1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዜናነህ መኮንን የጤና መቃወስ

እሑድ፣ ነሐሴ 12 2011

ዜናነሕ መኮንን ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ከጋዜጠኝነት በተለይም የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችን ተለይቶ አያውቅም። መጀመሪያ በኢትዮጵያ ራዲዮ፣ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በራዲዮ፤ በዝግጅቶች እና በዜና አቅራቢነት ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው። አንጋፋው ጋዜጠኛ ከወራት ወዲህ የጤና መቃወስ አጋጥሞታል።

https://p.dw.com/p/3O5wK
Journalist Zenaneh Mekonnen
ምስል DW/Z. Mekonnen

የዜናነህ መኮንን የጤና መቃወስ

ዜናነህ መኮንን ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ከጋዜጠኝነት በተለይም የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችን ተለይቶ አያውቅም። መጀመሪያ በኢትዮጵያ ራዲዮ፣ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በራዲዮ፤ በዝግጅቶች እና በዜና አቅራቢነት ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው። 

ወደ እስራኤል ከተሰደደ በኋላም በተለያዩ የራዲዮ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና በኢንተርኔት የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ ይታወቃል። በኢየሩሳሌም የዶይቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የመካከለኛው ምሥራቅን የፖለቲካ-ዲፕሎማሲን ውጥንቅጥን በመዘገብ እና በመተንተን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። 

Bücher von Zenaneh Mekonnen
ምስል DW/Z. Mekonnen

ዜናነህ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ የሁለት መጽሐፍት እና የግጥሞች ደራሲ ነዉ። “ነጻነት” የተሰኘው የበኩር ስራው በጣሊያን የአምስት ዓመት የወረራ ወቅት የነበረውን ጦርነት የሚያሳይ ታሪካዊ ልቦለድ ነው። በሁለተኛ መጽሐፉ “ከጣራው ስር” ደግሞ የአዲስ አበባን ድብቅ የማህበራዊ ህይወት በልቦለድ ከሽኖ አቅርቧል። “በረከተ ራዕይ” የተሰኘ በድምጽ የተቀረጹ የግጥም ስብስቦችም አሉት።   

ጋዜጠኛው ከጎርጎሮሳዊው 2013 ጀምሮ የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የጣቢያ መክፈቻ እና በዝግጅቶች መግቢያነት የሚጠቀምባቸው ማስተዋወቂያዎች አንባቢም ነዉ። እውቁ ጋዜጠኛ ከጥቂት ወራት በፊት የገጠመው የኩላሊት ሕመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። 

ዜናነህ ሁለቱም ኩላሊቶቹ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ሐኪሞቹ የነገሩት ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። ከኩላሊቶቹ ቢያንስ አንዱ በንቅለ ተከላ ካልተቀየረ የጤንነት ሁኔታው አሁን ካለበትም ሊከፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀውታል።  

ዜናነህን የገጠመውን የጤና መቃወስ አስመልክተን አነጋግረነዋል። ስለ ጋዜጠኝነት ህይወቱ፣ ስለ መጽሐፍቶቹ፣ የህዝቡን እርዳታ ስለጠየቀበት የኩላሊት ህመሙ አውግቶናል።

ሙሉ ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ