1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተኅዋሲ መከላከያ ክትባት በአፍሪቃ

ሐሙስ፣ የካቲት 11 2013

ከሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት በተወሰኑ የአፍሪቃ ሃገራት መከፋፈል እንደሚጀምር የአፍሪቃ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ምዕከል በምህጻሩ CDC አስታወቀ። የድርጅቱ ሃላፊ ጆን ንኬንጋሶንግ እንዳሉት አስታራዜኒካ የተባለው ክትባት 20 ለሚሆኑ ሃገራት ይከፋፈላል።

https://p.dw.com/p/3pZQ1
Weltspiegel 18.02.2021 | AstraZeneca - Impfstoff
ምስል Stephane Mahe/REUTERS

ከሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት በተወሰኑ የአፍሪቃ ሃገራት መከፋፈል እንደሚጀምር የአፍሪቃ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ምዕከል በምህጻሩ CDC አስታወቀ። የድርጅቱ ሃላፊ ጆን ንኬንጋሶንግ እንዳሉት አስታራዜኒካ የተባለው ክትባት 20 ለሚሆኑ ሃገራት ይከፋፈላል፤ በክትባቱ መርሃግብርም የጤና ሠራተኞች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ንኬንጋሶንግ ክትባቱ ከ54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት ለየትኛዎቹ እንደሚሰጥ ግን አላሳወቁም። እንደ ኃላፊው ከሚቀጥለው ሳምንት አንስቶ የሚከፋፈሉት ከሕንድ ይመጣሉ ከተባሉት 7 ሚሊዮን ክትባቶች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አንድ ሚሊዮን የአስትራዜኒካ ክትባቶች ናቸው። አስቀድሞ የገዛችውን የአስትራዜንካን ክትባት በሌላ ዓይነት ክትባት የተካችው ደቡብ አፍሪቃ የክትባቱን መርሃ ግብር መጀመሯ ተዘግቧል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት አስትራዜኒካ ደቡብ አፍሪቃ የተገኘውን ልውጡን የኮሮና ተኅዋሲ የመከላከል አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቋል። በዚህ የተነሳም ደቡብ አፍሪቃ ለጊዜው የአስትራዜኒካን ክትባት መስጠት አቁማለች። የማትጠቀመውን ይህን ክትባትም ለሌሎች ሃገራት ትሰጣለች ተብሏል። እስካሁን ልውጡ የኮሮና ተኅዋሲ ያልተመዘገባበቸው 12 ሃገራት ክትባቱን ከደቡብ አፍሪቃ የመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ማትሺድሶ ሞቲ አስታውቀዋል። የብሪታኒያ  ልውጥ የኮሮና ተኅዋሲ በ8 የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ተገኝቷል። ንኬንጋሶንግ የአስታራዜኒካ ክትባት  በጣም ውጤታማ ነው ሲሉ ዛሬ ተናግረዋል። የአስታራዜኒካ ክትባት እንደሌሎቹ ክትባቶች በከፍተኛ ቅዝቃዜ መቀመጥ ስለሌለበት በተለይ በመልማት ላይ ላሉ ሃገራት ጠቃሚ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በአፍሪቃ በኮሮና ተኅዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3.8 ሚሊዮን ገደማ ሆኗል። በሽታው የገደላቸው ቁጥር ደግሞ ወደ 100ሺህ እየተጠጋ ነው። በአፍሪቃ የኮቪድ 19 ሥርጭት ፣ ከዓለም አቀፉ የወርርሽኙ ሥርጭት 3.5 በመቶ ነው።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ