1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶስተኛው ዙር የኮሮና ተዋህሲ ክትባት እውነታዎች

ረቡዕ፣ ኅዳር 15 2014

ጀርመንን በመሳሰሉ የአዉሮፓ ሀገራት ሁለቱን የኮሮና ተዋህሲ ክትባቶች የወሰዱ እና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው።የበሽታውን ስርጭት ለመግታት  እነዚህ  ሀገራት ሶስተኛውን የማጠናከሪያ ክትባት በመስጠት ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/43QFs
Coronavirus Impfstoff
ምስል Weber/Eibner-Pressefoto/picture alliance

ድሃ ሀገራት 95 በመቶ የአንደኛውን ዙር ከትባት በመጠባበቅ ላይ ናቸው


የኮሮና  ተዋህሲ መከላከያ ክትባቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሁለት ዙር ሲሰጥ ቆይቷል። ምንም እንኳ ክትባቱ በታዳጊ ሀገራት ብዙ ርቀት ባይሄድም ፤ ባደጉ ሀገራት ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሌላ ሶስተኛ ዙር ክትባት እየተሰጠ ይገኛል።
ሁለቱን የኮሮና ተዋህሲ ክትባቶች የወሰዱ እና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ  በመምጣቱ፤ የአውሮፓ የመድሃኒት አስተዳደርም ይህ የማጠናከሪያ ክትባት እንዲሰጥ ወስኗል።ባለሙያዎችም የመጀሪያውንና ሁለተኛን ዙር  ክትባት ከወሰዱ ስድስት ወራትን ያስቆጠሩ  እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የመከላከያ አቅማቸውን ለማሳደግ ሶስተኛውን የማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህንን ክትባት መስጠት ያስፈለገው በሁለቱ ክትባቶች የተገኙት  የበሽታ ተከላካይ  ፀረ እንግዳ አካላት በደም ውስጥ ቁጥራቸው በጊዜ ሂደት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው።
ይሁን እንጅ  የክትባቱ አስፈላጊነትና ውጤታማነትም በማነጋገር ላይ ነው።ካለፈው ነሀሴ  ወር ጀምሮ ለዜጎቿ ሶስተኛውን ክትባት በመስጠት ላይ በምትገኘው  እስራኤል፤ ተጨማሪ ክትባት በወረርሽኙ ስርጭት ላይ ለውጥ ማምጣቱ እየተገለፀ ነው።በእስራኤል የህክምና ባለሙያና የሀገሪቱ የኮቪድ-19 አማካሪ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር ያየር ሉዊስ ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ።
«የበሽታው ስርጭት ከ10,000 በላይ ነበር። በየቀኑ  ክትትሎች ስለሚደረጉ፤ በጤና ስርዓቱ ላይም ጫና ነበር።በትንሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ  ፅኑ ህሙማን ነበሩ። የሟቾች ቁጥርም እየጨመረ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር  የሶስተኛ ዙር ማበረታቻ ክትባት  ዘመቻ የተጀመረው። አሁን በበሽታው የመያዝ  እና የመሞት ዕድል  በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው። ስለዚህ በጣም ውጤታማ ነበር ማለት እላለሁ።». 
ባለሙያው እንደሚሉት በሀገራቸው እስራኤል ፣አራተኛው የኮሮና ተዋህሲ ማዕበል የተገታው በሶስተኛው ዙር ክትባት ሲሆን፤ ይህም ብዙ ሰዎችን በበሽታው ከመያዝ እንዲሁም በፅኑ ከመታመም  ታድጓል።
ሁለቱን ክትባቶች የወሰዱ እና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ የሚገኝባቸው ጀርመን እና ሌሎች በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ያሉ ሀገራትም፤በእስራኤል የተገኘውን አይነት ውጤት ተስፋ ያደርጋሉ።ከሀገሪቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የኮቪድ-19 የበሽታ ሁለተኛው ዙር  የመከላከያ ክትባት ከተወሰደ ከጥቂት ወራት በኋላ የመከላከል አቅም ማሽቆልቆል ሊጀምር ይችላል።ነገር ግን ከሶስተኛው የማጠናከሪያ ክትባት በኋላ እንደገና ከፍ ማለቱን ተመራማሪዎች ገልፀዋል። 
ያ ማለት ግን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክትባቶች ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም።ምንም እንኳ ሁለቱን ክትባቶች  ወስደው በተዋህሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር  እየጨመረ ቢመጣም፤በኮቪድ-19 በሽታ በፅኑ ከመታመም በበቂ ሁኔታ ይከላከላሉ።በዚህም ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል ባለመግባት የሆስፒታል አቅምን ለሌሎች ነፃ በማድረግ ለተከተበው ሰው ብቻ ሳይሆን የሌላ ሰውን ህይወትም ሊታደግ ይችላል።እንደ ተመራማሪዎቹ ሶስተኛውን የማጠናከሪያ ክትባት የወሰደ ሰው ደግሞ ወረርሽኙን ለማቆም የበለጠ አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም በጊዜ ሂደት የበሽታ መከላከሉ ምላሽ ከመጀመሪያው ወይም ከሁለተኛው ክትባት የበለጠ  ጠንካራ ነውና።
 « ይህ በሌሎች ክትባቶች ላይ ያየነው አስደናቂ ክስተት ነው። በኮቪድ ክትባትም ቢሆን የመጀመሪያዎቹን ሁለት የክትባቶች አስር  እና  ሦስት ሳምንታት ቆይተው በወሰዱት ሰዎች መካከል ትልቅ  ልዩነት መኖሩን የሚያሳይ መረጃ አለ።ለምሳሌ፣ ይህ  በብሪታንያ  ታይቷል።ስለዚህ እንደሚሰጥበት ጊዜ የበሽታ መከላከል ምላሽን የማጠናከር ጉዳይ አለ። ሰፊ የጊዜ ልዮነት ሲኖር  የማጠናከሪያ ክትባቱ የሚሰጠው በሽታ የመከላከል ምላሽ  ይጨምራል። እናም የበለጠ ጠንካራ እና ረጅም ጊዜ እንዲቆይ ያደርገዋል።» 
ያም ሆኖ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ  እና ማንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የኮሮና ተዋህሲን የመከላከል አቅም አለኝ ብሎ ማሰብ እንደሌለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ ። ምክንያቱም አሁንም ቢሆን በሽታውን የመከላከል አቅም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ላይሆን ይችላልና።በዚህ የተነሳ አራተኛው ዙር ክትባት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል የሚሉ አሉ። ባለሙያው ዶክተር ሊውስ ግን ይህንን ለማለት «ስፓይክ ፕሮቲን»የተባለውን ተዋህሲውን ለመከላከል የሚያስችለውን አቅም በየጊዜው ያለበትን ደረጃ መፈተሽና መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል ይላሉ።
«አራተኛው ክትባት አስፈላጊ መሆኑን አላውቅም።ነገር ግን  የእስራኤል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየሰበሰበ ያለውን መረጃ መከታተል እና ማየት አለብን። በዚህ አመት ሰኔ ወር ላይ እስራኤል ያቀረበችው መረጃ በጣም ዘርዘር ያለ ነበር። ታውቃለህ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ወቅት ነበር  የሶስተኛው ዙር ክትባት መረጃ የወጣው። መጀመሪያ አካባቢ በዓለም ዙሪያ ሀሳቡ ሲተች ነበር። ነገር ግን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተደረገው ትንታኔ ትክክል ነበር ። የዋናው የ«ስፓይክ ፕሮቲን» የመከላከል አቅም እያሽቆለቆለ እንደነበረ ባደረግነው ግምግማ በትክክል ያየነው ክስተት ነበር።ስለዚህ ያንን መረጃ መከታተላችንን  መቀጠል አለብን ብዬ አስባለሁ።»
ስለ ሶስተኛው ክትባት ሲነሳ የትኛውን የክትባት አይነት መጠቀም የተሻለ ነው።የሚለው ጥያቄ አብሮ ይነሳል።ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንዶች የሞደርናን ክትባት ለማጠናከሪያነት መጠቀም የተሻለ ነው ሲሉም ይደመጣል።ባለሙያው ግን ይህንን የሚደግፍ የተለዬ ሳይንሳዊ ትንታኔ አለመኖሩን ይገልፃሉ።
«ትልቅ ልዩነት ያለ አይመስለኝም። እስራኤል ብዙ የፋይዘር  ክትባት እንዳላት አውቃለሁ።ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች የሞደርናን ክትባት የሚወስዱት  ምክንያቱ የክምችት ጉዳይ ነው ብዬ እገምታለሁ ። ይህንን ለማድረግ የተለየ ሳይንሳዊ ምክንያት ያለ አይመስለኝም። እንደሚታወቀው ፣በ ዩስ አሜሪካ የተለያዩ ክትባቶችን የማቀላቀል  እና የማመቻቸት ስልት የተፈቀደ ነው።ስለዚህ እንደ ማጠናከሪያም ቢሆን  የተለያዩ ክትባቶች ማግኘት ትችላለህ።» 
ሌላው ከሶስተኛው ክትባት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ክትባቱ ልውጥ የኮሮና ተዋህሲያንን ለመከላከል ያገለግላል ወይ?የሚለው  ነው።ባለሙያው እንደሚሉት ምንም እንኳ ክትባቱ ለልውጥ ተዋህሲያን ተብሎ የተሰራ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ  ውጤት ታይቶበታል።
«ለልውጥ ተዋሲያን የማጠናከሪያ ክትባቶች የተለዩ እና እነሱ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው።ምንም እንኳን ለዴልታ ተዋህሲ ተብሎ በተለዬ ሁኔታ የተሰራ ባይሆንም ማጠናከሪያ ክትባቱ በመከላከሉ ረገድ በጣም ውጤታማ ነበር። ስለዚህ ክትባቱ በተለየ ሁኔታ ተስተካክሎ ቢሰራም፤  የተለየ ምላሽ ላይኖር ይችላል።ስለዚህ ማለት የፈለኩት፣በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ እንደሚያስፈልግ እንኳን ግልጽ አይደለም ብዬ እገምታለሁ። በሁለተኛ ደረጃ፣ በእነዚህ የክትባት ልዩነቶች ላይ ምርምር እና ሙከራ እየተደረገ ነው።ነገር ግን ፋይዘር እና ሞደርናም ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን እርግጠኞች አይደሉም።» 
በሌላ በኩል ከሶስተኛው ዙር የኮሮና ተዋህሲ ክትባት ጋር ተያይዞ የድሃ ሀገራት የክትባት ፍትሃዊነት ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። በጀርመን የማጠናከሪያ ክትባት ያገኙ ሰዎች  የመጀመሪያ ክትባት ካገኙ  የድሃ ሀገራት ዜጎች ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ የበለጠ ነው።በመላው ዓለም  ከ27 ድሃ ሀገራት የመጀመሪያ ክትባት የወሰዱ ሰዎች  4.6  በመቶ ሲሆን፤ በጀርመን ብቻ  5.6% በመቶ የሚሆኑት ጀርመናውያን ሶስተኛውን ክትባት አግኝተዋል።
እናም የመጀመሪያውን የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ለሚጠባበቀው እና  95% በመቶ ለሚሆነው የድሃ ሀገራት ሕዝብ ሶስተኛው ክትባት ጉዳዩ አይደለም።ነገር ግን በክትባት መብታቸው የጥፋተኝነት ስሜት የተሰማቸው የሀብታም ሀገራት ዜጎች ፤ ገንዘብ መለገስ፣ ተቃውሞዎችን እና አቤቱታዎችን ማደራጀት ወይም የምርጫ ክልል ወኪሎቻቸውን ማነጋገር አንዳለባቸው እየወተወቱ ነው።ነገር ግን ይህ  መሆን ያለበት ያለምንም ማመንታት  ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ መሆኑን ጭምር እያሳሰቡ ነው። 

Deutschland Stuttgart Corona-Impfung
ምስል AFP
Pfizer-BioNTech COVID-19 Impfstoff
ምስል Pfizer/AP Photo/picture alliance
Coronavirus Impfstoff
ምስል Weber/Eibner-Pressefoto/picture alliance
Deutschland Erfurt Corona-Impfung
ምስል Jens Schlueter/Getty Images

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ