1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ግጭትና ጥቃት ማብቂያዉ መቼ ነዉ?

እሑድ፣ ታኅሣሥ 30 2015

አራት ዓመት ባስቆጠረዉ ግጭትና ጥቃት የተገደለዉን ሰዉ ቁጥር አንዳዶች እስከ መቶ ሺሕ ያደርሱታል። ብዙዎች ግን በብዙ አስር ሺሕ የሚቆጠረዉ በሚለዉ ይስማማሉ።በሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ተፈናቅሏል።አንዳድ አካባቢ ከደረሰዉ ጥቃት ያመለጡ እንደሚሉት የሚፈፀመዉ ግድያ ሲበዛ ዘግናኝ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4LqHJ
Symbolbild Kerzen
ምስል picture-alliance/Panther Media/F. Salimi

ዉይይት፣ ለዘግናኙ ጥቃትና ግድያ ተጠያቂዉ ማነዉ?

ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ለዛሬዉ ዉይይታችን የዘር ግጭት፣ጥቃትና መፍትሔዉ በኦሮሚያ» የሚል ጥቅል ርዕስ ሰጥተነዋል። በአንዳዶች ግምት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የፈጀዉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ካለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ ጀምሮ ቆሟል።የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት እስካሁን ያለብዙ እንቅፋት ገቢር ማድረጋቸዉ ብዙዎችን አስደስቷል።

ኦሮሚያ ዉስጥ የሚደረገዉ በጎሳ ላይ ያነጣጠረ ግጭትና ጥቃት ግን ለአራተኛ ዓመት እንደቀጠለ ነዉ።የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈዉ ሕዳር ማብቂያ እንደዘገበዉ ሆሮ ጉዱሩ፣ምስራቅ ወለጋ፣ሰሜን ሸዋ፣ቄሌም ወለጋ፣ኢሉ አባ ቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ምስራቅ ሸዋ፣ምዕራብ ሸዋ፣ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣አርሲ እና ሁለቱ የጉጂ ዞኖች ሰዉ ጎሳዉ እየተለየ ይገደል፣ይቆስል፣ይፈናቀልባቸዋል።ኢትዮጵያዉያን በጋራ የሚቆሙት ስንት ሰዉ ሲሞት ነዉ?

አራት ዓመት ባስቆጠረዉ ግጭትና ጥቃት የተገደለዉን  ሰዉ ቁጥር አንዳዶች እስከ መቶ ሺሕ ያደርሱታል። ብዙዎች ግን  በብዙ አስር ሺሕ የሚቆጠረዉ በሚለዉ ይስማማሉ።በሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ተፈናቅሏል።አንዳድ አካባቢ ከደረሰዉ ጥቃት ያመለጡ እንደሚሉት የሚፈፀመዉ ግድያ ሲበዛ ዘግናኝ ነዉ።ሴቶች፤ሕፃናት አቅመ ደካሞች በጅምላ የተረሸኑበት፣ቤት እየተዘጋ እሳት የተለቀቀባቸዉ፣በስለት ተጨቅጭቀዉ የተገደሉበት አጋጣሚ አለ።

Äthiopien | Binnenvertriebene aus der Oromia Region in Debre Birhan
ምስል North Shewa Zone communication Office

በተደጋጋሚ እንደዘገብነዉ አብዛኞቹ ሟች ተፈናቃዮች የአማራ ተወላጆች ናቸዉ።ቁጥራቸዉ የአማሮቹን ያክል  አይሁን እንጂ የኦሮሞ ተወላጆች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸዉም ከጥቃትና ግድያ አላመለጡም።በጥቃቱ በርካታ ሕዝብ በተገደለባቸዉ አካባቢዎች 4 የተለያዩ ታጣቂ ኃይላት መኖራቸዉን የኢሰመኮ ዘገባ አረጋግጧል።

የመንግስት ፀጥታ ኃይላት፣መንግስት ራሳችሁን ከጥቃት ተከላከሉ ብሎ ያስታጠቃቸዉ፣የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር (ኦነግ ሸኔ) እና ከአማራ ክልል የተሻገሩ የተባሉ ታጣቂዎች ናቸዉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ግድያዉን እንዲያስቆም፣ተጠያቂዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ የሟቾች ቤተሰቦች፤ ተፈናቃዮች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የመብት ተሟጋቾች፣የሐገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።

Äthiopien Flüchtlinge in Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW

በቅርቡ ደግሞ የገዢዉ ፓርቲና የኦሮሞ ተወላጅ የምክር ቤት እንደራሴዎች፣መጫና ቱለማን የመሰሉ ማሕበራት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለማስቆም በተደረገዉ አይነት ድርድር የኦሮሚያዉም ግጭት እንዲፈታ አቤት ብለዋል።ከወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው ምሥራቅ ጎጃም ዞን የተጠለሉ ሰዎች አቤቱታ

እስካሁን ግን መንግስት  በኃይልም ይሁን በድርድር ግድያዉን ማስቆም የቻለ ወይም የፈለገ አይመስልም።ዓለም አቀፍ የሚባለዉ ማሕበረሰብና የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም የሚጠፋዉ ሕይወት፣ሐብትና ንብረት፣ የሚደርሰዉ ስቃይም ብዙም ያሳሰባቸዉ አይመስልም።የግጭት፣ግድያዉ ደረጃ፣የመንግስት እርምጃ ወይም ዳተኝነትና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ደንታ ቢስነት የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ሶስት እንግዶች አሉን።

ነጋሽ መሐመድ