነገር ተቀጣሁ፣ ከትምህርቴም ተስተጓጎልኩ። ከዛች ቀን በኋላ ህይወቴ ከባድ ሆነ። የወር አበባዬ በመጣ ቁጥር ከማህበረሰቡ መገለል እና ከትምህርት ቤት ለሳምንት ያህል መቅረት የተለመደ ነገር ሆነ። ይህም በትምህርቴ ላይ ጫና አሳድሮብኛል። ። የወር አበባ ማህበረሰቡ እንደ እርግማንና ነውር እንዳያየው ትምህርት እና ግንዛቤ በማህበረሰብ አቀፍ እና ትምህርት ቤቶች ሊሰጥ ይገባል።>>

Damenbinde
ምስል INDRANIL MUKHERJEE//AFP/Getty Images

አይ ኬር የተባለ በሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ አጠቃቀም የንቃት ዘመቻ የሚያካሂድና ሀብት አስተባብሮ በተለይ ለሴት ተማሪዎች የወር አበባ መቀበያ በነጻ የሚያድል ድርጅት ከአጋሮቹ ጋ ባደረገው ጥናት የተካተተች ወይዘሮ የሰጠችው አስተያየት ነበር። የድርጅቱ መስራችና ሃላፊ ወይዘሮ ማህሌት ዘለቀ ይህ ችግር በገጠር ብቻ ተወስኖ የሚቀር አደለም ትላለች። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በተለይ ሴት ተማሪዎች ሕብረተሰቡ ለወር አበባ ያለው ግንዛቤ ላይ የመግዛት አቅም ችግር ታክሎበት ትምህርት ማቋረጥ፣ ከስራ ገበታ መቅረትና ከተለያዩ ማሕበራዊ መስተጋብሮች መታጎል እጣፈንታቸው እንደሆነ ወይዘሮ ማህሌት ዘለቀ ነግራናለች።

ይህን ሥር የሰደደ የባሕልና የኢኮኖሚ ችግሮች ተዳምረው የሴቶችን ህይወት ያከበዱት ተግባራት በአደባባይ ለሞሞገትና ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ የተመሰረተው አይ ኬር እስካሁን በማስተማርና በመርዳት በርካታ ስራዎችን እንዳከናወነ ወይዘሮ ማህሌት አጫውታናለች። እስካሁን በተካሁደው የበጎ አድራጎት ሥራ በ100 ትምህርት ቤቶች ወደ 30 ሺ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን በማከል።

በበጎ አድራጊው ድርጅት የወር አበባ መቀበያ ድጋፍ የተደረገላቸው ትምህርትቤት ሴት ተማሪዎች ጥሩ ውጤት በማምጣት ጭምር ወደቀጣይ ክፍል ሲያልፉ ትምህርትቤቶችም ተማሪዎች በማሳለፍ በኩል ከነበራቸው ዝቅተኛ ደረጃ ወጥተው ወደ ጥሩ ደረጃ መድረሳቸውን በጥናት መረጋገጡን ወይዘሮ ማህሌት ገልጻለች። ሆኖም ግን እንደሕብረተሰቡ ጎጂ ባሕል ሁሉ የመንግስት ትኩረት አናሳነትም ችግሩን እንዳባባሰው አክላለች። በመሆኑም የወር አበባ መቀበያ ከቅንጦት ዕቃነት ወጥቶ ከቀረጥ ነጻ የሚገባበትና አገር ውስጥ ለሚያመርቱትም ተገቢ ማትጊያ እንዲደረግላቸውና በግልጽ ተመን ወጥቶለት እንዲሸጥ ድርጅቱ ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 

አዜብ ታደሰ