1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የኮሮና ክትባት በኢትዮጵያ 

ማክሰኞ፣ የካቲት 30 2013

በኢትዮጵያ እስከ ትናንት የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ. ም ባለው ዕለት መረጃ መሰረት 167 ሺህ 133 ሰዎች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘዋል። 2442 ሰዎች ደግሞ በተኅዋሲው ምክንያት መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የጤና ሚኒስቴር ደጋግሞ እንዳለው የቫይረሱ ሥርጭት አሁን ላይ እየጨመረ ይገኛል። 

https://p.dw.com/p/3qP43
Äthiopien | AstraZeneca | COVAX-Impfstoff
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

በኢትዮጵያ እስከ ትናንት የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ. ም ባለው ዕለት መረጃ መሰረት 167 ሺህ 133 ሰዎች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘዋል። 2442 ሰዎች ደግሞ በተኅዋሲው ምክንያት መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የጤና ሚኒስቴር ደጋግሞ እንዳለው የቫይረሱ ሥርጭት አሁን ላይ እየጨመረ ይገኛል። 
ለዚሁ ወረርሽኝ ክትባት ለማግኘት ሲደረግ የነበረው ዓለም አቀፍ ርብርብ ውጤት አስገኝቶ ከተለያዩ ድርጅቶች ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠላቸው ክትባቶች ተመርተዋል። የዓለም ጤና ድርጅት በተለይ ደሃ ሀገራት ይህንን ክትባት እንዲያገኙም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜም ለተለያዩ ሀገራት በመሰራጨት ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያም ኮቫክስ ከተባለው ዓለም አቀፍ የኮቪድ 19 ክትባት ሸማችና አከፋፋይ ጥምረት ያለፈው እሁድ ዕለት 2.2 ሚሊዮን ዶዝ የአስትራ ዜኒካ ክትባትን ተረክባለች። ይህ የመጀመርያ ዙር ክትባት ግልፅነትና ፍትሓዊነትን መሰረት ባደረገው የክትባት አሰጣጥ መርህ መሰረት በተለይ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው እንደ የጤና ባለሙያዎች ፣ በእድሜ መግፋትና ተደራራቢ የጤና እክሎች ውስጥ ለሚገኙ እና ሌሎችም የሥራ ባህርያቸው ቅድሚያ እንዲያገኙ ለሚያስገድድ ሰዎች በቅርቡ በሁሉም ክልሎች መሰጠት ይጀምራል ተብሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ የወረርሹ ስርጭት አዲስ አበባ ከተማ ላይ በስፋት ተመዝግባል። የክትባት ስርጭቱ በሁሉም ክልሎች መሰራጨቱ እንዳለ ሆኖም በተለያየ ችግር በጤና ተቋማት ውስጥ ተገኝተው መከተብ ለማይችሉት ተንቀሳቃሽ የክትባት ሰጪ ግብረኃይል መቋቋሙን የጤና ሚኒስቴር በተለይም ለዶይቼ ቬለ ገልጿል። ኢትዮጵያ እስከ ጎርጎርያኑ 2021 መጨረሻ ከዚሁ ከኮቫክስ ጥምረት በሚገኝ ክትባት ሃያ በመቶ ዜጎቿን የመከተብ ውጥን አላት። ይህ ማለት ካለው የሕዝብ ቁጥር ብዛት አንፃር ይህንን ክትባት የሚያገኙት ጥቂት መሆናቸውን ነው። አሁን የክትባቱ ወደ ሃገር ውስጥ መግባትን ተከትሎ በተለይ ለጤና ባለሙያዎችና በፀና ሕመም ውስጥ ላሉት ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም በሌላ ጎኑ መዘናጋትን የበለጠ እንዳይፈጥርም ከወዲሁ ሥጋት ፈጥሯል። ቀደም ሲል የወረርሽኙ ወደ ሃገር መግባትን ተከትሎ ይታይ የነበረው ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃ በሰው ዘንድ ክትባት ገብቷል በሚል ተጨማሪ መዘናጋት እንዳይፈጥር ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲታይም ተጠይቋል። በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በትናንትናው ዕለት ብቻ 995 ሰዎች በተኅዋሲው ሲያዙ 13 ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ሞተዋል።

Äthiopien | AstraZeneca | COVAX-Impfstoff
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ