1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 28 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ የካቲት 28 2014

ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ባየርን ሙይንሽን፣ ኢንተር ሚላን፣ ሊዛቦን፣ ፓሪ ሳንጃርሞ፣ ሪያል ማድሪድ እና ዛልስቡርግ ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተፋጠዋል። የአውሮጳ ኃያሉኑ የመልስ ግጥሚያዎቻቸውን ነገ እና ረቡዕ ማታ ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደርቢ ማንቸስተር ዩናይትድ በማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/488bm
Champions League - Paris St Germain v Real Madrid
ምስል Alain Jocard/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ባየርን ሙይንሽን፣ ኢንተር ሚላን፣ ሊዛቦን፣ ፓሪ ሳንጃርሞ፣ ሪያል ማድሪድ እና ዛልስቡርግ ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተፋጠዋል። የአውሮጳ ኃያሉኑ የመልስ ግጥሚያዎቻቸውን ነገ እና ረቡዕ ማታ ይከናወናሉ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደርቢ ማንቸስተር ዩናይትድ በማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። አርሰናል እና ሊቨርፑል ድል ቀንቷቸዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ሦስተኛ ደረጃ ከሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰን ጋር ቅዳሜ ዕለት ተጋጥሞ ነጥብ ጥሏል።  በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ኤልሼን ድል ሲነሳ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ሪያል ቤቲስን አሸንፏል። በጣሊያን ሴሪ ኣ ደግሞ ናፖሊ በኤሲ ሚላን ሽንፈት ሲገጥመው ጁቬንቱስ ትናንት ድል ቀንቶታል። 

Spanien, Madrid | Illumniation | Solidarität mit Ukraine
ምስል Javier Barbancho/REUTERS

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የፊታችን እሁድ ከጋና አቻው ጋር የመጨረሻ ዙር ግጥሚያውን ያከናውናል። የታንዛኒያ ቡድንን 2 ለ0 በደርሶ መልስ 2 ለ1 በማሸነፍ ወደ አምስተኛው እና የመጨረሻው ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ድምር ውጤት የበላይ መሆን ይጠበቅበታል። ጋና ወደ መጨረሻው ዙር ያለፈው ተጋጣሚው ኡጋንዳን በደርሶ መልስ 7 ለ1 ረትቶ ነው። የአምስተኛው ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያ የፊታችን እሁድ ተከናውኖ የመልሱ ጨዋታ በሳምንቱ ዐርብ ይከናወናል። ኮስታሪካ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አፍሪቃን ወክለው የሚሰለፉ ሃገራት ሁለት ናቸው። ከወዲሁ ለብሔራዊ ቡድናችን ድል እንመኛለን።

በሌላ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ አቻው በሁለት ጎል ልዩነት ሲመራ ቆይቶ በአስደናቂ ሁኔታ በማንሰራራት 2-2 አቻ መለያየቱም ባሳለፍነው ሳምንት ተዘግቧል።  የብሔራዊ ቡድኑ ልዑካን ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ የተመለሰ ሲሆን፤ የቡድኑ የመልስ ጨዋታውን ከ15 ቀናት በኋላ መጋቢት 11 ቀን 2014 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከዩጋንዳ ጋር ያከናውናል። የታዳጊ ቡድኑ ከዩጋንዳ ጋር የማጣሪያ ውድድሩን የጀመረው በህንድ የ2022 የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ተሰላፊ ለመሆን ነው።   

ሻምፒዮንስ ሊግ

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። በነገው ዕለት የእንግሊዙ ሊቨርፑል ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ጋር የመልስ ጨዋታውን በሜዳው አንፊልድ ያከናውናል። ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያው በሮቤርቶ ፊርሚኖ እና ሞሐመድ ሳላኅ ግቦች ኢንተር ሚላንን 2 ለ0 ነበር ያሸነፈው። በተመሳሳይ ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን እና ኦስትሪያው ዛልስቡርግ ይጋጠማሉ።

UEFA Champions League | Atletico Madrid v Manchester United | Tor (1:0)
ምስል Juan Medina/REUTERS

ረቡዕ በሚኖሩ ሁለት ጨዋታዎች የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ከፖርቹጋሉ ሊዛቦን እንዲሁም የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ ጋር ይፋለማሉ። ሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ምሽት አምስት ሰአት ላይ ነው የሚከናወኑት። ቀደም ሲል በነበሩ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ሊዛቦንን 5 ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አንኮታኩቷል። ፓሪ ሳንጃርሞ በበኩሉ መደበኛው 90 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ላይ እምባፔ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በሜዳው ሪያል ማድሪድን 1 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ማንቸስተር ዩናይትድን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ሲያንኮታኩት የ37 ዓመቱ አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አለመኖር አነጋግሯል።  ፖርቹጋላዊው አጥቂ ቡድኑ በከተማው ተቀናቃኝ ቡድን ብርቱ ሽንፈት በገጠመበት ወቅት ለቡድኑ ጉዳት እንደደረሰበት አመልክቶ በሀገሩ ግን ሲዝናና እንደነበር በተለይ «ዘ ሰን» የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የ63 ዓመቱ አሰልጣኝ ራልፍ ራኚክ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚኖረው ግጥሚያ ቀዳሚ ተሳላፊ እንደማይሆን ከነገሩት በኋላ ነበር ወደ ሀገሩ መብረሩ የተዘገበው።

ማንቸስተር ሲቲ የበላይነት ባሳየበት የትናንቱ ግጥሚያ የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካዮች እጅግ ደካማ ሆነው ታይተዋል። ለማንቸስተር ሲቲ ኬቪን ደ ብሩይነ በ5ኛው እና 28ኛው ደቂቃዎች ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።  ሪያድ ማኅሬዝ በበኩሉ በ68ኛው እና በ91ኛው ደቂቃዎች ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። ለማንቸስተር ዩናይትድ ብቸኛዋን ግብ 22ኛው ደቂቃ ላይ ጄደን ሳንቾ አስቆጥሯል።

Portugal Porto | Champions League | Mohamed Salah
ምስል Luis Vieira/AP Photo/picture alliance

ትናንት አርሰናል ዋትፎርድን 3 ለ2 ማሸነፍ ችሏል። አርሰናል ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ48 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከስሩ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድንም በአንድ ነጥብ ይበልጠዋል።  ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ መሪው ማንቸስተር ሲቲ እስካሁን 28 ጨዋታዎችን አከናውኗል። ማንቸስተር ሲቲ 69 ነጥብ ሲኖረው፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል በ63 ነጥብ ይከተላል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ከአርሰናል በአምስት ነጥብ ልዩነት ይበልጣል፤ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል። በርንሌይ፣ ዋትፎርድ እና ኖርዊች ከ18ኛ እስከ 20 ደረጃ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር አንድ እኩል ቢለያይም በ59 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው።  ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 50 ነጥብ አለው። ከባየር ሙይንሽን ጋር ነጥብ የተጋራው ባየር ሌቨርኩሰን 45 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ትናንት በተከናወነ ጨዋታ ሆፈንሀይም ኮይልን ከተማን 1 ለ0 አሸንፏል። በቅዳሜ ግጥሚያዎች፦ ሽቱትጋርት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ2 አሸንፏል። ላይፕትሲሽ ከፍራይቡርግ ጋር አንድ እኩል ሲለያይ፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ1 ድል አድርጓል።  በቦሁም የ2 ለ1 ሽንፈት የገጠመው ግሮይተር ፍዩርት 14 ነጥብ ብቻ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ላይ ይገኛል። 23 እና 22 ነጥብ ብቻ ያላቸው ሔርታ ቤርሊን እና ሽቱትጋርትም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

RB Leipzig - SC Freiburg
ምስል Jan Woitas/dpa/picture alliance

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ መሪው ሪያል ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት ሪያል ሶሴዳድን 4 ለ1 ኩም አድርጓል፤ ነጥቡንም 63 አድርሷል። ተከታዩ ሴቪያ ዐርብ ዕለት ከአላቬስ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየቱ በ55 ነጥቡ ተወስኗል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባርሴሎና በ48 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት በ88ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ኤልሼን ገጥሞ 2 ለ1 ድል አድርጓል። በ48 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አትሌቲኮ ማድሪድ ትናንት ቤቲስን 3 ለ1 አሸንፏል። ዛሬ ማታ አትሌቲኮ ቢልባዊ ሌቫንቴን ያስተናግዳል።

ሴሪኣ

በጣሊያን ሴሪኣ ትናንት ናፖሊን 1 ለ0 ያሸነፈው ኤሲ ሚላን በ60 ነጥቡ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ናፖሊ በ57 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቀርቶት 58 ነጥብ የሰበሰበው ኢንተር ሚላን በበኩሉ ዐርብ ዕለት ተጋጣሚው ሳሌርኒታናን ድባቅ የመታው 5 ለ0 ነበር። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጁቬንቱስ ስፔትሲያን ትናንት 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል፤ በዚህም ነጥቡን 53 አድርሷል።

Italienische Fussball-Liga | Juventus Fc - ACF Fiorentina
ምስል Fabio Ferrari/LaPresse/AP/picture alliance

አትሌቲክስ

በቅርቡ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ለሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪቃ ታዳጊና ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች የሚመረጡበት ውድድር ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሯል። በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ አረንጓዴው ስቴድዮም ውስጥ ዛሬ በተጀመረው ውድድር ብርታታቸውን የሚያሳዩ ጠንካራ አትሌቶች ለአፍሪቃ ውድድር ይመረጣሉ። 10ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 3ኛው ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ከቀነ 7:00 ላይ በኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የመክፈቻ ንግግር ነበር በይፋ የተጀመረው። በመክፈቻ ውድድሩ የሴቶች ጦር ውርወራ ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ፣ የወንዶች ከፍታ ዝላይ ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ፣ እንዲሁም የሴቶች ከ18 ዓመት በታች 800 ሜትር ማጣሪያ ተከናውኗል።

Eröffnungsfeier der Olympischen Spiele in Tokio | Vorbereitungen
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጠንካራ ፉክክር በወንድም በሴትም ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ በወንዶች ፉክክር የሦስተኛ ደረጃ ተገኝቷል። በሴቶች ፉክክር አትሌት አሸቴ በከሪ 2:17:58 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ሌላኛዋ አትሌት ጎይተቶም ገ/ሥላሴ 2:18:18 በመሮጥ የሦስተኛውን ደረጃ ተቆጣጥራለች።

በዚህ ውድድር ኬኒያዊቷ የርቀቱ የክብረ ወሰን ባለቤት ብሪጊድ ኮስጌይ 2:16.02 በመሮጥ አሸናፊ ኾናለች። በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክርም አሸናፊ የኾነው የወቅቱ የኦሎምፒክ ባለድሉ ኤሉድ ኬፕቾጌ ነው። ኤሉድ ርቀቱን 2:02:40 በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል። አትሌት ታምራት ቶላ 2:02:14 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግንኝቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሹራ ቂጣታ 2:06:12 በመሮጥ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

ፓራሊምፒክ

China | Paralympics Peking 2022 | Logo
ምስል Patrick Steiner/GEPA pictures/imago images

ቻይና ቤጂንግ ከተማ ውስጥ «የወፍ ጎጆ» በተሰኘው ስታዲየም የአካል ጉዳተኞች የሚሳተፉበት የክረምት ፓራሊምፒክ ውድድር ባለፈው ዐርብ ሲጀምር ለዩክሬን ሰላም ጥሪ ተላልፏል። ሩስያ ዩክሬን ውስጥ ጦርነት በመክፈቷ የሩስያ እና የተባባሪዋ ቤላሩስ አትሌቶች በፓራሊምፒክ ውድድሩ እንዳይሳተፉ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC)እገዳ ተጥሎባቸዋል። ከፓራሊምፒክ ቀደም ብሎ እዛው ቻይና ውስጥ በነበረው የኦሎምፒክ ውድድር ሕገወጥ ኃይል ሰጪ ንጥር በመጠቀም በሚል የሩስያ አትሌቶች ተሳታፊ የነበሩት በኦሎምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ ስር ነበር። በፓራሊምፒክ ውድድሩ ግን የሩስያ አትሌቶች በኦሎምፒክ ሰንደቅ ዓላማ ጥላ ስርም እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል። ውድድሩ የሚካኼድበት የቻይና መንግስት ለአምስት መቶ አትሌቶች አቀባበል ባደረገበት ወቅት ምዕራባውያን እንደፈለጉት ሳይሆን የሩስያ መንግስትን ከማውገዝ ተቆጥቧል። እስከ እሁድ በሚዘልቀው ውድድር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የ46 ሃገራት ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ