1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ያለፍርድ እየማቀቁ ነው መባሉን

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5 2015

የፓርቲው አመራሮች መታሰር በኦነግ ላይ የሚደረግ ጫና ነው የሚሉት ሌላው የፓርቲው ባለስልጣን አቶ በቴ ዑርጌሳ፤ የፖለቲካ አመራሮቹ ታስረው የሚገኙት ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው ሲሉም መንግስትን ወቅሰዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Q0wZ
 Logo Oromo Liberation Front

የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ያለፍርድ እየማቀቁ ነው መባሉን

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት የተዘዋወረው በእስር ላይ ከሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች አንዱ አቶ ኬኔሳ አያና የተባሉ የፓርቲው ባለስልጣን ክፉኛ ተጎሳቅለውና ታመው እንደሚገኙ ምስላቸው አሳይቷል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) “ያለአግባብ ታስረውብኝ ይገኛሉ” ካሏቸው ስምንት ባለስልጣናቱ መካከል አብዛኛዎቹ በህመም ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በተለይም ሰሞኑን በጽኑ ህመም ላይ ይገኛሉ ያለው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ኬኔሳ አያና አሁን ላይ ብርቱ ህክምና እንደ ሚስፈልጋቸውም አመልክቷል፡፡ 
የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ከሚገኙት አቶ ኬኔሳ አያና ያለ ሰው ድጋፍም አይንቀሳቀሱም፡፡ “አቶ ኬኔሳ በጽኑ ታመው በሞትና በህይወት መካከል ቢሆኑም በቂ ህክምና እያገኙ አይደለም፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ተንገላተው መታሰራቸው ለነርቭ ህመም እንደዳረጋቸው ነው በሃኪም የተነገራቸው፡፡ ከዚህ በፊትም ወደ ሆስፒታሎች ሲመላለስ ነው የቆዩት፡፡ አሁን ደግሞ ያለ ክራንች እና ሰው ድጋፍ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ በሳምንት ሶስት ጊዜ ሆስፒታል እየተመላለሱም ህመም ውስጥ ነው ያሉት፡፡”  
አቶ ለሚ እንደሚሉት ከአቶ ኬኔሳ በተጨማሪ ሌላው የፓርቲው ፖለቲካል ኦፊሰር ገዳ ኦልጂራ እና ሌሎችም በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሰባት የኦነግ ባለስልጣናቱ ይታመማሉ፡፡ 
እነዚህ የፓርቲው አመራሮች መታሰር በኦነግ ላይ የሚደረግ ጫና ነው የሚሉት ሌላው የፓርቲው ባለስልጣን አቶ በቴ ዑርጌሳ፤ የፖለቲካ አመራሮቹ ታስረው የሚገኙት ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው ሲሉም መንግስትን ከሰዋል፡፡ 
ኦነግ በአገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህግ ተመዝግቦ ሰላማዊ ትግል ለመቀላቀል ነው ወደ አገር ውስጥ የገባው ያሉት አቶ በቴ፤ እነዚህ አመራሮችም ትጥቅ ፈተው በዚሁ የፖለቲካ ሂደት ብሳተፉም አብዛኞቹ ከ2012ቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት በኋላ ታስረው እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ 
በነዚህ የፓርቲው ባለስልጣናት ክስ ላይ የማይስማሙት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ፤ በእስር ላይ ያሉት የኦነግ አመራሮች ተብለው የተጠቀሱት መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ወይም መንግስት “ሸነ” ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ተጠርጥረው ነው፡፡ “ሲያዝ ኦነግ፤ ሲለቀቅ ደግሞ ሸነ እየሆነ የህዝቡን ሰላም የሚጎዳ እንጂ በህጋዊ መንገድ ሚንቀሳቀስ የኦነግ አመራር አላሰርንም፡፡ በስህተት እንኳ የታሰረ ካለ በተደጋጋሚ ከምርጫ ቦርድ በተጻፈልን ደብዳቤ የለቀቅናቸው አሉ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀ አካል ጋር የሚንቀሳቀሱ ከየትኛውም ፓርቲ ይሁን ተጠያቂ አድርገናል፡፡ ክሳቸው ውስብስብ በመሆኑ በሂደት ላይ ያለ ካልሆነ ያለ ህግ አግባብ ያሰርነው አካልም የለም” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ከዚህ በፊት በእስር ላይ ያሉ የኦነግ አመራሮቹ ያለ ህግ አግባብ በፖሊስ ታስሮ እንደሚገኙ በማረጋገጥ መግለጫ ማውጣቱን በተመለከተም የተጠየቁት ኮሚሽነር አራርሳ፤ ኮሚሽኑ የአንድ ወገን አስተያየት ይዞ ካልሆነ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አጣርተን መልስ ስንሰጥ ቆይተናል ብለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ከህግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ፖለቲካ አመራሮች መኖራቸውን አስተባብለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ዑርጌሳ እንደሚሉት ግን እስካሁን ለዓመታት በእስር ላይ በሚገኙ የኦነግ አመራሮቹ ላይ ከታጣቂዎች ጋር ይንቀሳቀሳሉ በሚል የቀረበባቸው ክስ አለመኖሩን አንስተው ሞግተዋል፡፡ “እነዚህን አመራሮች ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ጋር ለማገናኘት የሚሞክሩ ብኖሩም፤ እንዲህ ያለ ክስ እስካሁን አልተመሰረተባቸውም፡፡ ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸውም ነው በእስር ላይ የሚገኙት፡፡ ፍርድ ቤትም ስንቴ አሰናብቶአቸው ነው በእስር ላይ ያሉት” ብለዋል፡፡
የእስረኞቹ ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ሰባት የኦነግ አመራሮች፤ በአቃቤ ህግ የሚያስከስሳቸው የለም ተብሎ፤ በፍርድ ቤትም ነጻ የተባሉ ናቸው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በተለይም በጽኑ ታመዋል የተባሉት የኦነግ ባለስልጣን አቶ ኬኔሳ አያና ከአርቲስት ሃጫሉ ሁነዴሳ ግድያ ማግስት በ2012 ዓ.ም. ሚካኤል ቦረን እና ዳዊት አብደታ ከተባሉ ሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር የታሰሩ ናቸው፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ