1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከንቲባው ሹመት፣ የሚሊኒየሙ ውዝግብና ሌሎች

ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2010

​​​​​​​ከሚሌኒየም አዳራሽ ውዝግብ፣ እስከ አዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት፣ ከኦነግ መግለጫ እስከ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስመራ ማረፍ መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/31mjk
Äthiopien Begeisterter Empfang für Präsident Isaias an Adis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

በሳምንቱ በርካታ ጉዳዮች መነጋገሪያ ኾነዋል

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ በሳምንቱ መነጋገሪያ የኾኑ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። እንደሚሊኒየሙ አዳራሽ ውዝግብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሹመት ጉዳይ ግን ገኖ የወጣ የለም። በርካቶችን በእንባ ያራጨው እና ልብ የሚነካው ትእይንት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አስመራ ሲያርፍ ታይቷል። በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የቀጠለው ግጭት እና የኦነግ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሲኖዶስ መካከል የታቀደው የሰላም ንግግርን በተመለከተም ቅኝት ይኖረናል።  

ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ውጪ ከንቲባ ከኦሕዴድ መሾሙ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ነው የቀሰቀሰው። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በህወሓት የተጠላው የአንድ አካባቢን ሰዎች በሥልጣን ዙሪያ ማሰባሰብ በኦሕዴድም እየተደገመ ነው ሊታረም ይገባል ብለዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከንቲባ ሥራ እንዲሠሩ የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ዑማ በንቲ በሹመቱ የተሰማቸውን ደስታ ማክሰኞ እለት ፌስቡክ ገጻቸው ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ገልጠዋል። «የአዲስ አበባ- ፊንፊኔ እና ሕዝቧን በዚህ ወሳኝ ወቅት በሰአቱ ለማገልገል መሾም በእውነቱ ክብር ነው» ሲሉ።   

ያሬድ አሥራት ትዊተር ገጹ ላይ፦ «አዲሱ የአዲስ አበባ ከንቲባ የከተማዋን ሕጋዊ ስም ለመጠቀም ችግር እንዳለባቸው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አዲስ አበባ የሚለውን ስም አዲስ አበባ - ፊንፊኔ ብለው በመቀየር [edit] ጀምረዋል!» ሲል ጽፏል። «ከተማዋን ፊንፊኔ ብሎ ለመጥራት የሚያስችል ሕጋዊ መሰረት የለም!» ሲልም አክሏል።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

ጋዜጠኛ መሐመድ አዴሞ በተመሳሳይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቀጣዩን አስተያየት ትዊተር ላይ አስፍሯል። «ይኽን ወጣት፣ ብቃት ያለው መሪ ጓደኛዬ ብዬ ስጠራው በኩራት ነው» ሲል ይንደረደራል። ለረዥም ጊዜ በውጭ ሀገር በቆየበት ወቅትም በመዲናዪቱ በርካታ ነገሮች መቀየራቸውን በዛው መጠን ብዙ ጉዳዮች ባሉበት መቀጠላቸውንም ጠቅሷል።  «ሥር የሰደደ እኩል አለመኾን፣ ጎስቋላ መንደሮች፣ ደካማ የንጽህና አጠባበቅ፣ የመጓጓዣ ችግር፣ ቤት አልባነት» ባሉበት እንደቀጠሉ ዘርዝሯል። ጽሑፉን ሲያጠቃልልም፦ «ፊንፊኔ ከትህትናው እና ርህራሄው እንደምታተርፍ እተማመናለሁ» ብሏል።

ለከንቲባው የተሰጠውን ሙጉሳ የተቃወመው ሰለሞን ደርዜ «በእውነት? ይህንስ ምን ትሉታላችሁ?» ሲል በታከለ ዑማ በንቲ ስም ፌስቡክ ላይ የወጣ ጽሑፍን አያይዟል። ጽሑፉ በላቲን ፊደላት አፋን ኦሮሞ ብሎ ይጀምርና በአማርኛ ይቀጥላል። «አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግ፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን  ሕገ-መንግሥታዊ ጥቅም (መብት) እንዲፈጸም፣ የልዩ ዞን እና የአዲስ አበባ ወሰን በዘለቄታው ለማካለል ኦህዴድ ተግቶ እንደሚሠራ ማዕከላዊ ኮሚቴው በልበ ሙሉነት ወስኗል»  ሲል ይጠናቀቃል ጥር ወር መገባደጃ ላይ የተጻፈው የፌስቡክ ጽሑፍ።

EPRDF Logo

«የአቶ አብይ መንግስት ወያኔን ደርቦ ሊያልፋት ነው መሰለኝ... ወያኔ በህወሀት ሰዎች ትሞላው የነበረውን የመንግስት አስተዳደር ቦታዎች እሱ በተራው በኦፒዲኦ ሰዎች ጢቅ አድርጎ እየሞላልኝ ነው አያረሩ መሳቅ» ያለው ደግሞ ሃይከል ነው ትዊተር ላይ።

ሮማን ጊ ተሾመ፦ «ደሞ የተመረጠበት መንገድ ዲሞክራሲያዊ አይደለም» ስትል አስተያየቷን ታንደረድራለች። «‘በህዝብ ከተመረጡት' መሀከል መሆን ነበረበት። በዚያ ላይ በሚቀጥለው ምርጫ ሊመረጥ እንደሚችል ማሰባቸው» ስትል ተቃውማለች።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድ ስለከንቲባው የሚከተለውን በእንግሊዝኛ ጽፏል፦ «ኦቦ ታከለ ዑማ በንቲ የፊንፊኔ አዲስ ከንቲባ ኾኗል። ከተማዪቱ እና በርካታ ሕዝቧ ከዚህ ወጣት ብርቱ ሰው ብዙ ይጠብቃል። ከተማዪቱን ወደ ለውጥ እንደሚመራት ተስፋ እናደርጋለን። መልካም ዕድል ወንድሜ» ሲል ይጠቃለላል የጃዋር ጽሑፍ።

የጃዋርን የትዊተር መልእክት ያያዘው ደብ ርሃን፦ «የጠቅላይ ሚንሥትርት ዐቢይ አህመድ ሹመት አሰጣጥ ምን ያኽል የተሰባጠረ ነው?» ሲል ጠይቋል። «ይኽ በጥልቀት ሊፈተሽ ይገባል» ሲልም አጽንዖት ሰጥቷል።

ማዕዲ በሚል የትዊተር ስም ተጠቃሚ ከፌስቡክ የተገኘ በሚል ያቀረበችው አጭር ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦«"ኦህዴድ ከቦ ሊያናግረን የፈለገ ይመስላል።» ጽሑፉ በሳቅ በሚያነባ ምልክት ታጅቧል። ከቦ ሊያናግር የሚለው ሐረግ ከዚህ ቀደም የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጨዋቾች ግንቦት ወር መግቢያ ላይ ዳኛ መደብደባቸው በተነገረበት ወቅት በቡድኑ ከተሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማል። በወቅቱ የወልዋሎ አዲግራት ቡድን ተጨዋቾቹ ዳኛውን አለመደብደባቸውን ይልቁንስ ከበው ለማናገር ጥረት ማድረጋቸውን ገልጦ ነበር። መግለጫው በስፋት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲብጠለጠል ከርሞ ነበር።

Logo Oromo Peoples' Democratic Organization

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኾነው ከረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ መጀመራቸው የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ተገልጧል። በዚሁ የምክትል ከንቲባ ሹመት ላይ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች ቀጣዮቹ ይገኙበታል።

«የአዲስ አበባ ከንቲባ መሆን ያለበት የከተማዉ ህዝብ በመረጠዉ እንጂ እራሱ መንግስት አይደለም መምረጥ ያለበት። ባጠቃለይ ህወሀት/ኢህአዲግ ሳይበርዝ ሳይከለስ በኦህዴድ/ኢህአዴግ ተቀይሯል።» አስኒ ጥላ በተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ የተሰጠ አስተያየት  ነው። አክሊሉ ሐብተወልድ ደግሞ፦ «የአዲስ አበባ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኦህዴድ ጊዜም በድጋሜ ተነፈገች። በኗሪዎቿ ምርጫ መተዳደር ሲገባት በችሮታ ለኦህዴድ ፅንፈኞች ተሰጠች» ብሏል። «ማንም ይሁን ማን ለከተማዋና ለነዋሪዎቿ ከሠራ መልካም ነው» ያለው ደግሞ ኢትዮጵያ ሐገሬ ነው።

«የህዝቡ አእምሮ (አስተሳሰብ) ላይ ከፍተኛ ሥራ መንግስት በተከታታይ መስራት አለበት ምክንያቱም የአዲሱን ከንቲባ ሹመት አስመልክቶ በህዝቡ መሃከል ያሉት ብዥታዎች መስተካከል አለባቸው። ከንቲባው ከየትም ይሁን አያገባንም ስራው ይታያል» የሚል አስተያየት የተሰጠው ደግሞ በፍጹም ፍቃዱ ነው።

«አዲስ ንጉስ እንጂ መቼ ለውጥ መጣ። በውድድር መሆን አለበት ልክ እንደ ዩኒቨርስቲ። ካልሆነ ከአዲስ አበባ ውስጥ መሆን ነው ያለበት» የገሬ ገብረሥላሴ አስተያየት ነው።

ሌላው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪ ኾነው ከቆዩ ጉዳዮች መካከል በሚሌኒየም አዳራሽ የተከሰተው ውዝግብ ይገኝበታል። በአማርኛ ቋንቋ አጠር ባለ መልኩ መልእክታቸውን ያሰሙት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚያን በተገኙበት መድረክ የድምጻዊ ቴዲ አፍሮ እና የሀጫሉ ሁንዴሳ ድርጊት ክርክር አጭሯል።

Äthiopien Begeisterter Empfang für Präsident Isaias an Adis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

ቀደም ብሎ መድረኩ ላይ ለመጫወት የወጣው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ የአባገዳ ባንዲራ ይዞ ሙዚቃውን በኦሮሚኛ አሰምቷል።

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ቴዲ አፍሮም እዛው ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ ፊዮሪና የተሰኘውን ሙዚቃ ከማሰማቱ በፊት የዳግማዊ ዓጼ ምኒልክን ስም እና ሌሎች ነገሥታትን ስም በማንሳት «የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይኼን ስላደረገ እናመሰግነዋለን» ብሏል።

የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንም የሀጫሉ ሁንዴሳም ድርጊት በተለያየ ወገን የጦፈ ክርክርና ውዝግብ አጭሯል። ይኽን የታዘበው ቢያንካ አርጋው፦ «ሀጫሉ አዲስ አበባ ላይ፣ ቴዲ አፍሮ አርሲ ላይፋሲል ደሞዝ መቀሌ ላይ ዘፍነው በሰላም የሚንቀሳቀሱባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች» ብሏል ትዊተር ላይ።

ሁለቱ አርቲስቶች ላይ እና ሰዉ ተቧድኖ መወራረፉ ያታከተው ፍቄ ጃ፦ «ኸረ በ...ዛ!» ሲል የትዊተር ጽሑፉን ያንደረድራል። «ሀጫሉን ጋብዞ ለምን ኦሮሞ ኦሮሞ አለ የሚልና ቴዎድሮስን ጋብዞ ለምን ሚኒሊክ አለ ማለት የእውቀት እጥረት ይመስለኛል። አሁን ጉዳዩ እሱ አይደለም!» ሲልም መልእክቱን ቋጭቷል።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የተጀመረዉን «የሰለም ዉይይት» ለማሳካት በሚል ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ኦነግ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አዉጆ ነበር። ኾኖም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ኦነግ፣ ሰኞ እለት ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ጎን የሰላም ድርድር እያለ በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የግንባሩ ጦር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉን የመከላክያ ሰራዊት እያሰማራ እንደሚገኝ ገልጾዋል። ግንባሩ፦«መንግስት ሰላማዊ መፍትሔውን ወደ ጎን በመተዉ፣ ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ ያለን ምርጫ እንደ በፊቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን የኛን ትግል መቀጠል ነዉ» ማለቱን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

መላኩ እጅጉ በተባለ የፌስቡክ ስም የቀረበው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ «እነዚህ ሰዎች በሽግግር መንግስቱ ጊዜ ውይይትን በውይይት መፍታት ወይም መታገል ከዛም ህዝቡን ከጎናቸው አድርገው መቀጠል እየቻሉ ሸሽተው ጫካ የገቡ ናቸው» ሲል ጽፏል። «እስካሁንም በኦሮሞ ህዝብ ስም ሲነግዱ የነበሩ ናቸው፤ ቄሮ ሲያልቅ የት ነበሩ አሁን ኦሮሞ ከሌሎች ብ/ብሄረሰቦች ጋር ተስማምቶና ተረጋግቶ መኖር ስጀምር ምነው ተንገሸገሹ?» ሲል ጠይቋል።

ተመስገን አያና፦ «ተወደደም ተጠላም ኦነግ ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት ያለው ድርጅት ነው፣» ሲል ፌስቡክ ላይ ጽፏል።   

«አሁን አርፋችሁ ወደ ሰላም መንገድ መጣችሁ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይሻላል» ያለው ደግሞ ኢትዮጵያ ትቅደም የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው።

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና ግድያ ለማስቆም በመንግሥት የተሰጠውን ማሳሰቢያ በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል አይ ዘመን በሚል የፌስቡክ ስም ቀጣዩ ተጽፏል።  «ትእዛዙ ዘግይቷል ምክኒያቱም በተለያዩ አካባቢዎች በአሉባልታ ወሬዎች እውነታ በሌለው ነገር ህዝብና ንብረት እየወደመ ነው። ስለዚህ ሀይ ሊባሉ ይገባል።» በአጭሩ «ፍቅር ፍቅር ሰላም ሰላም» ሲል የጻፈው ደግሞ ሙለራ ማሩ ነው።

Äthiopien Addis Abeba Ethiopian Airlines neuer Linienflug nach Eritrea
ምስል Getty Images/AFP/H. Tadese

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዐሥርተ ዓመት በኋላ አስመራ ሲያርፍ ለዓመታት የተለያዩ ቤተሰቦች ተቃቅፈው በእንባ ሲራጩ የሚታይባቸው በርካታ ፎቶግራፎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተሰራጭተዋል።

ሀገር ቤት በሚገኘው እና በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ ጥረት መጀመሩን በርካቶች አወድሰዋል።

በራኪ የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ያልታረቀ የለም ይሳካል እርቅ ይቅር ማለት ኃጢአትን ይደመስሳል በተለይ በሀይማኖት አባቶች ይህን አሳፋሪ ምእመናን መስማት አይገባም ነበር» ብለዋል።

በእርቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ተስፋ በተጣለበት በዚህ ውይይት ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ይገኛሉ ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ