1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫ እና አልቃና ያለው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 30 2014

የኬንያ ህግ ሃገሪቱ ለምርጫ ከምታቀርባቸውም ሆነ ለመንግስታዊ ስልጣን ከምትሾማቸው ውስጥ አንድ ሶስተኛው ሴቶች መሆን እንዳለባቸው ደንግጓል። ነገር ግን የፊታችን ረቡዕ ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ/ም በሚደረገው የፕሬዚዳንታዊ እና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከቀረቡት 16 ሺ ዕጩዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከ 2 ሺ እንደማይበልጥ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4FCLJ
Kenia Wahlen 2022
ምስል John Ochieng/SOPA Images/ZUMAPRESS.com/picture alliance

ኬንያውያን ሴት ፖለቲከኞች ተስፋ የሚያደርጉበት መጻዒ ጊዜ ቶሎ ይደርስ ይሆን?

የኬንያ ህግ ሃገሪቱ ለምርጫ ከምታቀርባቸውም ሆነ ለመንግስታዊ ስልጣን ከምትሾማቸው ውስጥ አንድ ሶስተኛው ሴቶች መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። ነገር ግን የፊታችን ረቡዕ ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ/ም በሚደረገው የፕሬዚዳንታዊ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከቀረቡት 16,000 ዕጩዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከ 2 ሺ እንደማይበልጥ ተገልጿል። 
በኬንያ ለኢምቡ ግዛት ለፓርላማ አባልነት የምትወዳደረው ሱዛን ጊታሪ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ተጨማሪ ወጣት ሴቶች ዕጩ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል ትላለች። 
"ጅምር ላይ ነን፤  ነገርግን እስካሁን አልደረስንም። ስለዚህ ወጣት ሴቶች ዕጩ ሆነው ለምርጫ እንዲቀርቡ  አበረታታለሁ ምክንያቱም ስለምንችል! አዎ እንችላለን!"
በኬኒያ ለምርጫ የሚቀርቡ ዕጩዎችን ጾታን መሰረት አድርጎ የተደነገገውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በዘንድሮው ምርጫ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ሳይሆን አልቀረም። 
እንደ የዓለማቀፉ የፓርላማዎች ህብረት ከሆነ ከምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት በፖለቲካ ውስጥ ዝቅተና የሴቶች ተሳትፎ ያላት ሀገር ኬንያ ናት። በሀገሪቱ ፓርላማ ውስጥ በሴቶች የተያዘው ወንበር አሁን 23 ከመቶ ነው። እንደዚያውም ሆነ አብዛኞቹ ተመራጭ ሴቶች የዋናው ፓርላማ አባላት እንዳልሆኑ ሲገለጽ ኬኒያ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተግባራዊነቱ ገና ረዥም መንገድ እንደሚቀረው ማሳያ ሆኗል። 
የወንድ ፖለቲከኞች በሀገሪቱ ህገ መንግት መሰረት የተወዳዳሪም ሆነ የመንግስታዊ ተሿሚዎችን በኮታ ለማስፈጸም የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ጭምር ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው የሚነገረው ። ይህ ደግሞ  በሀገሪቱ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት አድካሚ ብቻ ሳይሆን ገና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ሆኗል። 
 ከአራት ዓመት በፊት በጎርጎርሳውያኑ 2018 በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከሶስት ሰዎች አንዷ ሴት መሆን በሚጠበቅበት የሀገሪቱ ፓርላማ ሳይሳካ ቀርቷል። አለመሳካቱ ብቻ አይደለም ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ በቀጣዩ ምርጫ ተጨማሪ ሴቶች ወደ ፓርላማ ብሎም ወደ መንግስታዊ የስልጣን እርከን እንዲመጡ የተደረገ ጥረት አለመኖሩ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ከወረቀት  እንዳይሻገር አስገድዶታል። 
በእርግጥ ነው ኬንያውያን ሴቶች ወረቀት ላይ እዩት ነገር ግን አትንኩት የተባሉ ያስመሰላቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ከወንዶቹ ጫና እና ፍላጎት ባሻገር ሴቶቹ ራሳቸው የሚገኙበት ተጨባች ሁኔታዎች የራሳቸውን አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል። 
እስቲ ነጣጥለን እንመልከት። 
ኤኮኖሚ !
ኬንያውያን ሴቶች ከወንዶች ፍላጎት እና ጫና ተላቀው ራሳቸውን ችለው በሀገሪቱ የማህበረ ኤኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የራሳቸውን ሚና እንዳይጫወቱ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የኤኮኖሚ ጥገኝነታቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ድሆች ናቸው። በዚህም ሴቶች ለትዳር ተጣማሪዎቻቸው ፍላጎት እና ትዕዛዝ የማደር ብርቱ ጫና እንዲፈጠርባቸው አስገድዷቸዋል። የሀገሪቱ መንግስታዊ የመረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከሆነ በመደበኛ የስራ መስኮች ተሰማርታ የምትገኘው ከሶስት ሴቶች አንዷ ብቻ ናት።  
በዚህም ምክንያት በተለመደው መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ በሚጠይቀው የምርጫ ዘመቻዎች ኬንያውያን ሴት ፖለቲከኞች አልቀመስ እያላቸው ሲውተረተሩ ይስተዋልሉ። እንደዚህም ሆኖ ግን ነገሩ  ጨርሶ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም ። በምርጫው የምትሳተፈው ሱዛን ጊታሪ እህት  ሜርሲ ዋምቡዪ እንደምትለው አንዳንድ ነገሮች እየተቀየሩ መምጣታቸውን ተስፋ ታደርጋለች። በምርጫው ላይ በምትሳተፈው እህቷ የፖለቲካ አቅም ተማምነው ድጋፋቸውን የሚቸሩ ሰዎች እየበዙ መምጣጣታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግራለች።  
„እሷን በሚረዱ እና ስለ እሷ አጭር ታሪክ ካላቸው እና ችሎታዋን ከሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥሩ ድጋፍ አግኝተናል“
ምናልባት በሀገሪቱ አሁን ያለውን ሁኔታ ሊያስቀር ይችል እንደሁ ተስፋ የተጣለበት በፕሬዘደንትነት የሚወዳደሩት የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ የቀድሞዋን የፍትህ ሚኒስቴር ማርታ ካሩዋን በምክትል ፕሬዚደንትነት አጭተው ለውድድሩ መቅረባቸው ምናልባት ከሴቶች አንጻር የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ይቀየር እንደሁ ተስፋ ተጥሎበታል። ራይላ ኦዲንጋ የፕሬዚደንትነቱን ምርጫ ካሸነፉ ማርታ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዚደንት ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ በኬኒያ የሴት ፖለቲከኞች የሚገባቸውን ስፍራ እንዲያገኙ ለሚታገሉት አንዳች የምስራች ይዞ መምጣቱ አይቀርም ። ምንም እንኳ ይህ ብቻውን የሀገሪቱን የሴት የፖለቲከኞች ተሳትፎ ማደግ ብቸኛ ማሳያ ባይሆንም። 
ዕጩ ምክትል ፕሬዚደንት ማርታ ካሩዋ ባለፈው የግንቦት ወር ዕጩነታቸው ይፋ ሲደረግ ባደረጉት ንግግር መጪው ጊዜ ለኬኒያ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል። 
« በእርግጥ ይህ የኬንያውያን ሴቶች ጊዜ እንደሆነ መናገር እችላለሁ»
ነገር ግን ሊዝ ንጁ  በፖለቲከኛዋ ንግግር አትስማማም ። ምክንያቱ ደግሞ ለፓርላማ አባልነት የምትወዳደረው የስነ ልቦና ባለሞያዋ በፓርቲዋ የመጀመሪያ ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት በወጣችበት አጋጣሚ ተቃዋሚዎች የአካል ጥቃት ደርሶባታል። በዚህም በወቅቱ ድምጽ ሳትሰጥ  ከአካባቢው ተገዳ መውጣቷን ትናገራለች ። አሳዛኙ ነገር ደግሞ ጥቃቱን ወዲያው ለፖሊስ ብታመለክትም መፍትሔ አለማግኘቷ ነው። ይህ በኬኒያ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የአደባባይ በደል ፤ ሴቶች ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ ንጁ አስረግጣ ትናገራለች።    
«ሰዎች  በፖለቲካው ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ እንፈልጋለን ፣ በርካታ ሴቶች እነዚህን የፖለቲካ መቀመጫዎች እንዲያገኙ እንፈልጋለን፤ ይላሉ ። ነገር ግን ግን ሴቷን ካዋረዷት በኋላ እንዴት ያገኟታል ?" 
 ስትል ጸጉሯ ተጎትቶ ፣ ልብሷ ተቀዶ እና ተዋርዳ ከፓርቲ ምርጫ የተገለለችው  የ39 ዓመቷ ንጁ ብሶቷን ገልጻለች።

Kenia Wahlen 2022
ምስል Boniface Muthoni/SOPA Images/ZUMAPRESS.com/picture alliance
Kenia Wahlen 2022
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP
BdTD | Kenia
ምስል Luis Tato/AFP
Kenia Wahlen Mary Mugure, Kandidatin
ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

በመጭው ረቡዕ ለሚደረገው ምርጫ ፤ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አካላዊ ጥቃት ከተፈፀመባቸው በርካታ  ሴት እጩዎች ንጁ አንዷ እንደሆነች  የኬንያ የሴቶች ፓርላማ ማህበር ኬዎፓ አስታውቋል። ይህ ለኬንያውያን ሴት ፖለቲከኞች ተስፋ ላደረጉበት መጻኢ ጊዜ መልካም ዋዜማ አይመስልም ።
በኬንያ ያለው የፆታ ጥቃት በፖለቲካ ብቻ የተገደበ አይደለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው  ከጠቅላላው የኬንያ ሴቶች  ግማሽ ያህሉ በአጋሮቻቸው ተደብድበዋል አልያም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም ሃያ ሶስት ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን ሳይደርስ ጋብቻ የፈጸሙ ናቸው። 
በተጨማሪም  በማያውቋቸው ሰዎች ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። አስገራሚው ነገር ደግሞ ከብዙዎች ጾታዊ ትንኮሳ እና በደል ጀርባ የፖለቲከኞች እጅ መኖሩ መጠርጠሩ ነው። 
ቀደም ሲል የስነ ጾታ ሰራተኛ የነበረችው እና ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ያለችው ሜሪ ሙጉሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የዕጩነት ድጋፍ በምታሰባስብበት ወቅት በስልክ እና በአችር የጽሁፍ መልዕክት ማስፈራሪዎች ሲደርሷት እንደነበር ገልጻለች።
ሌላው ኬንያውያን ሴቶችን በፖለቲካው የጎላ ተሳትፎ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኖባቸው የቆየው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚሰራጩ መልዕክቶ ተጠቃሾች ናቸው። 
የኬንያ የሴቶች ፓርላማ ማህበር ኬዎፓ ፕሮግራም አስተባባሪ ሜርሲ ምዋንጊ ሴት ህግ አውጭዎች ከድምጽ መስጫው ቀን በፊት የደረሰባቸውን ጾታዊ ትንኮሳ እና በደል በምስል ጭምር አሰደግፎ  ይፋ አድርጓል። 
"በዋነኛነት በፖለቲካ ስብሰባ ላይ በሚያደርጓቸው ጭፈራዎች ሴቶችን በመሳደብ ፣ ጡታቸውን ወይም የእግራቸውን ምስል በማጉላት ወይም ሰውነታቸውን የሚያሸማቅቁ እና በርካታ ሴትነትን ዝቅ የሚያደርጉ እንዲሁም ስሜትን የሚነኩ ድርጊቶችን ሲያደርጉ ይታያል።»
እንደዚያም ሆኖ ግን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኬንያውያን ወንዶች በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው በደል  አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል በማስጠንቀቅ ድምጽ የመሆን ዘመቻን እየተቀላቀሉ ነው።
"ኦንላይን ላይ ሴት ፖለቲከኞችን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ ምንም አይነት ጥረት ካልተደረገ ብዙ ሴቶች ከፖለቲካ ሲገለሉ እናያለን" ሲል ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚያበረታታው« አንቀፅ 19» የተባለው መርኃ ግብር ኃላፊ የሆኑት ሮበርት ዋንጃላ ያስጠነቅቃሉ።
"በመጨረሻም የሴቶችን  ድምጽ ካጠፋን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት ሀገር መሆን እንዴትስ ይቻለናል?" በማለት አንኳር ጥያቄ በማንሳት መጻዒ ጊዜ ሴቶችን ያማከለ እንዲሆን ያሳስባሉ  ። ምርጫው ግን ደርሷል፤ በጣት የሚቆጠሩ ቀናትም ቀርተውታል። ከኬንያ ምድር ቸር ያሰማን።  

Kenia Wahlen 2022
ምስል Baz Ratner/REUTERS


ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ