1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መግለጫ

ማክሰኞ፣ ጥር 16 2015

“ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሸነ የፈጸመውን ጥፋት አማርኛ ተናጋሪው ጽንፈኛም ፈጽሟል፡፡ የኦሮሞ ቤትን ለይቶ አቃጥለዋል፤ በርካታ ንብረትንም ከ100 ሺህ በላይ ከብቶችን ጨምሮ ዘርፈዋል፡፡ ይህ ማህበረሰብ በሺዎች ተፈናቅለዋል”

https://p.dw.com/p/4MdYR
Äthiopien Oromia Ato Hailu Adugna
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መግለጫ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በምእራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኘው አራቱ የወለጋ ዞኖች ከማህበረሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት በአከባቢው ሰላም ስለሚሰፍንበት ሁኔታ ላይ ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት መድረሳቸው ተገለጸ፡፡ የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአካባቢው ለደፈረሰው ሰላም ሸኔንን እና አማርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው የክልሉ የመንግስት ባለስልጣናት ልዑክ በኦሮሚያ በከፍተኛ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ ከነበረው የክልሉ ምዕራባዊ ዞኖች ነዋሪዎች ጋር ምክክር አድርገው ነበር፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖቹ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቀለም ወለጋ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎች ጋር መክረዋል የተባሉት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፤ የክልሉ ፀጥታን  በዘላቂነት ማስፈን ስለሚቻልበት ሁኔታ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው በአራት አበይት ጉዳዮች ላይ በማጠንጠን መወያየታቸውን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል፡፡
በውይይቱ በቀዳሚነት ነዋሪዎቹ በአጽእኖት ያነሱት የሰላም እጦትና መፍትሄውን ማጠየቅ ነው ያሉት የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ ባለፉት አራት ዓመታት በፀጥታ ችግር ውስጥ የቆየው የአከባቢው ማህበረሰብ ሰላም ለመመለስ መንግስት ሁለት አማራጮችን ይዞ ሲሰራ እንደነበርና ይህንኑን ለህዝቡ ማስረዳት መቻሉን አንስተዋል፡፡አቶ ኃይሉ በአሸባሪነት የጠቀሱት ሸነ ያሉት በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን በነዚህ አከባቢዎች ለሰላም እጦቱ በዋነኛ ተዋናይነት ጠቅሰውታል፡፡ መንግስታቸው በሁለት መንገድ ማለትም የሰላም አማራጭን እና ወታደራዊ እርምጃዎችን በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለመመለስ ሲሰራ እንደቆየም ገልጸዋል፡፡ 
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳም ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ሰላም ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ውስጥ የህዝቡን ድጋፍ መጠየቃቸውንም አመልክተው፤ መንግስት “ሸነ” ያለውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ለቀውሶቹ ግንበር ቀደም ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው በመግለጫቸው አክለውም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ህዝብና ህዝብን የሚያጋጩ በአከባቢው እየተንቀሳቀሱ ንጹሃን ላይም ጥቃት ይፈፅማሉ ያሏቸው አማርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች በሚል የገለጹዋቸውን ጭምር መሆኑን ንስተዋል፡፡ “ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሸነ የፈጸመውን ጥፋት አማርኛ ተናጋሪው ጽንፈኛም ፈጽሟል፡፡ የኦሮሞ ቤትን ለይቶ አቃጥለዋል፤ በርካታ ንብረትንም ከ100 ሺህ በላይ ከብቶችን ጨምሮ ዘርፈዋል፡፡ ይህ ማህበረሰብ በሺዎች ተፈናቅለዋል፤ አማራም ይሁን ኦሮሞ ህዝባችን ናቸውና በነዚህ ሁለቱ ጽንፈኛ ሃይላት ላይ በመታገል መረጋጋት ይፈጠራል የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡” 
አስቀድሞም የመልማት ሰፊ ጥያቄ የነበረባቸው እነዚህ የአራቱ ወለጋ ዞኖች አከባቢዎች ባለፉት ዓመታት በከረመባቸው ግጭትና አለመረጋጋቱ በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን እና ማህበረሰቡም የእነዚህ መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ ላይ ጥያቄ ማንሳቱን ገልጸዋል፡፡ ሸነ ያሏቸው ታጣቂዎች “በጤና እና ትምህርት ተቋማት እንዲሁም መንገዶች ላይ ጥቃት ፈጽሟል አውድሟል፡፡ ከዚህ በፊት በቢሊየን ብር በጀት ፕሮጀክቶችን ለመስራት የታቀደውም በጸጥታ ችግር በመክሸፉ አሁን ይህን እልባት በመስጠት ወደ ስራዎች ለመግባት ለህብረተሰቡ ቃል ተገብቷል” ብለዋልም፡፡
አቶ ኃይሉ በመግለጫቸው አሁን ላይ በኦሮሚያ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን አንስተው በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሰው የታጣቂዎች አባላት በብዛት እጅ እየሰጡ ወደ ሰላማው ኑሮ እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ እየተመለሱ ነው የተባሉ የታጣቂዎች አባላት ብዛትን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ በነዚህ በጸጥታ እጦት ውስጥ የነበሩ ማህበረሰብ በስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነትም በከፋ ሁኔታ መስተዋሉና ህብረተሰቡም ይህንኑን አማሮ ማንሳቱም ተብራርቷል፡፡
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ባለማቋረጥ የተስተዋለው የሰላምና መረጋጋት እጦት በተለያዩ የክልል አከባቢዎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን አፈናቅሎ ለበርካቶች ሞትም ምክኒያት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላም እልባት የሰጠችው አገሪቱም ስለ ኦሮሚያው ግጭት አሁንም የሃይል እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላም ማምጣት የመንግስት አቋም ስለመሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡
ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ ጋር በስልክ የተወያዩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከትግራይ በተጨማሪ ስለኦሮሚያው ግጭት እልባት አንስተው መወያየታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡  

Äthiopien | Oromiya Region
ኦሮምያምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance


ስዩም ጌቱ


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ