1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዉያን በጋራ የሚቆሙት ስንት ሰዉ ሲሞት ነዉ?

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2015

አንዳድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደ ሚንስትር፣ወይም እንደ ሌላ ባለስልጣን ገዢዉ ፓርቲ በሚመራዉ ካቢኔ ዉስጥ ተቀምጠዉ የመንግስትን መርሕ እያስፈፀሙ ከፓርቲያቸዉ ፅሕፈት ቤት በሚሰጡት መግለጫ ግን ያንኑ የሚያገለግሉትን መንግስት ሲወቅሱ የመስማትን ያክል ግራ የሚያጋባ የወለፊድ እዉነት መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4LBx9
የኢትዮጵያ ምክር ቤት
የኢትዮጵያ ምክር ቤትምስል Solomon Muchie/DW

ኢትዮጵያ ስንት ሞት፣የስንቶች ስቃይ ይበቃት ይሆን

ኢትዮጵያዊዉ፣ ያዉ መቼም እንደ ዓለም ትልቅ ሁነት፣ደግሞም እንደ አዝናኝ ክስተት ከተቀረዉ ዓለም ጋር ጎል ቆጥሮ፣ የተሸናፊ-አሸናፊን ሐዘን-ፌስታ አጅቦ ወደ ራሱ ቀልብ፣ወደ ራሱ እዉነት መለስ ሲል በወለጋ እልቂት፣በአዲስ አበባ ቀዉስ፣በትግራይ ዉዝግብ መባተት-መባተሉን ቀጠለ።በአብዛኛዉ ወለጋ፣ሰፋ ሲል ኦሮሚያ  ክልል የሚደረገዉ ግጭት፣ጥቃትና ግድያ ያጠፋዉ ሕይወት፣ሐብት፣ንብረትና ያፈነቃለዉ ሰዉ ብዛት በሚዘረዘርበት መሐል የአዲስ አበባ ትምሕርት ቤቶች የተቃዉሞ፣ ጠብ ዉዝግብ አምባ ሆኑ።ሰሜን ኢትዮጵያን ዉስጥ የጠመንጃዉ ላንቃ ቢዘጋም የአዲስ አበባና የመቀሌ ገዢዎች በቃላት ለመጎሻሸም ሰበብ አላጡም።ኢትዮጵያ ሰላም ትጠላ ወይም፣ ሰላም ይጠላት ይሆን? ወይስ ኢትዮጵያዊዉ በግጭት፣ጥቃት፣ግድያ ዉዝግብ እንዲተላለቅ የፈረደበት አለ ይሆን? ብዙ ጊዜ ተጠይቋል። እንደገና ላፍታ እንጠይቅ። መልስ የለሽ ጥያቄ።

 

የግሪጎሪያኑ 2022 ሊጠናቀቅ 10 ቀረዉ።አየር ላንድ ከጎርጎሪያኑ 2021 መጀመሪያ ጀምሮ ለሁለት ዓመት የያዘችዉን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተዘዋዋሪ አባልነት መቀመጫን አመቱ ማብቂያ ላይ ታስረክባለች።የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሲሞን ኮቬኔይ ትንሺቱ አዉሮጳዊት ሐገር  በትልቁ ዓለም አቀፍ ድርጅት ትልቅ ምክር ቤት ዉስጥ የሰራችና የታዘበችዉን በገመገሙበት ጋዜጣዊ መግለጫዉ «ዓለም የዕብዶች ስፍራ ነች» አሉ-በቀደም።

«ዓለም ባሁኑ ወቅት የዕብድና የመከራ ስፍራ ናት።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትም ሙሉ በሙሉ ከተሳካለት  ተቋምነት ሩቅ ነዉ።ያለን ግን እሱዉ ነዉ።» ሚንስትሩ ከ«ዕብዶቹ ስፍራዎች» ቀዳሚ አብነት አድርገዉ ከጠቀሷቸዉ ሁለተኛዋ ኢትዮጵያ ናት።

የኦሮሚያ ተፈናቃዮች
የኦሮሚያ ተፈናቃዮችምስል Seyoum Getu/DW

«በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ እያለን ብዙ ነገሮች እንደሚሆኑና ምላሽ መስጠት እንደሚገባን  እናዉቅ ነበር።ይሁንና የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ምላሽ ሊሰጠዉ የሚገባ፣ ያገጠመንን ያክል የከፋ ግጭት ይኖራል ብለን ጭራሽ አልመን አናዉቅም።በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ያለቀበት የኢትዮጵያ ግጭት ይሁን ሌላ ስፍራ (የሆነዉ ይሆናል ብለን አላሰብንም)።በአብዛኛዉ ዓለም በዜና እንኳን በቅጡ አልተነገረም።በትክክል የርስ በርስ ጦርነት በነበረዉ በኢትዮጵያ (ግጭት) የደረሰዉን ሰብአዊ ስቃይ ለማሳወቅ አየር ላንድ ጥራለች።»

 

የአየርላንድ ጥረት፣የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዲፕሎማሲና ብልሐት፣የኃያላኑ ግፊት፣ የአዲስ አበባ-መቀሌ ተፋላሚዎች ድል-ሽንፈት፣ ብልጠት ይሁን ድክመት ብዙ መቶ ሺሕዎችን ያረገፈዉ የሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቆሟል።ተፋላሚ ኃይላት አዝጋሚም ቢሆን የተፈራረሙትን ስምምነት ገቢር እያደረጉ መሆናቸዉ እየተዘገበ ነዉ።

የመድፍ-አዳፍኔ፣ ጠመንጃ-ቦምቡ ድምፅ ጠፍቶ የስምምነቱ ገቢራዊነት የፈነጠቀዉ ተስፋ ደመቅ-ፈዘዝ በሚልበት ወቅት ሰሞኑን ወትሮም በሰዉ ደም በጎደፈዉ ወለጋ ምድር የሚረግፈዉ ሰዉ መበርከቱ በርግጥ ከማሳዘን በላይ ሊያስፈራ ይገባል።

የአየርላንዱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የገረማቸዉ  የሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ያደረሰዉ ሰብአዊ ጥፋት ለአብዛኛዉ ዓለም ለዜናነት እንኳ አለመብቃቱ ነዉ።የወለጋዉን ግጭትና በዘር ላይ ባነጣጠረ ግድያ የሚያልቀዉ ሰዉ ብዛት  ሰምተዉት ይሆን?

አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ   ዞን፣ወረዳ፣ቀበሌ፣መንደር ጎጥ እየጠራ፣ የተዘረረ አስከሬን፣ በየጉርጉዶ የታመቀ አካል፣ አንገቱ የቆረጠ፣ በጥይት የተበሳሳ፣ በጩቤ የተጨቀጨቀ ወገኑን ብዛት እየቆጠረ፣ ከሞት ያመለጡትን የስቃይ ጩኸት አንደሰማ ሶስት ዓመት ዞሮ ገጠመ።ዛሬም ቀጥሏል።                                       

ከአፍታ ከንፈር መጠጣ፣ከዕለት ድንጋጤ፣ ግርምት  በላይ ሰዉነታቸዉን በሰዉ ደም በክለዉ፣ ብካያቸዉን በሰዉ ደም የሚያጥቡ  ዕብዶችን እስካሁን ሀይ ባይ አልተገኝም።እና በርግጥ ዕብዱ ማነዉ?

ብሪታንያና አርጀንቲና እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1982 ፎክላንድስ በተባሉት ደሰቶች ይገባኛል ሰበብ በሚዋጉበት ወቅት የለንደን አሽሙረኞች የአርጀንቲናዎችን ቅይጥነት ለማሳጣት ደጋግመዉ የሚናገሯት ፌዝ ነበረች።«አርጀንቲናዊ ማለት----«የስጳኝ ቋንቋ የሚናገር ኢጣሊያዊ፣ፈረንሳይ ቤት ዉስጥ እየኖረ ብሪቲሽነኝ የሚል ነዉ።»የምትል ምፀት መሰል ፌዝ።

የቅይጦቹን፣በጣሙን የአዉሮጳ ስደተኞቹን ሐገር ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የመታት የምጣኔ ሐብት ቀዉስ ሲበዛ ከፍተኛ ነዉ።ባለፈዉ ወር የመሰረታዊ ሸቀጥ ዋጋ ከዘጠና በመቶ በላይ ተንቻሮ ነበር።

Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ደቡብ አሜሪካ፣ ስጳኝ፣ ኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ ሌላም ስፍራ የሚኖሩና የሚሰሩ የእግር ኳስ ተጫዎች፣አሰልጣኝ፣ አስተባባሪዎቻቸዉና ደጋፊያቸዉ  አንድ ሆነዉ  ላንድ ሐገራቸዉ  ትልቁን የእግር ኳስ ክብር ለማጎናፀፍ ግን የጥንታዊ አመጣጣቸዉ ቅይጥነት፣የሚኖሩ-የሚሰሩበት አካባቢ መለያየትም ሆነ የምጣኔ ሐብቱ ቀዉስ አልበገራቸዉም።

የአርጀንቲናዎች አንድነት ለኢትዮጵያዉያን የቅርብ  ምሳሌ ላይሆን ይችላል።ግን ኢትዮጵያዉያን መገዳደልን ለማስቆም በጋራ የሚቆሙ፣ ባንድነት የሚነሱ እኩል የሚጮኹት ስንት ሰዉ ሲያልቅ ይሆን?

ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት እንደራሴዎች ባለፈዉ ሳምንት በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሚካሔደዉ ግጭት፣ ግድያና ዉዝግብ እጅግ እንዳሳሰባቸዉ አስታዉቀዋል።80 የሚሆኑትን የምክር ቤት እንደራሴዎች ያስተባበሩት እንደራሴ ብዙአየሁ ደገፋ እንዳሉት ኦሮሚያ ዉስጥ ሰላም የለም።

Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

እንደራሴዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጀዉ ከኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦር (OLA) ጋር እንዲደራደር የሚጠይቅ ባለ 10 ነጥብ አቤቱታ ለፌደራሉና ለኦሮሚያ መንግስታትና ለሁለቱ ምክር ቤቶች አስገብተዋል።የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄዉን መቀበል-አለመቀበሉን እስከዛሬ በይፋ አላሳወቀም።

ይሁንና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር  አቤቱታዉ ከመቅረቡ በፊት በሰጠዉ መግለጫ ሸማቂዉ ቡድን የተደረጀ መዋቅር ስለሌለዉ ለመደራደር እንደሚቸገር አስታዉቆ ነበር።

የእንደራሴዎቹ አቤቱታ ሰሚ አገኘም አላገኘ የመንግስት መሪዎችንና የባለስልጣናትን ረጃጅም ዲስኩር እንዳዴም ስድብና ተግሳፅን እያዛጉ፣እያንቀላፉ ብዙ ጊዜ እያጨበጨቡ ሲያደምጡ በቴሌቪዥን ከሚታዩ ሕግ አዉጪዎች የሰላም ጥያቄ ብልጭ ማለቱ አበረታች ነዉ።አቶ ብዙአየሁ እንዳሉትም እርቅ የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ የለም-ሰይጣን እንጂ።

ይሁንና ለኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም ፣ለመግባባትና እርቅ  አቤቱታ ያቀረቡት እንደራሴዎች «ሰይጣን» ከሌለበት ምክር ቤት ዉስጥ የሌላ ክልል ወይም ጎሳ  እንደራሴን ያልቀየጡበት ምክንያት ሰይጣኑ ያለበትን ስፍራ እንድንፈልግ አያስገድድ ይሆን? ወይስ  በክልል ወይም በጎሳ ብቻ የመደረጀታቸዉ ነጸብራቅ ይሆን?

ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ የሚያጠያይቁ፣ የማይገቡ፣ግራ የሚያጋቡ ፖለቲከኞችና ፖለቲካዊ እርምጃዎች አሉ።አንዳድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደ ሚንስትር፣ወይም እንደ ሌላ ባለስልጣን ገዢዉ ፓርቲ በሚመራዉ ካቢኔ ዉስጥ ተቀምጠዉ የመንግስትን መርሕ እያስፈፀሙ ከፓርቲያቸዉ ፅሕፈት ቤት በሚሰጡት መግለጫ ግን ያንኑ የሚያገለግሉትን መንግስት ሲወቅሱ የመስማትን ያክል ግራ የሚያጋባ የወለፊድ እዉነት መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።

Äthiopien Vertriebene aus Wollega in Bahir Dar angekommen | Hauptstadt der Amhara-Region
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሰሞኑን አዲስ አበባ ትምሕርት ቤቶች ዉስጥ የኦሮሚያ ባንዲራ መሰቀሉና መዝሙር መዘመሩ ብዙዎችን አስቆጥቷል።ተቃዉሞም ቀስቅሷል።ባንዲራ አሰቃይ አዘማሪዎቹ የወሰዱት ርምጃና ርምጃዉ ያስከተለዉ ቁጣና ተቃዉሞ የሕግ፣ የአስተዳደር፣ ለሕዝብ የመገዛት መርሕ በጎሰኝነት ስሜት እየተጠለፈ መሆኑን ለማወቅ ተታኝ አያስፈልገም።

የወለጋዉ ግድያ መክፋት፣የአዲስ አበባዉ ቀዉስ፣ የእደራሴዎቹ አቤቱታ፣የአሜሪካና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ለኢትዮጵያ የሚኖረዉ ፋይዳ አስገምግሞ ሳያበቃ የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ጦር ባልሰፈረበት  የትግራይ አካባቢ ወርሮ በሎች ሐብት ንብረት እየዘረፉ መሆናቸዉን አስታውቋል።የህወሓት መሪዎች ለተቃራኒ አፀፋ አላመነቱም።በትዊተር ባሰራጩት አፀፋ  «እኛ እና የትግራይ ሕዝብ ማስከበር የማንችለዉን ሰላም ማንም ሊያስከበር አይችልም» ይላሉ።እና ግድያ፣ምስቅልቅል፣ ዉዝግቡም ቀጥሏል።

ነጋሽ መሐመኝ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ