1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተከርቸም ዳፋ ማን ላይ ይበረታል?

ረቡዕ፣ መጋቢት 23 2012

በኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ሳቢያ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያ የሚሰሩባቸው ዘርፎች ጥብቅ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። የሕዝብ ማጓጓዣዎች፤ ገበያዎች፤ አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላልተወሰነ ጊዜ በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫ እንዲቆሙ ተወስኗል። እነዚህ ክልከላዎች የዕለት ጉርሳቸውን በለት ተለት ሩጫቸው በሚያበሱ ዜጎች ላይ ምን አይነት ጫና ያሳድራሉ?

https://p.dw.com/p/3aGzI
Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የኮሮና ተከርቸም ዳፋ ማን ላይ ይበረታል?

የኢትዮጵያ የክልል መንግሥታት በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ የሕዝብ መጓጓዣ መሰል አገልግሎቶች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በጊዜያዊነት እንዲቆሙ አድርገዋል። የወረርሽኙ ሥጋት ቀድሞውም ፈተና ውስጥ በከረመው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ላይ ጫና ማሳደር የጀመረው ቀደም ብሎ ነው። በአገሪቱ ገበያ ሎሚ እና ነጭ ሽንኩርት የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋቸው አሻቅቦ ታይቷል። በገበያው አቅርቦት እና ፍላጎትም መጣጣም ጉድለት የታየባቸው ሸቀጦችም ነበሩ።

እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ግምገማ ሰርቶ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በምን ፍጥነት ሊስፋፋ እንደሚችል ያስቀመጠው ቅድመ-ትንበያ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም። ይሁንና የክልል መንግሥታት ጥብቅ ክልከላዎች ገቢራዊ አድርገዋል።  በደቡብ ክልል አገር አቋራጭ የሕዝብ መጓጓዣዎችን ጨምሮ በወረዳዎች እና በዞኖች መካከል የነበሩ እንቅስቃሴዎች ተከልክለዋል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የሐረሪ ክልል እንደ ደቡብ ሁሉ የሕዝብ መጓጓዣዎች አግደዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገበት የትግራይ ክልል ከከተማ ወደ ገጠር፤ ከገጠር ወደ ከተማ አሊያም ከከተማ ወደ ከተማ መንቀሳቀስ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። በኦሮሚያ ገጠሩን ከከተማ ከተማውን ከገጠር የሚያገናኝ ገበያ ጭርሱን አይቆምም። 

የክልል መንግሥታት የኮሮና ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ለማገድ ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች በሺሕዎች በሚቆጠሩ ዜጎች የለት ተለት ኑሮ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ናቸው። ወትሮም ጤና ርቆት የሰነበተው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ እንዴት መቋቋም ይችላል? የአገሪቱ ኤኮኖሚ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፣ የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መጓደል ሲወዘውዙት ብዙ ክረምቶች አለፉ። የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት እና ወረርሽኙን ለመከላከል ገቢራዊ የተደረጉ ክልከላዎች ምን አይነት ጫና ያሳድራሉ?

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ