1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋ ግድያ ማብቂያዉ መቼ ነዉ?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2015

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቅርቡ እንዳሉት ገዳዮች «የኦሮሞና የአማራ ሸኔዎች» ናቸዉ። ጥያቄዉ የገዳዮች ማንነት፣ የአገዳደሉ ዘግነኝነት፣ የሟች፣ቁስለኛ፣ ስደተኞች ስንትነት አይደለም። መንግስት ግድያዉን ሲሆን በሰላም ካልሆነ በኃይል ማስቆም ያልተቻለዉ ወይም ያልፈለገዉ ለምንድን ነው ነዉ?

https://p.dw.com/p/4LVKg
Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የወለጋዉ ግድያና ማፈናቀል ዛሬም መፍትሔ አላገኘም

በተለያዩ የወለጋ ዞኖች የሚደረገዉን ግጭትና በዘር ላይ ያነጣጠረ ግድያን ለማስቆም መንግስት ሁነኛ ርምጃ እንዲወስድ የሚደረገዉ ግፊትና ጥሪ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነፃ ዉጪ ጦር  ወይም ኦነግ ሸኔ በተደጋጋሚ በሚከፍተዉ ጥቃት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።የአማራ ታጣቂዎችም የኦሮሞ ተወላጅ ሰላማዊ ገበሬዎችን መግደል፣ማፈናቀላቸዉ እየተዘገበ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

ቡና፣ቅመማ ቅመም፣እሕል፣ አትክልት ይመረትበት የነበረዉ ያ ዉብ ለም ምድር ደም፣ የየዋሕ ገበሬ፣ የአቅመ ቢስ አዛዉንት፣ የሴት፣ሕፃናት ደም እየጠጣ፣ ደም ሲጠማ፣ ወርቅ የተነጠፈበት ጉድባ-ሸለቆ አስከሬን ሲታጨቅበት እነሆ ሶስት ዓመት አለፈዉ።ወለጋ።ላንዳዶችማ  እየዬም ሲደላ ነዉ-ዓይነት ነዉ።

«እስከ አሮ፣እስከ ኖሌ-----ቤት እየተቃጠለ ነዉ።እሬሳቸዉ እስካሁን አልተነሳም----አሁንም ያልተቀበሩ ሰዎች አሉ።»
ጉተን፣ጊዳ አያና፣ኪረሙ፣ሆሮ ጉዱሩ፣አሙሩ፣ጊምቢ፣ነጆ ሌሎች አካባቢዎች በአይን ምስክሮች ግምት በአማካኝ በየሳምንቱ መቶዎች እየተገደሉ ሺዎች ይፈናቀላሉ።

ብዙ ጊዜ እንደሚባለዉ ገዳዮች የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ታጣቂዎች ናቸዉ።ምናልባት የአማራ ታጣቂዎች፣ የመንግስት ኃይላት ሊሆኑ ይችላሉ።አብዛኞቹ ሟች ተፈናቃዮች ግን ረሐብን ሸሽተዉ፣ከአርባ-ሐምሳ ዓመታት በፊት ከተሰደዱ ደሐ ገበሬዎች የተወለዱ መከላከያ የሌላቸዉ ደካሞ፣ የዋሆች መሆናቸዉ አላነጋገረም።ለቁስለኞች መታከሚያ፤ ለተፈናቃዮች መጠለያ፣ ለሕፃናት መሸሸጊያ ቀርቶ የሚላስ-የሚለበስ ማግኘት  ፈተና ነዉ።

 «ከማሳ ያልገባ ቦቆሎ፣እየተዘነጠለ፣ እየተፈለፈለ በበርሜል እየተቀቀለ ነብስ ለማቆያ በማንካ እየተጨለፈ ነዉ ለሕፃናትና ለሴቶች የሚሰጠዉ።የወደቀ አጥንት ሳይቀር ልጆቹ እያነሱ እየጋጡ----- በጣም ነዉ የሚያሳዝነዉ»
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቅርቡ እንዳሉት ገዳዮች የኦሮሞና የአማራ ሸኔዎች ናቸዉ።ጥያቄዉ የገዳዮች ማንነት፣የአገዳደሉ ዘግነኝነት፣ የሟች፣ቁስለኛ፣ ስደተኞች ስንትነት አይደለም።መንግስት ግድያዉን ሲሆን በሰላም ካልሆነ  በኃይል ማስቆም ያልተቻለዉ ወይም ያልፈለገዉ ለምንድነዉ-ነዉ?

Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

መንግስትን ከኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ሸማቂዎች ጋር ለሽምገል  ሞክረዉ ከነበሩት አንዱ የኦሮሞ አባገዳዎች ሕብረት ፀሐፊና የክልሉ መማክርት ጉባኤ አባል አባገዳ ጎበና ሆላ እሬሶ አባገዳ ቱለማ መንግስት ሽምግልናዉን አልፈለገም ይላሉ።

«የኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች ከግጭቱ መነሻ ጀምሮ እስካሁን ድረስ---ግጭቱን ለማቆም ጥረት ብናደርግም አልተሳካም።ከመንግስት በኩል በጦርነት የማንበርከክ ዓላማ ነዉ የያዘዉ።»
 መንበሩን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገዉ በአማራ ተወላጆች  ላይ የሚፈፀመዉን ግድያ ለማስቆም የሚከራከረዉ ድርጅት የሕግ አማካሪ ዶክተር ፍፁም አቻም የለሕ እንደሚሉት ደግሞ መንግስት ግድያዉን ማስቆም አለመቻል ሳይሆን አይፈልግም።

«እንደኛ ግምት (መንግስት እርምጃ) ያልወሰደበት ምክንያት ዶክተር ዓብይ ራሱ እንደዚሕ ዓይነቱን ነገር ስለሚፈልገዉ ይመስለኛል---»
የፌደራሉና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ስለጉዳዩ አስተያየት አንዲሰጡን በተደጋጋሚ ደዉለናል።ስልካቸዉን አያነሱም።የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከዚሕ ቀደም በሰጠዉ መግለጫ ግን የፓርቲ አደረጃጀትና መዋቅር ከሌለዉ ከኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር  ጋር መደራደር እንደሚቸገር አስታዉቋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር ቃል አቀባይ የተባሉትን ግለሰብ በስልክ ለማነጋገር ትናንት በተደጋጋሚ ደዉለን ነበር።እንደ መንግስት ባለስልጣናት ሁሉ እሳቸዉም ስልካቸዉን አያነሱም።
                                       
የመንግስት ባለስልጣናት፣ ደጋፊና ተቃዋሚዎቻቸዉ አዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ አዉሮጳና አሜሪካ  ተቀምጠዉ  ዘር የሚነዳዉን እልቂት ከማስቆም ይልቅ አንዳቸዉ ሌላቸዉን መዉቀስ መክሰሱን እንደ ጥሩ ፖለቲካዊ መርሕ እያነጠሩ-ያጎኑታል።ሕዝብም  ይረግፋል።«ተስፋ አስቆራጭ» ይሉታል አባ ገዳ ጎበና ሆላ እሬሶ።

ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ፣ ደብረ ብርሐን
ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ፣ ደብረ ብርሐንምስል North Shewa Zone communication Office

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ