1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ሥርጭት ሥጋት በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች

ማክሰኞ፣ መጋቢት 29 2012

ግሪክ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች የኮሮና ተህዋሲ እንዳይዛመት አቴንስ የአውሮጳ ህብረትን ድጋፍ እየጠየቀች ነው።የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ በሰዎች በተጨናነቁት የግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች ኮሮና የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት አስቸኳይ እርምጃዎች እንደሚወስድ ይናገራል። የግሪክ ባለሥልጣናት ግን ስጋታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም።

https://p.dw.com/p/3abVK
Griechenland Flüchtlingslager auf Lesbos nach Ausschreitungen
ምስል picture-alliance/dpa/A.Tzortzinis

የኮሮና ሥርጭት ሥጋት በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች

የኮሮና ተህዋሲ በየትኛውም ስፍራ የሚገኝ የሰው ልጅ ጭንቀት ሆኗል።በሽታውን ለመከላከል መንግሥታት ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ተግባራዊ አድርገዋል።ከቤት አትውጡ ክልከላዎች አንስቶ ፣ህብረተሰቡ በያለበት አካላዊ ርቀትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድ እየተመከረ ነው።የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ እስረኞች እየፈቱ ነው።ሰዎች ተፋፍገው የሚኖሩባቸው አካባቢዎችም ትኩረት እየተሰጣቸው ነው።ይሁን እና እዚህ አውሮጳ በተለይም በግሪክ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች የኮሮና ሥርጭት እያሰጋ ነው።110 ሺህ ስደተኞች በሚገኙባት በግሪክ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑት በሰዎች በተጨናነቁ የስደተኞች ጣቢያዎች ውስጥ ነው የተጠለሉት።ከመካከላቸው 19 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች የሚገኙበት የሞሪያው መጠለያ አንዱ ነው።ይህም በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች የኮሮና ስርጭት ስጋት እንዲያይል አድርጓል።በተለይም በሁለት የስደተኞች መጠለያዎች በኮሮና የተያዙ ሰዎች ከተገኙ በኋላ ስጋቱ ጨምሯል።በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም መጠለያዎች ተገልለው እንዲቆዩ ተደርጓል።ወደ ግሪክ የሚመጡ ስደተኞችም የኮሮና ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ነው ወደ ሃገሪቱ የሚገቡት ።በተለይ ሌስቦስ ወደተባለችው ደሴት የሚሄዱ ስደተኞች ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጡ እየተደረገ ነው።ከመካከላቸው አንዱ ይህ ኡጋንዳዊ ስደተኛ እንደሚለው በተደረገለት ምርመራ ከተህዋሲው ነጻ መሆኑ ቢነገረውም ለይቶ ማቆያ ውስጥ ነው የሚገኘው።
«በግሪክ መንግሥት እና በዩኤን ኤች ሲ ስር በለይቶ ማቆያ ውስጥ ነው የምንገኘው።መጥተው ሁላችንንም መረመሩን ሁላችንም ከተህዋሲው ነጻ ነበርን።ሆኖም ለ14 ቀናት ተገልለን እንድቆይ ተደረግን።»
በቅርቡ ወደ ግሪክዋ ሌስቦስ ደሴቶች የገቡ ከአንድ መቶ ባላይ ስደተኞች የኮሮናን ሥርጭት ለመቀነስ ሲባል ተለይተው እንዲቆዩ ተደርጓል።3ሺህ ስደተኞች በሚገኙበት በሪትሶና ሰሜን ግሪኩ መጠለያ፣ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በኮሮና የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘ በኋላ ስፍራው ተለይቶ እንዲቆይ ተደርጓል። ይህ የሆነውም አንዲት አቴንስ ወልዳ ወደ ጣቢያው የተመለሰች ሴት በኮሮና ተህዋሲ መያዟ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር። ከዚያ በኋላ በዚያ የሚገኙ ስደተኞች ላይ በተካሄደ ምርመራ 20 ዎቹ ላይ በሽታው መኖሩ ሲታወቅ ነው ስፍራው ተለይቶ እንዲቆይ የተደረገው። ባለፈው እሁድም በተመሳሳይ ሁኔታ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ አቅራቢያ በሚገኝ ሌላ የስደተኞች መጠለያ በተህዋሲው የተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ መጠለያው እንዲገለል ተደርጓል። ይህኛው መጠለያ ደግሞ ማላካሳ በተባለው እና ከአቴንስ 45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ 1800 ስደተኞች የተጠለሉበት ስፍራ ነው።የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ እንዳሉት የአውሮጳ ህብረት በስደተኞች መጠለያዎች ያለው ሁኔታ እንዲሻሻል ይበልጥ ሊሰራ ይገባል።ስደተኞቹንም ወደ ሌሎች ሃገራት መወሰድ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል። ሚትሶታኪስ፣ግሪክ ችግሩን ለመፍታት የበኩልዋን ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸው ከአውሮጳ ህብረት በኩል ግን በቂ ድጋፍ አልደረሰንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች  ያለውን ችግር ለመፍታት የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ነው የተናገረው።የህብረቱ የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ኢልቫ ጆሀንሰን በሰዎች በተጨናነቁት የግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች በአንዱ ኮሮና በወረርሽኝ መልክ ቢከሰት ምን ታደርጋላችሁ ተብለው ከዶቼቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ይህ እንዳይከሰት የማናደርገው ነገር አይኖርም ብለዋል።
« ይህን ማስቀረት አለብን።ይህ ቀውስ እንዳይከሰት ሁሉንም ነገር ማድረግ ይገባናል።ለዚህም ነው አሁን ከግሪክ መንግሥት ጋር የአስቸኳይ ምላሽ መርሃ የድርጊት መርሃ ግብር ላይ በጋራ የምንሰራው።ይህ አሁን ሥራ እየዋለ ነው። እናም አሁን ማድረግ ያለብን እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ከመጠለያ ጣቢያው በአስቸኳይ ማስወጣት ነው።ወረርሽኙ በነዚህ መጠለያዎች ከተከሰተ ችግር ላይ እንዳይወድቁ በሆቴሎች በመኖሪያ ህንጻዎች እንዲቆዩ በማድረግ፣በህክምና መሳሪያዎችና በህክምና ባለሞያዎች እንዲሁም በሌሎችም እርምጃዎች በመደገፍ  ነው ችግሩን ለመከላከል  ከግሪክ ባለሥልጣናት እና ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት እንዲሁም ከተመ የስደተኞች ጉዳይ  ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ጋር በቅርበት የምንሰራው።»
የተወሰኑ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ከሳምንታት በፊት በግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች ያለ ወላጆቻቸው ብቻቸውን የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ወጣቶችን ለመከፋፈል  ተስማምተው ነበር።ምናልባት የአውሮጳ ህብረት አሁን እተገብረዋለሁ የሚለው አስቸኳይ መርሃ ግብር እነዚህን የሚያካትት ይሆን ዶቼቬለ ለጆአንሰን የቀረበላቸው ሌላ ጥያቄ ነበር።
«ይህ ለበሽታው እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን በእድሜ የገፉ ሰዎች እና ታማሚዎች ከመጠለያ ጣቢያው ወደ ተሻሉ ወደ ሚባሉ ሆቴሎች የመወስድ አስቸኳይ እቅድ ነው።ሰዎቹ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መጠለያዎቹ ውስጥ አይቆዩም ።ካለወላጅ በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ብቻቸውን የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶችን ከጣቢያዎቹ የማስወጣቱ ጉዳይም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው።እነዚህን ህጻናት ለመቀበል 8 ሃገራት ዝግጁ ናቸው። እናም ልጆቹን ካሉበት የማዛወሩ ሥራ በመጪዎቹ ሳምንታት ይከናወናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።አሁን ልጆቹ ወደ ጊዜያዊ ማዕከላት እየተዛወሩ ነው።በዚያም የኮሮና ምርመራ እየተደረገላቸው ነው።ወደ አባል ሃገራት ለሚካሄደው ዝውውር ዝግጅት ላይ ናቸው።»
እናም ይላሉ ጆአንሰን ከመጠን በላይ በሰዎች በተጨናነቁት መጠለያዎች ስደተኞችን ለመቀነስ ሃገራቱ ያሳዩት ትብብር በጣም ጠቃሚ መልዕክት  እያስተላለፈ ነው።ያም ሆኖ ግን ህብረቱ ለዓመታት በግሪክ በሰቸጋሪ ሁኔታዎች ለቆዩት ስደተኞች መፍትሄ ባለመፈለግ መወቀሱ አልቀረም። ኢልቫ ጆአንሰን በበኩላቸው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
«ሃላፊነቱን ከተረከብኩ አንስቶ አዲስ የስደተኞች እና የተገን ጠያቂዎች ውል ለማዘጋጀት በጣም እየሰራን ነው።ይህንንም ምክረ ሃሳብ በቅርቡ አቀርበዋለሁ።በሁሉም አባል ሃገራት ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ።እኛም ከግሪክ መንግሥት ከግሪክ ባለሥልጣናት እና ከተመ ድርጅቶች ጋር በሰዎች በተጨናነቁት በነዚህ መጠለያዎች ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ለመርዳት እንዲሁም ስደተኞችንም ወደ ሌሎች ሃገራት በመውሰድ እና ወደ መጡበትም በመመለስ በመጠለያዎቹ ያለውን ጫና ለመቀነስ በቅርበት እየሰራን ነው።»
የአውሮጳ ህብረት ደቡባዊ ድንበር ከሚባሉት አንዷ የሆነችው ግሪክ ወደ ሰሜን አውሮጳ የመሻገር ሙከራ የሚያደርጉ ስደተኞች መተላለፊያ እና በርካታ ስደተኞችም የሚገኙባት ሃገር ናት። የግሪክ የተገን አሰጣጥ ሂደት መጓተትና የስደተኞቹም ቁጥር መበራከት ስደተኞች በግሪክ ለመጉላላታቸው በምክንያትነት ይቀርባል።ግሪክ በበኩልዋ ከአቅሜ በላይ ናቸው የምትላቸውን እነዚህን ስደተኞች አባል ሃገራት እንዲከፋፈሉ ስትጠይቅ ቆይታለች።ከግሪክ የመጠለያ ጣቢያዎች አንዳንዶቹ በስደተኞች መጨናነቃቸው ያሳሰበው ኮሮና ከመከሰቱ በፊትም ነው።በግሪክ ለተፈጠረው ለዚህ ችግር ተጠያቂው ማን ይሆናል የተባሉት ጆአንስን ግሪክን ተጠያቂ ቢያደርጉም ሌሎች የህብረቱ አባል ሃገራትም ሃላፊነት እንዳለባቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

Griechenland Insel Lesbos neue Migranten
ምስል AFP/L. Gouliamaki
Ylva Johansson | EU-Kommissarin für Inneres
ምስል imago images/ZUMA Wire/F. Sierakowski
Griechenland Lesbos-Insel Flüchtlingslager Moria-Elaionas
ምስል picture-alliance/ANE

«አዎ ግሪክ ውስጥ ለተፈጠረው ሁኔታ  ሃላፊነቱ የግሪክ መንግሥት ነው።ሆኖም ግሪክ ብቻዋን ምንም ልታደርግ አትችልም።እኛ መተባበር አለብን።የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ብዙ ገንዘብ እየሰጠ ነው።ችግሩ ያለበት ቦታ ለሚገኙ ሰዎች ተጨባጭ ድጋፍ እያደረገ ነው።እነርሱን ለመርዳት ሌት ተቀን እየሰራ ነው።መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተመ ድርጅቶች እየረዱዋቸው ነው።ስለዚህ  እነርሱ እኛ እና የግሪክ መንግሥት እንዲሁም የግሪክ ባለሥልጣናት ሃላፊነት አለብን።በአሁኑ ጊዜም ሁላችንም ለግሪክ እና ሰዎች በታጎሩባቸው መጠለያዎችለሚገኙ ስደተኞች ገቢራዊ የሚሆን ትብብር የማድረግ ሃላፊነት አለብን። »
በጎርጎሮሳዊው 2015 የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ኢጣልያ እና ግሪክ የሚገኙ 160 ሺህ ስደተኞችን ለመከፋፈል ተስማምተው ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላ አሁን ግሪክ በሺህዎች የሚቆጠሩ በአስከፊ ሁኔታ የተያዙ ስደተኞች የሚገኙባት ሃገር ናት።በጊዜያዊው የስደተኞች መከፋፈል ስምምነት ከ28 ቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ሁለት ሦስተኛው ቢስማሙም መጨረሻ ላይ ከግሪክና ከኢጣልያ የተወሰዱት ስደተኞች ወደ 40 ሺህ ገደማ ናቸው።ታዲያ አሁን በሰዎች ለተጨናነቁት የግሪክ የስደተኞች መጠለያዎች ኮሮና መፍትሄ ያመጣ ይሆን?

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ