የኬንያው ጄን ዚ ንቅናቄ ሁለተኛ ዓመት
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2018
ሰኔ 18 ማለትም በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ሰኔ 25 ለበርካታ የኬንያ ወጣቶች ተራ ቀን መሆኑ ከቀረ ሁለት ዓመት ተቆጠረ። የዛሬ ሁለት ዓመት ጀነሬሽን ዜድ የተሰኘው ንቅናቄ የኬንያን የፖለቲካ ገጽታ ቀይሯል። በሥራ አጥነት መባባስ፣ በኑሮ ውድነትና በመንግሥታቸው አስተዳደር ብልሽት የበሸቁት ኬንያውያን የሀገሪቱን ፓርላማ ከበው በከፊል በእሳት እስከመለኮስ ደርሰዋል። በወቅቱ የሀገሪቱ መንግሥት ያረቀቀውን የፋይናንስ ማሻሻያ የተባለ ሕግ በመቃወም አደባባይ ከወጡት 60 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በርካቶች ተጎድተዋል፤ ታስረዋል። ከሁለት ዓመት በኋላም፣ ከተቃውሞዎቹ ጋር የተያያዙ በርካታ ሰዎች አሁንም ያሉበት እንዳልታወቀ የሰብአዊ መብት ቡድኖች ይናገራሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት የንቅናቄው ተሳታፊዎች በወሰዱት እርምጃ የኬንያን የፖለቲካ ገጽታ ቀይረዋል። የጄን ዚ ንቅናቄ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ተግባራዊ ሊያደርጉ ያቀዱትን የፋይናንስ ሕግ በአደባባይ ተቃውሞ ከማስቆም ባሻገር ጥያቄው ተጠያቂነትን ጨምሮ፤ የዜጎችን ተስፋ አጨልሟል ያሉት አስተዳደራቸው ቃል የገባውን ተግባራዊ ባለማድረጉ ማሻሻያ እንዲያደርግ ግፊት እያደረገ ነው። በርካታ ወጣቶች ከሩቶ ሥልጣን መያዝ በኋላ የታየው ለውጥ በጣም ኢምንት ነው ባይ ናቸው። የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ንረት እና የመንግሥት አስተዳደር ሥልጣን ከተወሰነ ትውልድ ይዞታ አለመውጣት ስጋት አሳድሮባቸዋል። በዚህም ምክንያት ይህን ዕለት ጨካኝ አገዛዝን በመቃወም ድምፃቸውን የሚያሰሙበት፤ የአልበገር ባይነት ተምሳሌት አድርገው ይመለከቱታል።
የበይነመረቡ ንቅናቄ
በበይነመረብ ተጀምሮ ወደ ሀገሪቱ ጎዳናዎች የፈሰሰው የጄን ዚ ንቅናቄ ሁለተኛ ዓመት ከቀናት በፊት በታሰበበት ዕለት የኬንያ መንግሥት እጅግ በርካታ የፀጥታ ኃይሎችን አሰማርቶ ታይቷል። የናይሮቢ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተው በአድማ በታኝ ፖሊስ ቢሞሉም ሕይወታቸው የተቀጠፈ፤ አካላቸው የተጎዳና እስካሁን ደብዛቸው የጠፋውን ወገኖቻቸውን እንዳልዘነጓቸው ለመግለጽ የጀገኑ በርካቶች ለሰልፍ ወጥተዋል። ለሞቱት መታሰቢያ አበባ ካስቀመጡት ወጣቶች አንዷብሪያን ኦቲየኖ ይህ ቀን ለእነሱ ጓዶቻቸውን የሚያከብሩበት ቀን መሆኑን ትናገራለች።
«የሞቱትን ጓዶቻችንን ሕይወት በማክበር እቅፍ አበባዎችን ይዘን ነው የመጣ ነው። መንግሥታችሁ ደኅንነታችን ሊያስከብር መዘጋጀት ይኖርበታል።» ስትልም ለፍልሚያ የተዘጋጁ የሚመስሉትን አድማ በታኞች ጎንተል አድርጋለች።
የዛሬ ሁለት ዓመት ለቀናት የዘለቀውን የተጠናከረ ሕዝባዊ አመጽና ተቃውሞ ተከትሎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደው የኃይል እርምጃ ለደረሰው ጉዳት ዛሬም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጥሪ እየቀረበ ነው። ቦኒፌስ ሙዋንጊ የኬንያ የመብት ተሟጋች ናቸው።
«ኬንያ ውስጥ ተቃውሞ ማሰማት ሕጋዊ ነው። በሕገ መንግሥቱም የተደነገገ መብት ነው፤ ሆኖም ኬንያውያን ይህን ማድረግ አይፈቀድላቸውም። ለሰላማዊ ተቃውሞዎች የፖሊስ ምላሽ ጥይት መሆኑ እየታየ ነው።»
ለተጎዱ ካሣ ወይስ ፍትህ
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋማት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስዎች ኬንያ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመንግሥትን ብልሹ አሠራር የሚተቹ ወገኖችን መሰወር እና ማገት ተጠናክሮ መቀጠሉን ይፋ አድርገዋል። መንግሥት ሀላፊነቱን ችላ በማለት እየተወቀሰ ነው። የጄን ዚ ንቅናቄ ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት ዋዜማ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በወቅቱ የመንግሥት ኃይሎች የፈጸሙትን ድርጊትና ያደረሱትን ጉዳት አምነው፤ ለተጎጂዎች ካሳ የሚውል የ 15 ሚሊየን ዶላር መንግሥታቸው መመደቡን ይፋ አድርገዋል። ከጎርጎሪዮሳዊው 2017 እስከ 2025 በዚህ መንገድ ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ሁለት ሺህ ሰለባዎች እንዳሉ ነው የተገለጸው።
ምንም እንኳን መንግሥት የገንዘብ ካሳ እንደሚሰጥ ቢጠቁምም ኬንያውያን ግን ፍትህ እየጠየቁ ነው። ፍትህ ሲሉ ምን ማለታቸው ይሆን? እነሱ የሚሉት ገንዘብ ያለተጠያቂነት እና ፍትህ ትርጉም የለውም ነው። የቀይ ሰደሪያ እንቅስቃሴ አራማብ ቢያትሪስ ዋይቴራ ገንዘብ መስጠቱ ብቻ በቂ አይደለም ከሚሉት ወገን ናቸው።
«ገንዘብ መስጠቱ ብቻ በቂ አይደለም ምክንያቱም የእነዚያን ሰዎች ነፍስ የሚመልስ ምንም ዓይነት ገንዘብ፤ ታውቂያለሽ? ምንም ዓይነት ገንዘብ የለም። እስከ 20 እና 19 ዓመታቸው ያደጉ ልጆች ነበሩ። ከወንድሙ ጋር የሄደ አንድ ወጣት ነበር፤ ወንድሙ ግን ወደ ቤቱ አልተመለሰም። ወንድሙ ኪጂያዶ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ነበር። ልጅ ላሳደገ ወላጅ እንዴት ነው የምትከፍይው? ያን ማድረግ በፍጹም አይቻልም።»
ከዚህ ጎን ለጎን የዛሬ ሁለት ዓመት የተቃውሞ ሰልፉን ለመደፍለቅ የተፈጸመውን የኃይል እርምጃ እንዲጣራና ተጠያቂነት እንዲኖር ግፊቱ ቀጥሏል። የመብት ተሟጋቾች እና የተጎጂዎች ቤተሰቦች ምርመራ እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው። የፍትህ አካላትና ፍርድ ቤቶች ለዚህ አቤቱታ በቂ መልስ እንዳይሰጡ ተተብትበዋል ሲሉም ይወቅሳሉ።
ድምፅ አልባው አብዮት
በዚህ የተናደዱት የኬንያ ወጣቶች ድምጻቸውን ሰጥተው ከመረጡት መንግሥት የጠበቁትን እንዳላገኙ ነው የሚናገሩት። በዚህም ምክንያት እስኪለወጥ ድረስ መቃወማቸውን እንደሚቀጥሉና መንግሥትንም በድምጻቸውም ለመቅጣት መዘጋጀታቸው በአደባባይ ይገልጻሉ።
«በጥይት የሚመጣ አብዮት አለ፤ ድምጽ አልባ አብዮትም አለ። ድምፃችንን እንሰጣለን። በ2024 እና በ2025 በ2027 ምርጫ ድምጻቸውን ሊሰጡ የሚችሉ እጅግ በርካታ ወጣት ኬንያውያንን አጥተናል፤ ስለዚህ አሁን ተጨማሪ ሕይወት ማጣት አንፈልግም። ወደ ምርጫ እንሄድና በምንሰጠው ድምፅ እነዚያ በተቃውሞ አደባባይ እንድንወጣና ጓዶቻችን እንዲሞቱ ምክንያት የሆኑትን መጥፎ መሪዎች በካርዳችን ምን ማድረግ እንደምንችል እናሳያለን።»
«ይህ ወጣቶች ለዴሞክራሲ የሚሰጡት የመጨረሻ እድል ነው፤ ዴሞክራሲ በሚቀጥለው ዓመት የማይሠራ ከሆነ፤ ከዚያ በኋላ በድጋሚ በዴሞክራሲ በፍጹም አናምንም። ስለዚህ ምንም የመጨረሻው ቀን ቢሆንም እንኳ ድምፅ ለመስጠት እንሄዳለን፤ ለዚህ ነው ይህ ካርድ የሚጠቅመው።»
«በርካታ ወጣቶች የመራጭ ካርድ የላቸውም፤ ለ2027 ውሳኔ መስጠት እንዲያስችላቸው ብዙ ወጣቶች የምርጫ ካርድ እንዲኖራቸው እንቀሰቅሳለን። ወጣቶች በዚህ ዓመት ንቁ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። እኛን ላልተገባ ነገር ከሚጠቀሙብን ይልቅ ይህን አመራር እኛ መያዝ ይኖርብናል።»
ኬንያውያን ወጣቶች አመጽ ከቀላቀለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ድምፅ አልባ ያሉትን ንቅናቄ ማጠናከራቸው ነው የሚነገረው። በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2027 የኬንያ ምርጫ መብታችንን አልጠበቀም፤ ለጥያቄያችን በቂ ምላሽ አልሰጠም ያሉትን አስተዳደር በድምጻቸው ለመቅጣት ዝተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ