1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ፕሬዚዳንት የአንድ ዓመት የስልጣን ጉዞ

ሰኞ፣ ጥር 18 2012

የዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼሴኬዲ የስልጣን መንበሩ ላይ ከወጡ አንድ ዓመት ሞላቸዉ። የፕሬዚዳንቱ የአንድ ዓመት የስልጣን ቆይታ ግምገማ በሁለት አይነት አስተያየቶች የተከፈለ ነዉ። ፌሊክ ሼኬሴዲ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ተብለዉ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቦታዉ አልጋ በአልጋ ሆኖ አልጠበቃቸዉም።

https://p.dw.com/p/3WmsF
Demokratische Republik Kongo Kinshasa - Amtseinführung: Felix Tshisekedi wird Kongos Präsident
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ሲይዙ ያለምንም ዉዝግብ በመሆኑ እንደ አንድ እድል ነበር የተቆጠረዉ

የዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼሴኬዲ የስልጣን መንበሩ ላይ ከወጡ አንድ ዓመት ሞላቸዉ። የሼሴኬዲ የስልጣን ሽግግር ያለምንም ችግር ነበር። የፕሬዚዳንቱ የአንድ ዓመት የስልጣን ቆይታ ግምገማ በሁለት አይነት አስተያየቶች የተከፈለ ነዉ። ፌሊክ ሼኬሴዲ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ተብለዉ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቦታዉ አልጋ በአልጋ ሆኖ አልጠበቃቸዉም። በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ዓ.ም የነበረዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እና ዉጤቱም ቢሆን አወዛጋቢ ሆኖ ነዉ ያለፈዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2019 ዓ.ም መጀመርያ የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ፌሊክ ሼኬሴዲ አሸንፈዋል ብሎ ሲያዉጅ ፤ አብዛኞች የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫዉ መጭበርበሩን በይፋ ሲናገሩ ነበር። 

Demokratische Republik Kongo Landwirtschaft Palmöl Feronia Inc.
ምስል Feronia Inc.

እንድያም ሆኖ ፌሊክ ሼኬሴዲ የዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ሆነዉ መንበራቸዉን ሲይዙ ለሃገሪቱ እንደ አንድ እድል ነበር የተቆጠረዉ። ምክንያቱም በተፈጥሮ ማዕድን ኃብት በበለፀገችዉ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ከቅኝ ግዛት ከተላቀችበት ከጎርጎረሳዉያኑ 1960 ዓ.ም ወዲህ ያለምንም ደም መፋሰስ የመጀመርያዉ ሰላማዊ ለዉጥ የተካሄደበት በመሆኑ ነዉ። በምክር ቤት በጥምረት የሚመሩት ሼሴኬዲ በአባላት ምርጫ ላይ ቁጥብነትን ማሳየታቸዉ ነዉ የተነገረዉ። አብዛኛዉ የምክር ቤት መቀመጫን የሰጡት ለፓርቲያቸዉ እና ለቅንጅቱ ለቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ካቢላ “የጋራ ግንባር ለኮንጎ” (FCC)ለተባለዉ ፓርቲ ነው ፡፡

ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼኬሴዲ በቀድሞ የሃገሬቱ ፕሬዚዳንት ካቢላ ላይ ጥገኛ ናቸዉ ። ሼኬሴዲ ስልጣን በያዙ በሦስተኛ ወራቸዉ ነዉ፤ ከቀድሞዉን ፕሬዚዳንት ከጆሴፍ ካቢላ ጋር ያላቸውን የትብብር ስራ በይፋ ያሳወቁት ፡፡ በዚህ ምክንያት ፣ ፌሊክ ሼኬሴዲ ለቀድሞው ገዥ አሻንጉሊት ናቸዉ ተብለዉ ይተቻሉ።  

የኮንጎ ሕዝብ የሃገሪቱ ፖለቲካ እንዲስተካከል ከውጥ ሌላ ብዙም የሚጠይቀዉ ነገር የለም። ምስራቃዊቱ የሃገሪቱ ክፍል ለዓመታት ያለመረጋጋት እና ዉጥረት ይታያል። በሃገሪቱ በሚሊሻዎች፣ አመፀኞች እና በሃገሪቱ የጦር ሠራዊት መካካል አሁንም እርስ በእርስ ግጭት እና ዉግያ ይታያል። በክልሉ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ጀምሮ ከ 2,000 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈዉ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱም የሚታወቅ ነዉ። በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሙስና የዕለት ተዕለት ክስተት መሆኑ ነዋሪዉ በየለቱ ተቃዉሞዉን ይገልፃል። በቤልጂየም ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዣን ክላውድ ሞፑቱ ለ«DW » በሰጡት ቃለ ምልልስ በኮንጎ ከምርጫ በኋላ ትልቅ ለዉጥ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎ ነበር፤ አሁንም በጣም ትልቅ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ይታያል ብለዋል።

«በአብዛኛዉ ያልተሟሉ ተስፋዎች እና ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ነዉ የሚታየዉ። ፕሬዚዳንቱ ለመንቀሳቀስ ለመስራት የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር የላቸዉም። የለዉጥ እቅዱ ሊኖር ይችላል ። አዎ በኮንጎ ባለፉት 20 ዓመታት እንዲህ የሚታይ ሕዝብ ጋር የሚቀላቀል እና ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ከሕዝብ ጋር የሚነጋገር ወደ ዉጭ ሃገራት የሚጓዝ ፕሬዚዳንት በጭራሽ ታይቶ አይታውቅም። አዎ ፣ በእነዚህ ረገድ ፕሬዚዳንቱ መሻሻል ማሳየት ችለዋል። ነገር ግን ይህንን መገለጫ በመንግስት ንግድ ውስጥ ወይም በተቋማት ውስጥ ማሳየት አልቻሉም»

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ካቢላ እንደቀድሞዉ ሁሉ አሁንም ብዙ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ካቢላ እስከሕይወታቸዉ መጨረሻ የሃገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆነዉ ይቀጥላሉ።  በሌላ በኩል የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ ጥምረት የሆነዉ “የጋራ ግንባር ለኮንጎ” ፓርቲ (FCC)ሊቀመንበርም ናቸዉ ። በኮንጎ ከሚገኘዉ 26 ግዛት መካከል የ 24 ግዛት አብዛኛዉ  ነዋሪ የዚህ ፓርቲ ደጋፊ ነዉ። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቬስተር ኢሉንጋ አዲስ የተመሰረተዉን መንግሥት ለማስተዋወቅ ሰባት ወራትን ወስዶባቸዋል»

Symbolbild Masernkrise
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ባለፈው ሰኞ በፕሬዚዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ዳግም ግብግብ መቀስቀሱ በግልፅ ታይቷል። ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼኬሴዲ በጥምር መንግሥቱ ዉስጥ ያለዉ ተቀናቃኝ ፓርቲ የመንግሥትን ሥራ የሚያደናቅፍ ከሆነ ብሔራዊ ሸንጎውን አግዳለሁ ሲሉ ማስፈራርያ አዘል ንግግር አድርገዋል። ይህን ተከትሎም የቀድሞ ፕሬዚዳንት የካቢላ ደጋፊ አፈጉባዔ ዣን ማቡንዳ፤ ህገ-መንግስቱን በመጥቀስ “አንቀጾቹን በተሳሳተ በመረዳት ልንወረዉራቸዉ አይገባም“ ሲሉ ነገሩ የ“ክህደት” ጉዳይ እንዳይሆን አስጠንቅቀዋል። ይህን ንግግር ያዳመጡት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኪንሻሳ ነዋሪ ጠበቃ ሲልቪያን ሉዋሙ ማባያ እንደሚሉት ይህ «በሃገሪቱ የመናገር ነፃነት እጅግ መሻሻሉን አመላካች ነዉ። 

«አሁን ባለንበት ሃገር ፕሬዚደንቱ ያለዉን አመለካከት እና ሃሳብ ሲናገር፤ በፓርላማ አፈ-ጉባዔ ትችት ሲቀርብበት ነዉ የምናየዉ። ይህ ደግሞ በሃገሪቱ ሃሳብን በነፃነት የመናገር መብት ከፍተኛዉ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልካች ነዉ » 

በዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ኮንጎ የኮነራድ አደናወር መታሰብያ ጥናት ተቋም ዋና ተጠሪ ቤኖ ሙሽነር በኮንጎ ትምህርት ቤቶች ያለ ክፍያ እንዲያገለግሉ ሲሉም ተናግረዋል።

«ለምሳሌ በዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ኮንጎ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለ ክፍያ ያገልግሉ የሚለዉን እቅድን ማንሳት እወዳለሁ። ይህ አይነቱ ደንብ በሌሎች በርካታ አፍሪቃ ሃገራት ሥራ ላይ ዉሎአል። በኮንጎ ግን እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። ይህን እቅድ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸዉ ናቸዉ የጀመሩት ነዉ። ይህን ያደረጉት ከጥምር ፓርቲን ለመቃረን ነዉ ። ፕሬዚዳንቱ ግልፅ አቋማቸዉን ማሳወቅ ይችላሉ። »

በአዲሱ ዓመት ይህ ሁሉ ይቀየራል፤ 2020 ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ዓመት ነዉ ሲሉ የ 56 ዓመቱ ፕሬዚደንት ፌሊክ ሼኬሴዲ በአዲሱ የጎርጎረሳዉያን 2020 ዓመት መቀበያ ለሃገሪቱ ሕዝብ ንግግር አድርገዋል። እንድያም ሆኖ አዲሱ 2020 ዓመት በሃገሪቱ ካለፈዉ ዓመት የተለየ ነገር ስለመኖሩ ምንም አይነት ፍንጭ የሚሰጥ ተግባር እስካሁን አልታየም። የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያዉ ሞፑቱ በኮንጎ የኢኮኖሚዉ ሁኔታ ከነበረበት በባሰ መልኩ ያቆለቁላል፤ ኅብረተሰቡ ዉስጥ የተዳፈነዉ ቁጭት እና ንዴት በርትቶ ይወጣል የሚል እምነት አላቸዉ። በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ በሃገሪቱ ቀዉስ እና ግጭት ጎልቶ የሚታይባቸዉን አዉራጃና ወረዳዎች ረስተዋቸዋል፤ ከዚህ ይልቅ በዓለም ሃገራት ጉብኝት ያደርጋሉ ሲሉ የሚተቹዋቸዉ ጥቂቶች አይደሉም።            

Symbolbild:  Schule im Kongo
ምስል picture-alliance/H. Heine

የዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼኬሴዲ በሃገራቸዉ የፖለቲካ ምህዳር እንብዛም ኃይል ተጠቅመዉ ስራን የሚስፈጽሙበት እምብዛም አቅም እንደሌላቸዉ ያዉቃሉ። በዚህም ምክንያት የያዙትን የተሃድሶ እቅድ ዳር ለማድረስ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍን ይሻሉ። ስለዚህ ለለውጡ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ድጋፍ ይፈልጋሉ ሲሉ የሚገልፁት ደግሞ በዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ኮንጎ የኮነራድ አደናወር መታሰብያ ጥናት ተቋም ዋና ተጠሪ ቤኖ ሙሽነር ናቸዉ።  ሙሽነር ለምሳሌ ይላሉ ለምሳሌ አዲሱ ፕሬዝዳንት ኃይላቸዉን ለማጠናከር ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ብድርን ይወስዳሉ ። ብድሩ ለፕሬዚዳንቱ  “ኮንጎን በዓለም አቀፍ ካርታ ዳግም መግባትዋን እና ስኬታማነታቸዉን የሚያሳዩበት ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ