1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋው ጥቃት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በትግራይ ክልል፣ የሞሮኮ ድል

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2015

ማኅበራዊ መገናኛው መድረክ በየዕለቱ የሚነጋገርበት ሀገራዊ ጉዳይ አያጣም። በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙና ጊዳ አያና ጉቲን ከተማን ጨምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው ግድያ፤ በትግራይ ክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስለመጀመሩ እንዲሁም ስፔንን በግብ ብልጫ አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፈችውን የሞሮኮን ድል ከተመለከቱት መራርጠናል።

https://p.dw.com/p/4KkFy
Symbolbild Social Media
ምስል Jaap Arriens/NurPhoto/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ጉቲን ከተማን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የፈጸሙት ግድያ ብዙዎችን ያወዛገበ መሆኑ ቢስተዋልም የሞተው ክቡሩ የሰው ልጅ ነው በሚል የደረሰውን ጥፋት ያወገዙ እና የሚያወግዙ በርካቶች ናቸው። አብ ማን ታደሰ በፌስቡክ፤ «ሰው ከሰውነቱ ሲለቅ አንደ ማየት የሚያሳዝን ነገር የለም እግዚአብሔር ይፈርዳል የፈሰሰው ደም አንደ አቤል ደም ወደ እግዚአብሔር ይጮሃል።» የሚል አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ወርቁ አዲሱም በፌስቡክ፤ «ትክክል ብዙ ሺዎች ተፈናቅለዋል ሞተዋል፤ ቆስለዋል ንብረት ወድሟል ተዘርፏል ። የሚያሳዝነው ደግሞ ከጥቃቱ የተረፉት ሰብአዊ ድጋፍ ማጣታቸው ነው።» ይላሉ፤ ከድር ተገኘም እንዲሁ በፌስቡክ፤ «በኦሮሚያ ግፍ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው ... ይሄን አስከፊና አሰቃቂ በደም እየተፃጻፈ ያለ ጥቁር ታሪክ መንግሥት ትኩረት ከመንፈጉም በላይ እጁ ያለበት እስኪመስል ድረስ ህዝብን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል!» ሲሉ፤ ክፍሉ በዳኔ በበኩላቸው፤ «ኧረ የመንግሥት ያለህ ፣ሳይቃጠል በቅጠል ይሁን።» ነው ያሉት። አንተነህ በትርፍ የተባሉ ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚ ግን፤ «መንግሥት?  ወይ መንግሥት!» ነው ያሉት። ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚ በቃሉ አንተነህም፤ «መንግሥት እራሱ ባልሰማ እያለፈ ነዉ ባይሆንማ መልስ ለመስጠት አያፍርም ነበር ።» ብለዋል።  ጥላዬ ከበደ ግን «እንዴት እንተማመን ሁሉ ፈራጅ!» ይላሉ። ጥቃት ያደረሰውም ሆነ የደረሰበት እየተባለ የሚነገረው ግራ ያጋባቸው የመሰሉት ኢብራሂም አብዱ በበኩላቸው፤ «እባካችሁ በሰው ሕይወት ላይ የድብብቆሽ ጨዋታ ይቅርባችሁ፤ አያስፈልግም» በማለት ይመክራሉ። አክለውም፤ «በወለጋ የደረሰውን ውድመት የሚያጠና ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል።» ይላሉ። በዚሁ በፌስቡክ ብርሃኔ ገብረኢየሱስ ሀብቱ፤ «ዱሮ ያልነበረ ግጭት ተከባብረው እየኖሩ ሳለ በሁለቱ ብሔሮች መካከል አሁን ምን አመጣው?» በማለት ጠየቁ፤ አንተነህ በትርፍ፤ «እኔ ወለጋን በእንደዚህ አይነት መልኩ አልነበረም የማውቃት፤ ማኅበረሰቡ መልካም አስተሳሰብ ቀና፤ ሩህሩህ እንደነበር ነው የማውቀው። አሁን ከየት የመጣ ነው መጥፎ ነገር የምሰማው? እባካችሁ እንደድሯችን።» ብለዋል። አንሙት ሁንዴ ደግሞ የሚታየው ጥቃት እና ግጭት መነሻው ሌላ ነው ባይ ናቸው፤ «የመሬት ደላሎች እና ሌቦች ባለሥልጣናት ተልእኮ ነው ይሄን ግጭት እንዲነሳ የሚቀሰቅሱት !! ቄሮ የማንም መጠቀሚያ አይደለም መቼ መነሳት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል !!!» ብለዋል። ሀዩ ወሎዬ ግን ፤ «እስከመቸ?» በማለት ይጠይቃሉ። ኢሳያስ ይልማም ሌላ ጥያቄ አቅርበዋል፤ «አካባቢውን የሚቆጣጠር የመንግሥት አካል የለም ወይ ?» የሚል።

Ukraine Krieg - Kherson
የኤሌክትሪክ መስመርምስል Metin Aktas/AA/picture alliance

በዚህ ሳምንት ከወደ ኢትዮጵያ የተሰማው መልካም ዜና መቐለን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች ከ18 ወራት በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማግኘት ጀመሩ የሚለው ነው። ይህን የሰሙት ይርጋለም ጸጋዬ፤ «ደስ ይላል» ሲሉ፤ ዮናስ ኢክንዴም እንዲሁ፤ «ደስ የሚል ዜና።» ነው ያሉት። ዓለሙ አበበም እንዲሁ በፌስቡክ፤ «በጣም ደስ ይላል እርቅ ማለት እንዲህ ነው።» ብለዋል። ተካ ተሾመ ደግሞ፤ «ደስ ይላል፤ የትግራይ ህዝብ እንኳን ደስ ያለህ» ሲሉ ሀብታሙ ኑኑ በበኩላቸው፤ «እንኳን ደስ ያላችሁ በሉልኝ» ይላሉ። አሸናፊ አረጋዊም፤ «እናመሰግናለን ሽረ፣ሑሞራ ፣ ማይካድራ ሙሉ ትግራይ ያርገው ስልክም ጭምር አርጉት..!!» ይላሉ።

 አጥናው አቡሀይ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ የሚሉት እንዲህ ነው፤« የመንግሥት ሆደ ሰፊነት ይህን ያክል ነዉ!!! ሁሉም የትግራይ ማኅበረሰብ አሁን ለመጣዉ ሰላምና ለተጀመረዉ መሰረተ ልማትና ልማት ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የድርሻዉን መወጣት አለበት!!!!!» መርከብ አግአዚ ደግሞ የጎደለውን ነው የሚጠቁሙት፣ «ግን ስልክ አይሠራም» በማለት። የአብዮት በቀለ አስተያየት ደግሞ ይለያይል፤ «ሰላሙ ጥሩ  ነው፤ ግን በትግራይ ጦርነት መብራት ያጣው አርማጭሆ ምን አጠፋ ?።» ይላሉ። ተስፋዬ ጆርጊም እንዲሁ፤ «ወልቃይት እና ሁመራ አካባቢዎች ከሶረቃ ጀምሮ እሰከ አብረሃ ጅራ ለሁለት ዓመት ያክል በጨለማ ውስጥ ናቸው። እንድረስላቸው አሁንም።» ብለዋል።

Symbolbild Facebook
ፌስቡክምስል Joel Saget/AFP/Getty Images/Newscom/picture alliance

ሞሮኮ ቀተር በምታስተናግደው በዘንድሮው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ተጋጣሚዋን የስፔን ብሔራዊ ቡድንን በፍጹም ቅጣት ምት የግብ ብልጫ አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜው ያለፈች ብቸኛ አፍሪቃዊት ሀገር መሆኗ ለብዙዎች ደስታ ፈጥሯል። ምንም እንኳን የተለያዩ የዜና አውታሮች አረብ አፍሪቃዊቱ ሞሮኮ እያሉ ከአረብ ጋር ያላትን ትስስር እያጎሉ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰች አረባዊት ሀገር እያሉ ቢጠሯትም አፍሪቃውያን ግን የሞሮኮን ውጤት የአፍሪቃ ድል አድርገው ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ተመሳሳይ ስሜታቸውን እየገለጹ ነው።  ዳውዴ አብራር፤ «ድል ለሞሮኮ!» ሲሉ፣ ጁ ሞ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፤ «ምርጥ በረኛ የሚደንቅ ነው» ሲሉ የሞሮኮን ግብ ጠባቂ አድንቀዋል። ይርጋ ምትኬም፤ «ግሩም የአፍሪቃ ቡድን» በማለት የሞሮኮን አፍሪቃዊነት አመላክተዋል። ግርማይ ወንዱ ደግሞ፣ «ማድሪድ የተወለደው ሰው ስፔንን ከዓለም ዋንጫ በዝረራ አስወጣት።» ነው ያሉት። አንተርቢና ሀብ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «አፍሪቃ በሞሮኮ ተክሳለች፣ በቀጣይ በርትታ ከተጫወተች ለዋንጫ ልትደርስ ትችላለች።» ይላሉ። ፈድሉ ጁሀር ደግሞ፤ «ምርኮ ፖርቱጋልን ካሸነፈች ማንም አያቆማትም ፖርቱጋል በጣም ከባድ ነው ዕድል ለሞሮኮ ትሁን።»» በማለት ከወዲሁ መልካሙን ተመኝተውላታል። አበበ ኃይሉ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረውን ያነሳሉ፤ «ከእንግዲህ ስለዋንጫው ብናስብ ምን ይለናል? ስፔኖችም በሰፊ ጎል ሲያሸንፉ እንዲ ብለው ነበር። የእግር ኳስ ስፖርትን ጣፋጭ የሚያደርገው ቀድሞ ውጤትን በምንም ሁኔታ ማወቅ የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ ሞሮኮ ስፔንን ጥላ ታልፋለች ብሎ ገንዘብ የሚያሲዝ በራሱ በሞሮኮ ሀገር እንኳ ማግኘት ይከብዳል። እግር ኳስ በደሜ ውስጥ ይሯሯጣል።» የስፔን ቡድን አሰልጣኝ ሉዊስ ኤነሪኬ ቡድኑ በሞሮኮ ከተሸነፈ በኋላ ከስፔን ብሔራዊ አሰልጣኝነታቸው መሰናበታቸውን የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።የአሰልጣኙን መሰናበት ተንተርሰው አክሱም ዮናስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «እኛ ከዚህ ስንብት ምን እንማራለን ? በአግባቡ ኃላፊነቱን የማይወጣ ሰው ከኃላፊነቱ መነሳት አለበት እና የኛም መሪዎችም ቢማሩ እላለሁ።» ይላሉ። እኛም የዕለቱን ጥንቅር በዚሁ እናብቃ።

Katar WM FIFA 2022 Achtelfinale Marokko vs Spanien Elfmeterschießen
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችምስል Matthew Childs/REUTERS

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ