1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያው ምርጫ ተስፋና ስጋት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 4 2014

የአየር መዛባት ያስከተለው ድርቅና በተደጋጋሚ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዓመታዊ የሰብል ምርቷ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የረድኤት ድርጅቶች ተመጽዋች እንድትሆን ያስገደዳት ኬንያ፤ በዚህ ሁሉ ፈታኝ ችግር ታጅባ በትላንትናው ዕለት "ከሞላ ጎደል ነጻና ሰላማዊ ነው" የተባለለትን አገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫ አካሂዳለች::

https://p.dw.com/p/4FNGN
Kenia Wahlen Raila Odinga William Ruto
ምስል AFP

የኬንያው ምርጫ ተስፋና ስጋት

ከ 4 ሚልዮን የሚልቁ ዜጎቿ ለረሃብ አደጋና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡባት፣ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የተንሰራፋባት፣ ከጎረቤት ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አል-ሸባብ በርካታ ጥቃቶችን በመፈጸም በቱሪዝም ገቢዋና በምጣኔ ኃብቷ ላይ ማነቆ እንዲሁም የጸጥታና ደህንነት ስጋጥ የጋረጠባት በተጨማሪም የአየር መዛባት ያስከተለው ድርቅና በተደጋጋሚ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዓመታዊ የሰብል ምርቷ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የረድኤት ድርጅቶች ተመጽዋች እንድትሆን ያስገደዳት ኬንያ፤ በዚህ ሁሉ ፈታኝ ችግር ታጅባ በትላንትናው ዕለት "ከሞላ ጎደል ነጻና ሰላማዊ ነው" የተባለለትን አገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫ አካሂዳለች:: ኬንያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1991 ዓ.ም ካስተዋወቀች በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚሁ ፕሬዝዳንታዊ እና የከተማ አስተዳደር፣የሕዝብ እንደራሴዎች፣የሕግ አውጪዎችና የሴቶች ተወካዮች ምርጫ 22 ሚልዮን ያህል የሃገሪቱ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚሁ መራጮች በትላንትናው ዕለት የድምጽ መስጫው የጊዜ ሰሌዳ ሊጠናቀቅ እስከተቃረበበት ሰዓት ድረስ ከ 56 በመቶ የሚልቁ ድምጽ መስጠታቸው ታውቋል:: የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንዳመለከተው ከኬንያ ውጪ በሌሎች 12 የአፍሪቃና የምዕራባውያን ሃገራት ነዋሪ የሆኑ ዲያስፖራ ኬንያውያንም በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ተሳታፊ ሆነዋል:: ዓለም በትኩረት በተከታተለው የዘንድሮው ምርጫ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 1960ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ኑሮዋቸውን በኬንያ የቀለሱትና የሩዋንዳ የዘር ማንነት አላቸው የሚባሉት በሺህ የሚቆጠሩ አገር አልባዎቹ የሳሆና ማኅበረሰብ አባላት ሙሉ የኬንያ ዜግነት ከተሰጣቸው በኋላ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ እንዲሰጡ በመደረጉ ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልጹ ታይተዋል:: በብሪታንያ የጉዞ ሰነድ በክርስቲያን ሚስዮናዊነት ከዚምባብዌ ኬንያ የገቡት ሳሆናዎች አምና በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ሙሉ ዜግነት እንዲያገኙ መወሰኑ በዓለማቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በኩል "የሺህዎችን ሕይወት የቀየረ" የሚል ምስጋና ተችሮታል::

Kenia Kibera Slum Nairobi Wahlen
ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

በኬንያው የዘንድሮ ምርጫ ለመራጩ ሕዝብ ቁጥር ማነስ በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አስተዳደር፣የምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆልና የኑሮ ውድነት በማኅበረሰቡ ዘንድ የፈጠረው ተስፋ ማጣት ነው ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳይ ተንታኝ ባለሙያዎች ይገልጻሉ:: ኬንያና ሶማሊያ በሚዋሰኑባቸው በተለይም በሰሜን ምሥራቅ የድንበር አካባቢዎች የአል-ሸባብን ዛቻና ወከባ ተከትሎ የመራጩ ሕዝብ ያደረበት ስጋትም ቁጥሩ በእጅጉ ለማሽቆልቆሉ ሌላው ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል:: አራት ዕጩዎች ለርዕሰ ብሔርነት በተፎካከሩበት የዘንድሮው ምርጫ በተለይም በምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊልያም ሩቶና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ መካከል ጠንካራ ፉክክር የተደረገ ሲሆን ምርጫውን ለማካሄድ አገሪቱ 400 ሚልዮን ያህል ዶላር ከፍተኛ በጀት መመደቧም ተነግሯል::

በኬንያ ዘንድሮ ነጻ፣ገለልተኛ፣ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ቆርጬ ተነስቻለሁ ሲል ያስታወቀው የአገሪቱ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ጽ/ቤት በምርጫው ዋዜማ ስድስት ከፍተኛ ባለስልጣናቱን "ምርጫውን ለማዛባት በማሴር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ" ሲል በፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን የኮምሽኑ ሊቀመንበር ዋፉላ ቼቡካቲ ይፋ አድርገዋል:: የኒሺዋ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኮማንደር ፓውል ሪዮባ እንዳሉት የካንዮዶቶ ምርጫ ጣቢያ ዋና አስተባባሪና ሁለት ምክትል ሃላፊዎች እንዲሁም የአጎራባች ቀበሌ ክዋብዋይ ምርጫ ጣቢያ ጸሃፊ የምርጫውን ውጤት በማዛባት የተወሰኑ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በማጭበርበር ምርጫውን እንዲያሸንፉ አሻጥር ለመፈጸም በድብቅ ስብሰባ አካሂደዋል በሚል ጥቆማ ነው ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት:: ከዚህ ሌላ ከምርጫ ቁሳቁስ ጋር በተያያዘ ግልጽ ችግር ተስተውለውባቸዋል የተባሉ አራት የምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ተደርጓል:: በተለይም በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ እና ካካሜጋ አውራጃዎች የሚካሄደው የከተሞች አስተዳደር ም/ቤት ምርጫ እንዲሁም በካቺሊባና በደቡባዊ ፖኮት የምርጫ ክልሎች የሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮች የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተሳሳቱ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ሳቢያ ኮሚሽኑ ተጨማሪ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ የምርጫው ሂደት ለጊዜው መታገዱና መራዘሙ ተገልጿል::

Kenia Wahlen 2022
ምስል Luis Tato/AFP

በትላንትናው ዕለት በኬንያው ምርጫ ካጋጠሙ የምርጫ አፈጻጸም ግድፈቶች መካከል ድምጽ ለመስጠት ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ወደ ሜርሲ ኔሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምርጫ ጣቢያ ያቀኑ እና በድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች እና በድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት እንዲሁም መጥፋት ሳቢያ የምርጫው ሂደት ተስተጓጉሎ የሕዝብ ተወካዮቻቸውን መምረጥ ባለመቻላቸው የተቆጡ የሮንጋኢ ከተማ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ በማቅናትና ጎማዎችን ጭምር በማቃጠልተቃውሞዋቸው ለማሰማት የሞከሩ ሲሆን ፖሊስ በኃይል ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ አድርጓል:: በሌላ በኩል ሁለት የኬንያ ፖሊስ ባልደረቦችና አንድ ተጠርጣሪ ግብረ-አበራቸው በትላንትናው ዕለት በኪልጎሪስ አውራጃ የምርጫ ቁሳቁሶችን በቶዮታ መኪና ጭነው ሲጓዙ ነዋሪው ሕዝብ ባደረሰው የጥርጣሬ ጥቆማ መሰረት በመንግሥት የጸጥታ ኃይላት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኬንያው ዜና አገልግሎት ዘግቧል:: በሞምባሳም እንዲሁ የከተማዋ አስተዳዳሪ አሊ ጆሆና በ 2020 ዓ.ም ሥልጣንን አለ አግባብ በመጠቀም ወንጀል ተከሰው ከኃላፊነታቸው የተነሱት የቀድሞ የናይሮቢ ከተማ ም/አስተዳዳሪ ሚኬ ሶንኮ ትላንት በምርጫው ዕለት በሞምባሳው የማሪ ክሊፍ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የምርጫ ጣቢያ ድምጽ በሚሰጡበት ወቅት ተገናኝተው ደጋፊዎቻቸው በቀሰቀሱት ጸብ ለቦክስ በመጋበዛቸው በስፍራው የነበረው ፖሊስ ጥይት ተኩሶ ግጭቱን በማብረድ ሁከቱን መቆጣጠሩን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ከተጋሩ የቪድዮ ምስሎች ለማረጋገጥ ተችሏል:: በዘንድሮም ምርጫ ለሞምባሳ ምክርቤት አስተዳዳሪነት በዕጩነት እንዳይወዳደሩ በገለልተኛው የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የታገዱት ሶንኮ የምርጫውን ሂደት በማወክ ወንጀል እንደሚጠየቁ እየተነገረ ነው::

Kenia Wahlen 2022
ምስል Patrick Meinhardt/AFP

አጠቃላይ የኬንያውን የድምጽ አሰጣጥ ሂደትና የሚጨረሻውን ውጤት በተመለከተ አንጋፋ ፖለቲከኛና ለአምስተኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት የ 77 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ራይላ ኦዲንጋ ለደጋፊዎቻቸው ወጤቱ ምንም ይሁን ምን በሰላምና በጸጋ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል::

"በ 2002 ዓ.ም ምርጫ አሸናፊውን ሞይን እጁን በመጨበጥ መልካም ምኞቴን ገልጬለታለሁ፤ በ 2008 ዓ.ም ምርጫም የሙአይ ኪባኪን እጅ በመጨበጥ ለምርጫ ተቀናቃኜ መልካም የስራ ዘመን ተመኝቻለሁ፤ በ 2018 ዓ.ም ምርጫም ለወንድሜ ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፌያለሁ:: በፖለቲካ ሰበብ ማንም ሕይወቱን እንዲያጣ አልፈልግም፤ በዚህም ምርጫ ባሸንፍም ብሸነፍም መርሄ የማይናወጥ በመሆኑ ለሰላምና ለኬንያውያን ስል እጆቼ አሁንም ተዘርግተው ይጠብቃሉ" ብለዋል:: ከኦዲንጋ ጋር አንገት ለአንገት የምርጫ ትንቅንቅ ውስጥ የገቡት የ 55 ዓመቱ ቱጃርና በአገሪቱ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉት የኬንያው ም/ፕሬዝዳንት ዶክተር ዊልያም ሩቶ ግን በአንጻሩ "የኬንያ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚሰራለትን ሰው ጠንቅቆ ያውቃል:: በዚህ ምርጫ እንደማሸንፍ ከፍተኛ እምነት አለኝ" ሲሉ በይፋ ተናግረዋል:: በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና በእጩ ተወዳዳሪዎች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበት የዘንድሮው የኬንያ ብሔራዊ ምርጫ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከታየው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ዘግይቶ መጀመር፤ መጠነኛ የምርጫ ቁሳቁሶች እጥረትና መጥፋት እንዲሁም የቴክኒክ አፈጻጸም ግድፈት ውጪ ነጻና ሰላማዊ እንደነበር ተነግሯል:: የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን የ /ኢጋድ/ የምርጫ ታዛቢ ልዑክን በመምራት እንዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በኬንያው ምርጫ በታዛቢነት መካፈላቸው ታውቋል:: የምርጫው ሂደት ተጠናቆ እስካሁን በተደረገው 95 በመቶ ያህል የድምጽ ቆጠራ ም/ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በ 55.96 % እየመሩ ሲሆን ራይላ ኦዲንጋ 48.5 % ሌሎች ዕጩዎች ደግሞ 0.7 % ድምጽ ማግኘታቸው እየተገጸ ነው::

Kenia Wahlen 2022
ምስል Boniface Muthoni/SOPA Images/ZUMAPRESS.com/picture alliance

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ