1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 20 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 20 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተደረጉ ውድድሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ አምስተኛ ዙራቸው ይቀጥላሉ ። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ዝነኛው ታይሰን ፉሪ ወንድም ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በተከናወነ ግጥሚያ አሸናፊ ሆኗል ።

https://p.dw.com/p/4O2Hd
Bundesliga | FC Bayern München v 1. FC Union Berlin
ምስል Matthias Koch/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተደረጉ ውድድሮች ድል ተቀዳጅተዋል ።  የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ አምስተኛ ዙራቸው ይቀጥላል ። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ዝነኛው ታይሰን ፉሪ ወንድም ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በተከናወነ ግጥሚያ አሸናፊ ሆኗል ። 

አትሌቲክስ

በጃፓን የኦሳካ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴትም በወንድም በአንደኛነት አሸንፈው ድል ተቀዳጅተዋል ። በወንዶች ፉክክር ከሦስት ዓመት በፊት በዓለም የግማሽ ማራቶን ምርጥ 15 ውስጥ የነበረው አትሌት ኃይለማርያም ኪሮስ ያሸነፈው 2:06:01 በመሮጥ ነው ። በበለጸጉ ሃገራት የማራቶን ፉክክር ባለድሉ የኡጋንዳው ሯጭ ቪክቶር ኪፕላጋት በኃይለማርያም በሁለት ሰከንድ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። የታንዛኒያው አልፎንሴ ፌሊክስ ቪክቶርን በ16 ሰከንዶች ተከትሎ በመግባት የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ።

ብርቱ ፉክክር በታየበት በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ሄለን በቀለ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው 2:22:16 በመሮጥ ነው ። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የቀድሞው የዓለም ሻምፒዮን ባለድል ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት በየኑ ደገፉ የሁለተኛ ደረጃን ስታገኝ የገባችበት ሰአትም 2:23:07 ነው ። በዚህ ውጤቷም የግል ምርጥ ሰአቷን ለማሻሻል ለጥቂት ሦስት ሰከንድ ብቻ ዘግይታለች ። ጃፓናዊቷ አትሌት ሞሞኮ ዋታናቤ ከአትሌት በየኑ በአንድ ሰከንድ ተበልጣ የግል ምርጥ ሰአቷ የሆነውን በማስመዝገብ የሦስተኛ ደረጃን አግኝታለች።

Symbolbild - Marathon
የማራቶን ሩጫ፦ ሯጮች ሲሮጡ ከጀርመባቸው ይታያሉምስል Colourbox

በዐሥረኛው የናፖሊ ግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክርም በ5000 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሁለት ጊዜያት ባለድሉ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር እድሪስ አሸናፊ ሆኗል። በሴቶች ዘርፍ የፖላንዷ ሯጭ አንጄሊካ ማች 1 ሰአት ከ12 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ በመሮጥ በአንደኛነት አጠናቃለች ።

ጣሊያን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የሩጫ ፉክክር ሙክታር ለድል የበቃው 1 ሰአት ከ27 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። የፈረንሳዩ ሯጭ መኅዲ ፍሬሬ ከ16 ሰከንዶች በኋላ ሙክታርን ተከትሎ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል ። ኬኒያዊው ዴኒስ ኪቤት ሦስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የገባበት ጊዜ 1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ተመዝግቧል ። በሴቶች ውድድር ዐሥረኛው ኪሎ ሜትር ላይ ቀዳሚ የነበረችው ቡልጋሪያዊቷ ሚሊትሳ ሚርቼቫ በአራት ሰከንዶች ተቀድማ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ከ5000 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ በነበሩበት በናፖሊው ውድድር ጣሊያናዊቷ ሬቤካ ሎኔዶ የሦስተኛ ደረጃን ይዛለች ።

15,000 አትሌቶች በተሳተፉበት በሜክሲኮ የጓዳላኻራ የግማሽ ማራቶን ሩጫ በወንድም በሴትም ድሉ የኢትዮጵያ ሆኗል ። በወንዶች ፉክክር አትሌት ያሲን ሐጂ ሃያቶ 1 ሰአት ከ1 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ በመሮጥ ድል ተቀዳጅቷል ። ኬንያውያኑ ርሆዛስ ሎኪታም እና ቤንሶን ኪፕሩቶ የ2ኛ እና 3ኛ ደረጃን አግኝተዋል ። በሴቶች ፉክክር ሕይወት ገብረኪዳን 1 ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ6 ሰከንድ በመሮጥ በአንደኛነት አሸንፋለች ። ኬኒያውያቱ ሲንቲያ ጄፕኮጂ እና ጃኔት ሩጉሩ የ2ኛ እና የ3ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል ።  ኢትዮጵያውያቱ መሠረት ገብሬ እና አፈራ ጎድፋይ ኬንያውያቱን ተከታትለው እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል ።

በሌሎች ፉክክሮች፦ ስፔን ውስጥ በተካሄደው የካስቴሎን ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ዳዲ ያሚ በስተመጨረሻ ተስፈንጥሮ በመውጣት በ2:11:15 አሸናፊ ሆኗል። ለሚ ዱሜቻ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በሴቶች ፉክክር ደግሞ አልጄሪያዊቷ ዓሚና ቤቲቼ አሸንፋለች። አትሌት ያለምጌጥ ያረጋል እሥራኤል ውስጥ በተከናወነው የቴል አቪቭ የ10 ሺህ ሜትር ፉክክር አሸናፊ ሆናለች።

Symbolbild - Marathon
የማራቶን ሩጫ፦ ሯጮች ሲሮጡ ከጀርመባቸው ይታያሉምስል Colourbox/Labrador

1ኛው የኢትዮጵያ ኘሮጄክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከየካቲት 15 -19 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ድረስ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል ። በአትሌቲክሱ ዘርፍ የወደፊት ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ አዳጊዎችን ለማፍራት መሰል ዝግጅቶች እና ውድድሮች እጅግ አስፈላጊ ናቸው ። በአብዛኛው የ16 ዓመት እና የ18 ዓመት አዳጊ አትሌቶች የሚሳተፉበት መሰል ውድድር ወደፊት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ። ከዚህ ቀደም በአሰላ አረንጓዴው ስታድየም እንደተፈጸመው የእድሜ ማጭበርበር እንዳይከሰትም ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ። ለ11ኛ ጊዜ በተከናወነውና እድሜያቸው «ከ20 ዓመት በታች» አትሌቶች በተሳተፉበት የአሰላው ውድድር ብርቱ የዕድሜ ማጭበርበር መፈጸሙ ቀደም ሲል ተዘግቧል ።

በሪዮ ዴጄኔሮ የ2016 ኦሎምፒክ የ1,500 ሜትር የፍጻሜ ተፎካካሪ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በሱ ሳዶ ባለቤቷን በመግደል ወንጀል ተጠርጥራ እድሜ ልክ ተፈርዶባታል ሲል ዎርልድ ትራክ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ ዛሬ ዘግቧል። በአትሌቲክስ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እና ክስተቶችን የሚዘግበው ዎርልድ ትራክ አትሌቷ ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ባለቤቷን ከሁለት ወንድሞቿ ጋር እና ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆና መገኘቷን የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች መዘገባቸውን በመግለጥ አትቷል። በወንጀሉ ተጠርጣሪ ከሆኑት የአትሌት በሱ ሳዶ ሁለት ወንድሞች አንደኛው እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች መሰወራቸውንም ይኸው ድረ ገጽ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሑፉ ዘግቧል። በመካከለኛ እና ረዥም ርቀት ተስፋ ተጥሎባት የነበረችው አትሌት በሱ ሳዶ ከወንድሞቿ ጋር ወንጀሉን ፈጽመዋል የተባለው ባለፈው ዓመት መሆኑም ተዘግቧል። በሱ ሳዶ በሀገር ውስጥ የ1,500 ሜትር ርቀት የሩጫ ፉክክር ለሦስት ጊዜያት አሸናፊ ነበረች። ባለፈው ዓመት ደግሞ ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቋም የሚታወስ ነው።

እግር ኳስ

ትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናዊው መልካሙ ፍራወንዶርፍ በሊቨርፑል ቡድን ከ21 ዓመት በታች ተስፋ የሚጣልበት ሆኗል ። ላለፉት 2 ዓመታት በሊቨርፑል ቡድን ውስጥ የሚገኘውን ይህን ወጣት ምናልባትም አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ዐይናቸውን ሳይጥሉበትም አልቀረም ። ደቡብ ኢትዮጵያ ከምባታ የተወለደው የ19 ዓመቱ አዳጊ አማካይ ተጨዋች ቀደም ሲል ጀርመን ውስጥ ለሼፍሌንትስ እና ሆፈንሀይም ቡድኖች ተጫውቷል ። ላለፉት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ደግሞ አንፊልድ ሜዳ ላይ ሄድ መለስ እያለ ነው ። መልካሙ አንድ ዓመት ተኩል ከሚበልጠው ታላቅ ወንድሙ መለሠ ጋር የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ወደ ጀርመን ባደን ቩይርተምበርግ የመጣው በጀርመናውያን ጥንዶች አሳዳጊነት ነው ። በሊቨርፑል ቆይታው እንዲሳካለት ከወዲሁ እንመኛለን ።

Riyad Mahrez, Fußballer
የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ሪያድ ማኅሬዝምስል David Blunsden/imago images

ፕሬሚየር ሊግ

የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ አምስተኛ ዙር የእግር ኳስ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ ወዲያ ይከናወናሉ ። በፕሬሚየር ሊጉ ቅዳሜ እለት በርመስን 4 ለ1 በመርታት ነጥቡን 55 ያደረሰው ማንቸስተር ሲቲ ከብሪስቶል ሲቲ ጋር ነገ ይጋጠማል ።  በፕሬሚየር ሊጉ አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ማንቸስተር ሲቲ በ2 ነጥብ ይበለጣል ። ኒውካስል ዩናይትድን ትናንት 2 ለ0 በማሸነፍ የሊጉን ዋንጫ የወሰደው ማንቸስተር ዩናይትድ ለኤፍ ኤ ካፕ ረቡዕ እለት ዌስትሀም ዩናይትድን ይገጥማል ። ቶትንሀም ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋርም በተመሳሳይ ቀን ያጋጠማል ። በነገው ዕለት ላይስተር ከብላክበርን፤ ስቶክ ሲቲ ከብራይተን፤ እንዲሁም ፉልሀም ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጋጠማሉ ። በርንሌይ ከፍሊት ውድ እንዲሁም ሳውዝሀምፕተን ከግሪምብሲ ታውን የሚጋጠሙት ረቡዕ እለት ነው ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት በነበረ ወሳኝ ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 አሸንፏል ። በደረጃ ሰንጠረዡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ 43 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ከዶርትሙንድ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ለነበረው ዑኒዮን ቤርሊን በባየርን ሙይንሽን የደረሰበት ሽንፈት መራር ነው ። ውጤቱ በ43 ነጥቡ ተወስኖ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀር አድርጎታል ። ባየርን ሙይንሽን በ46 ነጥቡ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ቢስተካከልም በግብ ክፍያ መሪነቱን ይዟል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ፎፈንሀይምን በጠበበ የ1 ለ0 ውጤትም ቢሆን ማሸነፉ በጅቶታል ።

ቡጢ

Symbolbild Boxhandschuhe
የቡጢ መቧቀሻ ጓንቶች ወለል ላይ ተቀምጠውምስል Sergiy Tryapitsyn/PantherMedia/IMAGO

ሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የቡጢ ፍልሚያ በቀድሞው የዓለም ቡጢ ምክር ቤት (WBC)ከባድ ሚዛን የቡጢ ባለድል ታይሰን ፉሪ ወንድም አሸናፊነት ተጠናቀቀ ። ጥሩ የቡጢ ችሎታ እንዳለው ያስመሰከረው ቶሚ ፉሪ በስምንተኛው ዙር ላይ ግን በተቀናቃኙ ባረፈበት ቡጢ ተዘርሮ ነበር ። ቀደም ሲል በዩትዩብ ታዋቂ የሆነው እና ወደ ቡጢ ስፖርት የገባው ጃክ ፖል የተሸነፈው ከሦስቱ ዳኞች ሁለቱ በተመሳሳይ ለቶሚ ፉሪ በሰጡት የ76 ለ73 ነጥብ ነበር ። አንደኛው ዳኛ ግን በተቃራኒው ለፉሪ የሰጡት 74 ለ75 የሚል ነጥብ ነበር ። በዚህ የዓለም ቡጢ ምክር ቤት (WBC) ከከባድ ሚዛን መለስ ያለ የቡጢ ውድድር የቀድሞ የከባድ ሚዛን ባለድል ማይክ ታይሰንን ጨምሮ በርካታ የቡጢ ስፖርት አፍቃሪዎች ታድመዋል ። በተለያዩ ምክንያቶች ውድድራቸው ቢራዘምም ሁለቱ ተፋላሚዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲዛዛቱ ነበር ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ