1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነግ አመራሮች ውዝግብ 

ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2012

ይህ ረዥም የታሪክ ጉዞ ሂደት ግን ውጣውረዶች የነበሩበት፣የመከፋፈልና የስደት፣ የትግል ስልት ልዩነቶችና ሌሎችም ፈተናዎች የነበሩበት ስለመሆኑም ይነገራል። በተለይም ከጎርጎሮሳዊው 1998 ወዲህ በይፋ የአመራሮችን የየቅል መንገድ ማሳየት የጀመረው የግንባሩ የትግል ጉዞ እስከ ዛሬም ድረስ በተመሳሳይ መንገድ ለመጓዙ በውል መገንዘብ ይቻላል።

https://p.dw.com/p/3h5r1
 Logo Oromo Liberation Front

የኦነግ አመራሮች ውዝግብ 

ምስረታው ወደ ጎርጎሮሳዊው 1976 ዓ.ም. ይወስደናል። የትግል ስልት መነሻውን ህቡዕ በማድረግ ባካሄደው የመጀመሪያው ድርጅታዊ ምስረታው ጉባኤ የትጥቅ ትግልና ፖለቲካዊ ዓለማውን በማቀናጀት በይፋ እርምጃውን የጀመረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እነሆ በጉዙው 45 ዓመታትን አስቆጠረ። ይህ ረዥም የታሪክ ጉዞ ሂደት ግን ውጣውረዶች የነበሩብት፣ የመከፋፈልና የስደት፣ የትግል ስልት ልዩነቶችና ሌሎችም ፈተናዎች የነበሩበት ስለመሆኑም ይነገራል። በተለይም ከጎርጎሮሳዊው 1998 ወዲህ በይፋ የአመራሮችን የየቅል መንገድ ማሳየት የጀመረው የግንባሩ የትግል ጉዞ እስከ ዛሬም ድረስ በተመሳሳይ መንገድ ለመጓዙ በውል የሚያስገነዝቡ ነጥቦች አሉት።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦ.ነ.ግ) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ስማቸው በቀዳሚነት ከሚነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በርግጥ ድርጅቱ በተበታተነ የፖለቲካ ትግል መንቀሳቀስ የጀመረው ከ50 ዓመታት በፊት ስለመሆኑ ሲነገርለት፤ የነጻነት ትግሉን በማማከል ለመምራት ይቻል ዘንድ በጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 11 ቀን 1976 ዓ.ም. ባካሄደው መስራች ጉባኤ በይፋ ፖለቲካዊና ወታደራዊ የትግል ስልትን ተቀላቀለ፡፡

የኦሮሞን ብሄርተኝነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ስሙ አስቀድሞ የሚነሳው ይህ የፖለቲካ ድርጅት በዋናነት የያዘው ዓለማ የእኩልነትና የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ነው ይላሉ የግንባሩ ነባር አመራሮች፡፡ በዚሁ ላይ ሃሳባቸውን ለዶይቼ ቬሌ ያጋሩት፣ በአውሮፓውያኑ የቀን ቀመር ከ1989 እስከ 1998 የግንባሩ ሊቀመንበር በመሆንም ያገለገሉት አቶ ጋላሳ ዲልቦ ፓርቲው አንግቦ የተነሳው የብሔር ጭቆናን ማስቀረት ነው ይላሉ፡፡

Kenia OLF Rebellen
ምስል Jonathan Alpeyrie

የ1992ቱ የሽግግር መንግስት ምስረታ እና ያንን ተከትሎ የመጡት ተለዋጭ የፖለቲካ አካሄዶች ግን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባሰበውና ባለመው መንገድ እንዳይጓዝ ማድረጉ ነው የሚነሳው። ግንባሩን ከመጀመሪያው የምስረታ ጉባኤ ጀምሮ ለ 2 ዓመታት በሊቀመንበርነት የመምራት ዕድል አግኝተው የነበሩት ዶ/ር ዲማ ነገዎ በወቅቱ ያለ በቂ ዝግጅትና ከወቅቱ ጋር የተጣጣመ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዘው ለሽግግሩ መንግስት አለመቅረባቸው ብርቱ ዋጋን ለመክፈላቸው እንደ አንድ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡

ቢያንስ የሁለት ዓመታት እድሜን ይኖረዋል ተብሎ የተጠበቀው የሽግግር መንግስትም ፈጥኖ ወደ መንግስትነት ተሸጋገረ፡፡ ህ ደግሞ የሃሳብ ልዩነት ነበረው የተባለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በአፋጣኝ ወደ ውጭ እንዲገፋ ምቹ ሁኔታን ስለመፍጠሩ በኦ.ነ.ግ ነባር አመራሮች ይነሳል፡፡ እንደ አቶ ገላሳ ዲልቦ ገለጻም የወቅቱ የድርጅቱ ፈተናዎች የተለያዩ ገጽታዎች የነበሩት ቢሆኑም በሽግግር መንግስት ውስጥ ሳለ ግን ከሐራርጌ እስከ ወለጋ፣ ከቦሬና እስከ ባሬንቱ፣ ከመጫ እስከ ቱለማ ከህዝብ ዘንድ የተቸረው ድጋፍ የበትረ ስልጣኑን ቁንጮ ለያዘው ህወሃት በስጋት ታይቶ ነበር ነው የሚሉት፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በግራ ዘመም የፖለቲካ ዓላማው ከህወሃት ጋር ተመሳሳይ አመለካከት እንዳለው ያሳብቅበታል የሚሉ በርካቶች ቢሆኑም፤ የቆሙለትን ዓላማ ጨምሮ ከድርጅታዊ ባህል እስከ አቀራረጹ ግን ሰፊ ልዩነት በመካከላቸው መኖሩን የድርጅቱ አመራሮች ይገልጻሉ፡፡ ግንባሩ እስከ ሽግግር መንግስት ድረስ የአመራሮቹን የሃሳብ ልዩነቶችን አቻችሎ ቢጓዝም፤ ያን ተከትሎ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ በተበታተነ መንገድ ሲደረግ የነበረው ትግል የአንድነት ኮንፍረንስ እንኳ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ያልፈጠረ በመሆኑ ለግንባሩ መፈረካከስ እንደ ጉልህ ምክኒያት ይነሳል፡፡ የቀድሞ የግንባሩ አመራሮች ዶ/ር ዲማ ነገዎ እና አቶ ጋላሳ ድልቦም ይህንኑን ሀሳብ አጠናክረውታል፡፡

ደርግ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑን ያጠናከረበት እና ዋነኛ የመንቀሳቀሻ ስፍራውን በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ያደረገው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ገና በጅምር የትግል ጉዞው አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ወቅት ሆኖ ነው የሚነሳው፡፡ በዚህ ወቅት ኦነግ ከሶማሊያ የቀረበለትን የአጋርነት ጥያቄን ውድቅ በማድረጉ በጎርጎሳዊው 1978 ዓ.ም የሊቀመንበርነት ኃላፊነቱን ከዲማ ነገዎ የተቀበሉት ጃል መገርሳ በሪ በሶማሊያ መንግስት ተገደሉ፡፡ ከዚያን በኋላ የአመራሮች ግድያ የበረታበት ኦነግ አቶ ገላሳ ዲልቦ በ1989ኙ ድርጅታዊ ጉባኤ በሊቀመንበርነት እስከተመረጡበት ጊዜ ድረስ በኮሚቴ እየተመራም ቆዬ፡፡

Äthiopien Oromo-Befreiungsfront (OLF)
ምስል DW/N. Desalegn

የጎርጎሳውያኑ 1998 ግን የድርጅቱ አመራሮች አቅጣጫ የተለያየበት፡ የአመራሮች ልዩነትም በገሃድ የተስተዋለበት ይባልለታል፡፡ በዚህን ወቅት እነ አቶ ሌንጮ ለታ ከድርጅቱ ተለይተው በ2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)ን መሰረቱ፡፡ በዚሁ ዓመት እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመሩት ኦ.ነ.ግ መንገዳቸውን የለዩት ገላሳ ዲልቦም ከአባነጋ ጃራ ጋር ሌላኛውን ኦነግ መስርተው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡

እነዚህ የታሪክ ክንውኖች አልፎ የመጣው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኢትዮጵያ የተስተዋለውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትለው ከሁለት ዓመታት በፊት በሁሉም ክንፎቹ ወደ ሃገር ቤት ቢመለስም ፓርቲው አሁንም በበርካታ መንገድ የሚነሱበት ውዝግቦች ግን አልተለዩትም፡፡ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል የመሸጋገር አማራጭን ወስዶ ስምምነትንም አኑሮ ወደ አገር ቤት የተመለሰው ፓርቲው በምዕራብ እና በደቡብ ኦሮሚያ ታጥቀው በጫካ ይንቀሳቀሳል ከተባለው ሸማቂ ኃይል ጋር ስሙ ቢያያዝም እያስተባበለ ይገኛል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ አሁን አሁን ሃምሌ 19 እና 20 በቅርቡ በግንባሩ ዋና ጽህፈት ቤት ሊቀመንበሩን ሳያሳትፍ ተካሂዷል የተባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባን ተከትሎ የተስተዋሉ ክስተቶች በሰፊው እያነጋገሩ ነው፡፡ በወቅቱም የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በስብሰባው ላይ ያልተሳተፉት ለደህንነታቸው ነው በሚል በመንግስት የጸጥታ አካላት ተነግሯቸው በቤታቸው በመሆናቸው ነው ከመባሉ ውጭም ምስጢር መስለው የተቀመጡ ቁምነገሮች ለመኖራቸው ፍንጮች ነበሩ፡፡  የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትለው ሊቀመንበሩ ፈጽመው ከኃላፊነታቸው አልተነሱም ብለው ለዶይቼ ቨሌ ተናግረው ነበር፡፡

Äthiopien Bevölkerung begrüßen OLF-Führungskräfte
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

አቶ ዳውድ ኢብሳ ይህን ቃል ለማስተባበል የወሰደባቸው ግን ሰዓታት ብቻ ነበር፡፡ የማላውቀውና ይሁኝታ ያልሰጠሁት ስብሰባ ተካሂዷል ሲሉም ለመገናኛ ብዙሃን ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አቶ ዳውድ ከሃላፊነታቸው ሊነሱ ነው መባሉን ተከትሎ አቶ ቀጄላ አረ በፍጹም አሉ፡፡

ውዝግቡ መቋጫ ሳያገኝ ቀጠለ፡፡በጎርጎሮሳዊ ጁላይ 30 እና 31 ወደ ጽህፈት ቤታቸው ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን የጀመሩት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት አመራሮች ጋር ዳግም መስራት እንደማይፈልጉ አስረዱ፡፡ክስተቱም በጊዜያዊነት ወደ ጽህፈት ቤቱ ማንም እንዳይገባ የሚል ውሳኔ እንዲተላለፍ ምክንያት ሊሆን ቻለ፡፡ አቶ ዳውድ ግን የጽህፈት ቤቱን ለጊዜው ለሁሉም አካላት ዝግ የመሆኑን ጉዳይ የደህንነት ጉዳይ ይሉታል፡፡

ሌላው የፓርቲው ውዝግብም ሶስት የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባላት በሂልተን ሆቴል የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫን ተከትሎ ይፋ የወጣ ነው፡፡ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ አቶ ዳውድ ኢብሳ ነገሩን እንደማያውቁት ለሚዲያ በማስረዳት  በፊርማቸው ወጥቷል በተባለው መግለጫ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ ስድስት የስራ አስፈጻሚ አባላትን ከስራ አገዱ፡፡

ውሳኔው የድርጅቱ ህጋዊ አሰራርን ያልተከተለ ነውና ገቢራዊም አይሆንም  ያለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተራው የሚወስደውን አማራጭ ጠቆመ፡፡ ውሎም አላደረም የግንባሩን ሊቀመንበር በደንብ ጥሰት ወቅሶ በጊዜያዊነት ከኃላፊነታቸው ማንሳቱንም አስረዳ፡፡  

አሁን ላይ ሁለቱም አካላት ጉዳዩን ለድርጅቱ ህግና ቁጥጥር ኮሚቴ አስተላልፈው በመስጠት ውሳኔውን እየተጠባበቁት ይገኛሉ፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ድሮ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ጉዳዩን እያዩት ነው፡፡

Äthiopien Statement Oromo Liberation Front
ምስል DW/Seyoum Getu

እረጅም የትግል ሂደት እና ከጊዜው ጋር የተለዋዋጭነት ባህሪን አለማሳየት በፓርቲው ውስጥ ለሚፈጠሩ ልዩነቶች ዋነኞቹ ምክንያቶች ተደርጎ የሚነሱበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፤ ከተለያየም በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ያደረገው የአንድነትና የጥምረት ጥረቶቹ ፍሬ ሲያፈራለት አልተስተዋለም፡፡መሰል ጥረቶች ደግሞ ከተሞከሩበት ጊዜው አሁን አይደለም ይላሉ የደርጅቱ ነባር አመራር የነበሩ አቶ ገላሳ ዲልቦ፡፡

አሁን ላይ ግን መንታ መንገድ ላይ የቆመው የኦሮሞ ነጸነት ግንባር የአመራሮች ልዩነት በተካረረ አኳኋን ባልሆነ፣ በመግባባት መርህም ቢፈታ የሚሉ አመራሮች አሉ፡፡ ስለ ድርጅቱ የወደፊት እጣ ፈንታ አቶ ዳውድ ኢብሳን ለማነጋገር ዶቼቬለ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ውዝግቡ ከመጦዙ በፊት በሽምግልና ቢፈታ የሚል ሃሳብ አላቸው።

የሆነ ሆኖ ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳን በቤታቸው ያቆየው፤ ስልካቸውም እንዳይሰራ ሆኖ ከበርካታ ሰራ አስፈጻሚ አባላቶቻቸው ጋር ከተገናኙ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ ያስገደደውና የወደፊት ግንኙነታቸውንም በትልቁ አጠያያቀቂ ያደረገው የግንባሩ የመተጋገድ ውዝግቡ ወዴት ያመራ ይሆን?አብረን የምናየው የምንሰማው ይሆናል።

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ