1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ወረርሽኝ በጀርመን ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ ሰኔ 3 2012

ጀርመን በምጣኔ ሐብቷ የኮሮና ወረርሽኝ ካሳደረው ተፅዕኖ ለማነቃቃት 750 ቢሊዮን ዩሮ አጽድቃለች። ከዚህ ውስጥ 156 ቢሊዮን ዩሮ ተጨማሪ በጀት ሲሆን 600 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ በወረርሽኙ ሳቢያ ችግር ውስጥ ለገቡ የቢዝነስ ሥራዎች ማረጋጊያ በብድር መልክ የሚቀርብ ነው።

https://p.dw.com/p/3dacI
Bundestag Abgeordnete applaudieren medizinischen Helfern
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

የኮሮና ወረርሽኝ በጀርመን ኤኮኖሚ

የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጥምር መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝን ተቋቁሞ የጀርመን ምጣኔ ሐብትን ለማነቃቃት 750 ቢሊዮን ዩሮ አፅድቋል። ከዚህ ውስጥ 156 ቢሊዮን ዩሮ ተጨማሪ በጀት ሲሆን 600 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ በወረርሽኙ ሳቢያ ችግር ውስጥ ለገቡ የቢዝነስ ሥራዎች ማረጋጊያ በብድር መልክ የሚቀርብ ነው።

የጀርመን መንግሥት ያጸደቀው ተጨማሪ በጀት ሙሉ በሙሉ በብድር የሚሸፈን ነው። የጀርመን መንግሥት የገንዘብ መጠኑን ለመበደር የአገሪቱን ምክር ቤት ማስፈቀድ ነበረበት። ከአስራ አንድ ዓመታት ገደማ በፊት በጀርመን ሕገ-መንግሥት በተካተተ "የብድር ታኮ" መሠረት የፌድራል መንግሥቱ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የአገሪቱ የምርት መጠን  (GDP) ከ0.35 በመቶ መብለጥ የለበትም። ይኸ በመንግሥት የመበደር አቅም ላይ የተጣለን ገደብ ለመሻገር በሕገ-መንግሥቱ የተካተቱ የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌዎችን መጠቀም ነበረበት።

የጀርመን መንግሥት ለምን ተበደረ?

መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል "በጀርመን ታሪክ የከፋ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ ስለገጠመን ይኸ ገንዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው። የሰባት ሚሊዮን ጊዜያዊ ሰራተኞች እጣ-ፈንታ ብቻውን ያለንበትን ከባድ ኤኮኖሚያዊ ኹኔታ ያሳያል። ስለዚህ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ወኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከቀጠፈው ሕይወት እና ለሕመም ከዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር አኳያ በጀርመን ያሳደረው የከፋ አይደለም ሊባል ይችላል። ይሁንና በሮበርት ኮኽ ኢንስቲትዩት መረጃ መሠረት 184 ሺሕ በላይ ሰዎች በሁሉም የጀርመን ግዛቶች በኮሮና  ተይዘዋል። ከ8700 በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ገቢራዊ ተደርገው የነበሩ ገደቦች ከናጠጡ አገራት ጎራ በምትመደበው የጀርመን ምጣኔ-ሐብት ላይ የከፋ ተፅዕኖ አሳድረዋል። የጀርመን ስታስቲክስ መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚያሳየው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርት በሚያዝያ ወር ብቻ 17 በመቶ ገደማ ቀንሷል። የኢነርጂ እና የግንባታ ዘርፎችም ኮሮና በበረታባቸው ወራት ተቀዛቅዘዋል። በወቅቱ የጀርመን የሥራ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የስራ አጦች ቁጥር ወደ 5.8 በመቶ ገደማ ደርሶ ነበር።

ጀርመን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ገቢራዊ ያደረገቻቸውን ገደቦች በሒደት አላልታ ለምጣኔ-ሐብቱ ማነቃቂያ ብድርን ጨምሮ 750 ቢሊዮን ዩሮ ስታዘጋጅ ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም። መራሒተ-መንግሥቷም የብድሩ ነገር ጥንቃቄ እንደሚሻ ከማስገንዘብ አላፈገፈጉም።

"ጥረታችን በገንዘብ የተደገፈው በመንግሥት ተቀማጭ እንዳልሆነ መርሳት የለብንም። አዲስ ብድር መውሰድ ነበረብን። ይኸ ማለት በመጪዎቹ አመታት ጥሩ የበጀት አስተዳደር ያስፈልገናል። በጀርመን የከፋ የኤኮኖሚ ቀውስ በተፈጠረበት በዚህ ወቅት ግን በወኔ እና በቁርጠኝነት መስራት አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

የጀርመን መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ ከተቀመጠለት የብድር ጣሪያ ሲሻገር ከጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያው ነው። በመንግሥት የብድር ጣሪያ ላይ ገደብ የሚጥለው የሕገ-መንግሥቱ ክፍል በምክር ቤቱ አባላት ድምፅ ከታገደ በኋላ መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም  ተጨማሪ 156 ቢሊዮን ዩሮ እንዲበደር ተፈቅዶለታል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ