1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቅሬታ

ሰኞ፣ ጥር 22 2015

የምክር ቤቱ መግለጫ “ህዝበ ውሳኔው የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ ፣ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ተፅኖ የተንጸባረቀበት ነው “ ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ህዝበ ውሳኔው የአካባቢው ህዝቦች መብቶቻቸውን እንዲለማመዱ እንደ ዜጋ ያላቸውን ሥልጣን እንዲያሳዩ ዕድል የሚሰጥ አንጂ የሚጻረር አይደለም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4MtBY
Äthiopien Wahllokale für Vertriebene im Süden
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቅሬታ

በደቡብ ክልል በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ህዝበ ውሳኔ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መብት እየተጻረረ ይገኛል ሲል የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  ገለጸ፡፡ አሥር የፖለቲካ ፖርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው ምክር ቤት ባወጣው  መግለጫ በህዝበ ውሳኔው ዙሪያ አሉ ያላቻውን ችግሮች ዘርዝሯል ፡፡ 

በምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በአቶ ማቱሳላ ማለቆ አማካኝነት በንባብ በቀረበው የምክር ቤቱ መግለጫ “ህዝበ ውሳኔው የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ ፣ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ተፅኖ የተንጸባረቀበት ነው “ ሲል ቅሬታውን አሰምቷል ፡፡  

ህዝበ ውሳኔው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያልተሳተፉበት ነው ሲሉ መግለጫውን ያሰሙት አቶ ማቱሳላ “ ነጭ እርግብ በጋራ ክልል መደራጀትን ለሚደግፉ ጎጆ ደግሞ ለማይደግፉ የቀረቡ ምልክቶች ናቸው ፡፡ ይሁንእንጂ አንድን ምልክት ብቻ አጉልቶ የማስተዋወቅ ተግባር እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሕዝበ ውሳኔውን እያስፈጸመ የሚገኘው የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ክትትል እንዲያደርግ እንጠይቃለን “ ብለዋል ፡፡ 

Äthiopien Nationale Wahlbehörde hat zehn Wahllokale in den Zonen Wolaita und Gofa geschlossen
በደቡብ ክልል የመራጮች ምዝገባ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ዶቼ ቬለ DW   በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  መግለጫ ዙሪያ ያነጋገራቸው የኢትዮጲያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ፓርቲዎቹ በህዝበ ውሳኔው ሀሳባቸውን መግለጻቸው የሚጠበቅ ፣ የሚደገፍም ነው ብለዋል ፡፡ “ እየተካሄደ የሚገኘው ህዝበ ውሳኔ የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ ነው “ የሚለው ግልጽ አይደለም ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ ” የአካባቢው ህዝቦች በመራጭነት መሳተፉቸው ይልቁንም መብቶቻቸውን እንዲለማመዱ ፣ እንደ ዜጋ ያላቸውን ሥልጣን እንዲያሳዩ ዕድል የሚሰጥ አንጂ የሚጻረር አይደለም ፡፡ መራጮች ሀሳባቸውን እንዲገልጹና ድምጻቸው በአግባቡ እንዲቆጠር ማድረግ ደግሞ የቦርዱ ሃላፊነት ነው  “ ብለዋል ፡፡  

በዞኖችና ወረዳዎች አካባቢ አንድን ምልክት ብቻ አጉልቶ የማስተዋወቅ ተግባር እየተስተዋለ ይገኛል የተባለው ትክክል አይደለም ያሉት ሰብሳቢዋ በቦርዱ በኩል ህዝቡ ሁለቱንም ምልክቶች ለይቶ እንዲያውቅና ሀሳቡን በትክክል እንዲገልፅ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን እየተሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡ እንዲሁም በነጻ የሲቪል ማህበራት አማካኝነት የክርክር መድረኮች መከናወናቸው የጠቀሱት ብርቱካን ሚደቅሳ “ ለመራጮች ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ በቀሪ ቀናትም ይቀጥላል ፡፡ በእኛ በኩል ግን ሁለቱም ሀሳቦች እንዲጸባረቁ እየሠራን እንገኛለን  ፡፡  ያ ማለት ግን አንድ ፓርቲ ነጭ እርግብን ሥላስተዋወቀ ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው ብሎ ለመለካት አያስችልም “ ብለዋል ፡፡ 

በደቡብ ክልል የፊታችን ጥር 29 2015 ዓ.ም በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በክልሉ  6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የጋራ ክልል እንዲመሠረት “ እደግፋለሁ “ ወይም “ አልደግፍም “ የሚሉ ድምፆች ይሰጣሉ  ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለህዝበ ውሳኔ ከ3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ለመራጭነት መመዝገባቸውን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡  

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ