1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ሥርጭት በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ መጋቢት 25 2012

የኢትዮጵያ የማሕበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እስካሁን ከሰራቸው 1200 በላይ ምርመራዎች 35 በኮሮና የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል። ይኸ ከጅቡቲ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ያነሰ ነው። የኢትዮጵያ ተቋማት ምርመራውን ለማድረግ ያለባቸው የአቅም ውስንነትና የጤና ሚኒስቴር የሚከተለው ስልት ቁጥሮቹ የኮሮናን እውነተኛ ገፅታ ላያሳዩ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል

https://p.dw.com/p/3aPn4
Coronavirus in Äthiopien Isolationszentrum in Mekelle
ምስል DW/M.H. Brhane

የጤና ሚኒስቴር በ24 ሰዓታት ካደረጋቸው 74 ምርመራዎች ስድስት በኮሮና የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጧል። ዕድሜያቸው ከ28 እስከ 56 ሲሆን ከአንዷ በቀር አምስቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። ከስድስቱ አራቱ ጭርሱን ከኢትዮጵያ ወጥተው አያውቁም። የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው አራቱ ሰዎች በኮሮና ከተያዘ ሰው ግንኙነት ይኑራቸው አይኖራቸው አይታወቅም።  

የካቲት 25 ቀን 2012 ዓም ከቡርኪና ፋሶ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ጃፓናዊ በኮሮና መያዛቸው በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተረጋገጠ የመጀመሪያው ግለሰብ ናቸው። ከዚያ ወዲህ ባሉት ቀናት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር እና አዲስ ቅዳም የተባለች አነስተኛ ከተማ በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ተገኝተዋል። ባለፉት 22 ቀናት በኢትዮጵያ በኮሮና መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች 35 ደርሷል።

ይኸ ቁጥር ግን እውነተኛውን መረጃ ማሳየት የመቻሉ ነገር አጠያያቂ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ወንደሰን አሞኜ  «ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቁጥር እውነተኛውን ገፅታ ያሳያል ብዬ መናገር ይከብደኛል። ምክንያቱም የመመርመር ብቃታችን ሌሎች አገሮች ከደረሱበት ብቃት አንፃር ዝቅተኛ ነው። ምርመራ ልናደርግባቸው የምንችላቸው ላብራቶሪዎች በብቃት ያሉን በጣም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

Äthiopien Flughafen Addis Abeba | Sicherheitsmaßnahmen gegen Coronavirus
ምስል Getty Images/L. Dray

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 1200 በላይ ምርመራዎችን አድርጋለች። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሁለት ተከታታይ ቀናት ባደረጋቸው ምርመራዎች መካከል ያለው ልዩነት ዘጠኝ ብቻ ነው። ተቋሙ መጋቢት 24 ቀን 65 በማግሥቱ ዛሬ ደግሞ 74 ምርመራዎች አድርጓል። ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካ ይደረግ የነበረው የኮሮና ምርመራ በኢትዮጵያ የተጀመረው መጋቢት ዘጠኝ ገደማ ነው። በየኢትዮጵያ የማሕበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተገድቦ የቆየው ምርመራ ወደ ክልሎች እና ሌሎች ተቋማት ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው ዘግይቶ ነው። ይኸ ባለሙያዎቹ ቁጥሮቹ የኢትዮጵያን እውነታ ላያሳዩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሪያቸውን ካበረቱ መካከል ይገኝበታል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው ምርመራዎች ውስንነት የጤና ሚኒስቴር ይፋ ያደረጋቸው ቁጥሮች እውነታውን ላያሳዩ ይችላሉ በሚለው ይስማማሉ። «አሁን እየተከተልን ያለንው ወረርሽኙ ደረሰብኝ የሚሉ ሰዎች እየነገሩህ የምትሰራው የበሽታ መቁጠር ስርዓት ነው። በሽተኞችን የምታገኘው እነሱ ምልክት አለን፤ መመርመር አለብን የሚል መረጃ ሲሰጡ ነው» ሲሉ ሁለተኛውን ዕክል አስረድተዋል። ይኸ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ነው። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት አንድም በኢትዮጵያ ወደ ሕክምና ተቋም የመሔድ ልምድ ውስን በመሆኑ አንድም በኮሮና ጠባይ የተነሳ። 

ዶክተር ወንደሰን «ከሌላው በሽታ ለየት የሚያደርገው በበሽታው የታመመ ሰው ሁሉም ምልክት ላይኖርበት ግን በሽታውን ሊያሰራጭ ይችላል» ሲሉ ፈታኙን ነገር ይገልፃሉ። የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ ወረርሽኙን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ደጋግመው እንዳሉት በተለይ ወጣቶች በኮሮና ተይዘው ምንም ዓይነት ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። 

በኬንያ፣ ጅቡቲ እና ርዋንዳ በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከኢትዮጵያ የላቀ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ወረርሽኝ ወደ በረታባቸው የቻይና፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከነበሩት በረራዎች አኳያ ኢትዮጵያ የበለጠ ለወረርሽኙ ተጋላጭ ትሆናለች። ይኸ እንደገና የኢትዮጵያን ቁጥሮች ጥርጣሬ ውስጥ ይጥላቸዋል። 

የኮሮናን ሥርጭት እና የሚያስከትለውን ሞት በመጋፈጥ ረገድ የተሻለ ሰርታለች የምትባለው ጀርመን በሳምንት 500,000 ምርመራዎችን ማድረግ ትችላለች። እንዲያም ሆኖ የአገሪቱ ሳይንቲስቶች የተሕዋሲውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ከዚህ በላይ ማድረግ ይጠበቅባታል ሲሉ መክረዋል። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ