1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ «203 ሚሊዮን ኩንታል» ተመርቷል

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

በዘንድሮ ዓመት እንደ ኦሮሚያ በሁሉም ዘርፍ የተሻለ የምርት ውጤት መኖሩን ያመለከቱት ባለስልጣኑ ሰሞኑን በገቢያ ላይ የምርት እጥረት ተከስቶ የህዝብን ምሬት ማስከተለውን ተከትሎ፤ የፖለቲካ ትርፍ የሚፈልጉ ያሏቸውና በስም ያልጠቀሳቸው ምርት በመደበቅ ህዝብን ያስመርራሉ ብለዋል

https://p.dw.com/p/4Or1Y
Äthiopien PK Hailu Adugna Oromia Region
ምስል Seyoum Getu/DW

«የምርት እጥረት የለም» የኦሮሚያ ክልል

 

በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ 203 ሚሊየን ኩንታል ሰብል መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ክልሉ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  እንዳስታወቀዉ ዘንድሮዉ ምርት ከዓማናዉ ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ7.3 በመቶ ብልጫ አለዉ።በሌላ በኩል ቦረና ዞንን ጨምሮ በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ለሚኖረዉ ሕዝብ መርጃ እስካሁን ከ1.2 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ መሰብሰቡን ተነግሯል፡፡፡

መንግስት በምግብ ዋስትና እራስን መቻል፣ ከውጪ ተመርቶ የሚገባን ምርት መተካት፣ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አተኩሮ ይሰራል ያሉት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ በዛሬ መግለጫቸው ስኬታማ ባሉት የምርት ዘመኑ ላይ አተኩረው ነው ምግለጫውን የሰጡት፡፡ በ2014/15 የምርት ዘመን 6.4 ሚሊየን ሄክታር መሬትም በክልሉ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 6.6 ሚሊየን ሄክታር በዘር መሸፈን መቻሉንም በማመልከት እስካሁን በክልሉ 203 ሚሊየን ኪንታል የሚጠጋ ምርት መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡ “ይህም ከአነድ ዓመት በፊት ከነበረው ምርታማነት ጋር ሲነጻፀር የ7.3 በመቶ እምርታ አለው ማለት ነው፡፡ ምርታማነትም በክልሉ በ2.7 እድገት አሳይቷል፡፡ የበጋ ስንዴ ምርትም ከወሰድን እስካሁን ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኖ ከ38 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡”

በዘንድሮ ዓመት እንደ ኦሮሚያ በሁሉም ዘርፍ የተሻለ የምርት ውጤት መኖሩን ያመለከቱት ባለስልጣኑ ሰሞኑን በገቢያ ላይ የምርት እጥረት ተከስቶ የህዝብን ምሬት ማስከተለውን ተከትሎ፤ የፖለቲካ ትርፍ የሚፈልጉ ያሏቸውና በስም ያልጠቀሳቸው ምርት በመደበቅ ህዝብን ያስመርራሉ ብለዋል በመግለጫቸው፡፡ “ከዚህ በፊት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ተንቀሳቅሰው ያልተሳካላቸው አሁን ደግሞ ህዝቡን በኑሮ ለማስመረር የሚያደርጉት እንቅስቀሴ አለ፡፡ የምርት ጭማሪ ነው እንጂ እጥረት የለም፡፡ መንግስት ችግሩን ለመፍታት በአንድ በኩል በህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች በኩል ምርት በገፍ እያቀረበ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ምርትን በሚደብቁ ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅርበት በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡”

በሌላ በኩል በኦሮሚያ በስፋት በአስር ዞኖች ገደማ ውስጥ ተከስቶ በተለይም እንደ ቦረና ያሉ አከባቢዎችን ክፉኛ የጎዳውን ድርቅ ጉዳት ለመቀነስ የክልሉ መንግስት የአጭር እና ረጂም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ኃይሉ፤ እስካሁን በተለያዩ መንገዶች ከህዝብ የተሰበሰቡ 1.2 ቢሊየን ብር የሚገመት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተሰባስቦ ለተጎጂዎች ተደራሽ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ “አሁን ቦረና በሁሉም ወረዳዎች ዝናብ ዘንቧል፡፡ ከተሰሩ 14 የውሃ ማቆሪያ ኩሬዎችም 11ዱ አሁን ውሃ ሊይዝ ችሏል፡፡ ድጋፍም ላደረጉ እውቅና እየሰጠን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን የግል እውቅናቸውን ለማግኘት በህዝብ ስም ገንዘብ ሰብስበው ያላደረሱትን እንዲያደርሱ እንጠይቃለን፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ስለድርቁ ሲዘግቡ ከሀሰት መረጃ መታቀብ አለባቸው፡፡ ህዝቡን በዘላቂነትም ለማቋቋም አሁንም ድጋፉ መቀጠል አለበት” ብለዋል አቶ ኃይሉ አዱኛ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፡፡   

ሥዩም ጌቱ 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ